Get Mystery Box with random crypto!

የልጃቸውን ገዳይ እግር ያጠቡት ኢትዮጵያዊ አቶ ማቲዎስ ደስታ የ85 ዓመት አዛውንት ናቸው። አሁን | Skyline media

የልጃቸውን ገዳይ እግር ያጠቡት ኢትዮጵያዊ

አቶ ማቲዎስ ደስታ የ85 ዓመት አዛውንት ናቸው። አሁን የሚኖሩት ሀዋሳ ይሁን እንጂ ትውልድ እና እድገታቸው ዎላይታ ነው።

ድፍን የሀዋሳ ህዝብ ያወቃቸዋል። ያከብራቸዋል። ‘ኢንጅነር’ እያለም ይጠራቸዋል።

‘ኢንጅነር’ የሚለውን ስያሜ በትምህርት ያገኙት አይደለም።

ለሰላሳ ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩ በቤት እና ህንጻ ግንባታዎች በመሳተፋቸው ነዋሪው የሰጣቸው እንጂ።

በሀዋሳም የኮንስትራክሽን ፍቃድ አውጥተው በርከት ያሉ ግንባታዎችን አከናውነው ተመስግነዋል።

‘ኢንጅነር’ በዚህ ብቻ አይደለም የሚታወቁት።

መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ አነስተኛ ቢሮ በመክፈት ‘የእርቅ አገልግሎት’ ይሰጣሉ።

‘የእርቅ አገልግሎት’?! - ግር ሊያሰኝ ይችላል። የሀዋሳ ነዋሪ ግን በደንብ ያውቀዋል።

የ‘ኢንጅነር’ እውቅና ግን በዚህ ብቻ አያበቃም። እስከዛሬ ድረስ ‘ጉድ’ እየተባለ የሚወራ ነገር ፈጽመዋል - የልጃቸውን ገዳይ ማረሚያ ቤት ድረስ ሄደው ‘ይቅር ለእግዚያብሔር ብያለሁ’ ብለዋል።

ይቅርታ ማድረግ ብቻ ሳይሆን እግሩንም አጥበዋል። ነገሩን አንድ በአንድ እንየው!

‘ኢንጅነር’ ማቲዎስ እና ሟቹ ልጃቸው
አቶ ማቲዎስ ደስታ የ85 ዓመት አዛውንት ናቸው። አሁን የሚኖሩት ሀዋሳ ይሁን እንጂ ትውልድ እና እድገታቸው ዎላይታ ነው።

በወጣትነት ዘመናቸው በመጀመሪያ የብረታ ብረት በመቀጠል የግንባታ ስራዎች ላይ እየተቀጠሩ ሰርተዋል።

በኋላም በግንባታ ሙያው የያዙትን ልምድ በማጠናከር እና ፍቃድ በማውጣት በተለይም በደቡብ ኢትዮጵያ ግንባታ ሲሰሩ ኖረዋል። በዚህ ስራቸው ያልረገጡት የኢትዮጵያ ክፍል የለም።

ከ54 ዓመታት በፊት በ1960 ዓመተ ምህረት ደግሞ ትዳር መሰረቱ።

“በትዳሬ ደርዘን ልጆችን አፍርቻለሁ” የሚሉት አቶ ማቲዎስ ከ12 ልጆቻቸው 12 የልጅ ልጆችን እንዳዩም ይናገራሉ።

ከልጅ ልጇቻቸው አንደኛዋ የሟቹ ልጃቸው የእስራኤል ማቲዎስ ልጅ ነች። አሁን የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን እየተከታተለች ነው።

እስራኤል “በጣም ሙያ ያለው የምወደው ልጄ ነበር” የሚሉት አቶ ማቲዎስ ከአስራ ሁለቱ ልጆቻቸው 5ኛው በሆነው እስራኤል ሞት እጅግ አዝነው እንደነበር ይገልጻሉ።

በ1998 ዓመተ ምህረት አንድ ቀን ከምሽቱ አምስት ሰዓት አከባቢ እስራኤል በሚኖርበት አካባቢ ግጭት እንደተፈጠረ እና ልጃቸውም ጉዳት እንደደረሰበት ለአቶ ማቲዎስና ቤተሰቦቻቸው ይነገራቸዋል።

“በዚያን ጊዜ ባለቤቴ በህይወት ነበረች። ሌሎች ሰዎችም ነበሩ ሮጠው ሄዱ - ለማየት። እኔ ግን ተንበርክኬ ጸለይኩ። ጸሎቴን ጨርሼ ስሄድ ሰዎች ተሰብሰበው ደረስኩ። ከዝያ ፖሊሶች በምርመራ አጣርተው [አስክሬኑን] አመጡ” ሲሉ የሚያስታውስት አቶ ማቲዎስ በተፈጠረ ጸብ ልጃቸው በስለት ተወግቶ መገደሉን ይናገራሉ።

“ልጄን የገደልከው አንተ ነህ እኔ ግን አንተን እወድሃለሁ”

አቶ ማቲዎስ ደስታ እና በስለት ተወግቶ የተገደለው ልጃቸው "የልጄ ገዳይ ተፈረደበት እና ማረሚያ ቤት ገባ። ማረሚያ ቤት ገባሁና ሰው [ገዳዩ] እሱ ነው ብሎ በርቀት አሳየኝ። እሱ ሳያየኝ ከኋላው ሄድኩ። ከዛ እግሩን ያዝኩት። ‘ለምን ያዝክ?’ አለኝ። ‘አይ ያንተን እግር ለማጠብ ነው የመጣሁት’ አልኩት።

‘ለምን አለ?’ ‘ልጄን የገደልከው አንተ ነህ እኔ ግን አንተን እወድሃለሁ አልኩት። ልጄን እስራኤልን ገድለሃልና አንተ የኔ ልጅ ትሆናለህ አልኩት።’

[ይህንን ሲሰማ] አፈር ላይ ተንከባለለ። አትንከባለል አልኩት። በእጄ ሃይላንድ ይዤ ነበር በዛ ነው ያጠብኩት። ...ዶክመንት አዘጋጀሁ እና ጉዳዩ ወደ ይቅርታ ቦርድ ሄደ። ከዚያም ተፈታ” ሲሉ ያኔ የሆነውን ያስታውሳሉ።

“ሰው እንኳን ልጁን የገደለበትን የሰደበበትን ይቅር ለማለት ሊቸገር እንደሚችል አውቃለሁ” የሚሉት አዛውንቱ ሰዎች ለማመን የሚቸግራቸውን ይህንን ነገር ፈጽመውታል።

ይሄ ነው ሰውን ‘ጉድ’ ያሰኘው። ሰውን ያስገረመው። እውነት አልመስልህ ያለው።

“ ‘አንተ ይቅርታ ስታደርግ ወንድሞች ልጆች ቤተሰቦች አይቀየሙህም ወይ? ያሉኝ አሉ።

እኔ ይሄንን አላውቅም አእምሮዬ ውስጥ የተሞላው ይቅር በል የሚል ነገር ነው እንጂ ያን ነገር የሚያውቀው እግዚያብሔር ነው’ ነው ያልኩት።

የኔ ልጆች እግዚያብሔርን ስለሚያመልኩ ሌሎች [ደግሞ] ስለ እኔ ስለሚያውቁ ሌላ ነገር አልተናገሩም” ሲሉ ያስረዳሉ።

ቢቢሲ ይቅርታ ያደረጉለትን ሰው እግር ያጠቡት በምን ምክንያት ነው? ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ጌታ ኢየሱስ እግር አጥቧል። ይሄንን ለማስተማር ነው ራሱን ዝቅ ያደረገው” ስለዚህም በሚያምኑበት እምነት መሰረት ፍጹም ይቅርታ ማድረጋቸውን ለመግለጽ ይህንን ፈጽሜያለሁ ብለዋል።

‘ኢንጅነር’ ይቅርታ ማድረጋቸውን የሰሙት የገዳይ ቤተሰቦች “እርስዎ ይህንን ካደረጉ ምን እናድርግልዎት” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታውሳሉ።

እሳቸው ግን “እኔ ዋጋውን ከሰማይ ነው የማገኘው” ብለው ምንም አይነት የውለታ ምላሽ አልተቀበሉም።

ከዚህ በኋላ ከገዳዩም ይሁን ከቤተሰቦቹ ጋር ተገናኝተው አይውቁም። እሳቸው ይቅርታ ያደረጉለትን ሰው ቢያገኙትም ቢጠይቃቸው ደስ ይላቸዋል። ሆኖም ከዚያ ቀን በኋላ አልተገናኙም።

“ተጠራጥሮ ይሆናል። ይቅርታ ያደረገው ሌላ ነገር አስቦ ይሆናል ብሎ ይሆናል የጠፋው” ብለዋል።

‘ማንም የማይደፍረውን’ ይህንን በማድረጋቸው የመንፈስ እርካታ እንዳገኙ የሚጠቅሱት አቶ ማቲዎስ ውሳኔያቸው በህይወታቸው “እጅግ ደስተኛ” እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ይገልጻሉ።

“በሀገር ስለሚወራ፣ የእግዚያብሔር ቃል ‘ይቅርታ አድርጉ’ ስለሚል [ያን ስላደረኩ] በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲሉም አክለዋል።

አቶ ማቲዎስ በሀዋሳ ከተማ የእርቅ አገልግሎት ይሰጣሉ።

የ‘ኢንጅነሩ’ የእርቅ አገልግሎት
በነገራችን ላይ፣ ኢንጅነሩ በደቡብ ክልል የሀገር ሽማግሌም ናቸው።

አቶ ማቲዎስ በመኖሪያ ቤታቸው በከፈቱት ቢሮ አማካኝነት ደግሞ ያለምንም ክፍያ የእርቅ አገልግሎት ይሰጣሉ።

በርግጥ ይህንን አገልግሎት የጀመሩት ልጃቸው ከመገደሉ እና እሳቸውም ይቅርታ ከማድረጋቸው በፊት ነው። 1995 ዓመተ ምህረት አካባቢ።

አገልግሎታቸው ከሳቸው ስም ጋር በሀዋሳ ከተማ የገነነው ግን ከዚያ ክስተት በኋላ ነው።

‘ይቅር በሉ’ ‘ይቅርታም ጠይቁ’ ‘ታረቁ’ ‘ቂም አትያዙ’ እያሉ ይመክራሉ። በተግባር የተደገፈ ምክር!

ከቤታቸው መግቢያ ላይ የእርቅ አገልግሎት እሰጣለሁ የሚል ማስታወቂያ ለጥፈዋል።

በራቸው ደግሞ እርቅ ለሚፈልግ ለየትኛውም ሰው ክፍት ነው።

እሳቸው ይህንን አገልግሎት በሁለት አይነት መልኩ ያከናውኑታል።

አንድ: ሁለት ያልተስማሙ ሰዎች ወደሳቸው መጥተው ‘አስማሙን’ ‘ፍረዱን’ ይላሉ።

እሳቸውም በቻሉት መንገድ ለማስታረቅ ይሞክራሉ። የማይታበየው ሃቅ ግን የመጡት ሰዎች ቢያንስ በሳቸው ፊት ተማምነው እና ተስማምተው መውጣታቸው።

ሁለት: የተጣሉ ሰዎች መኖራቸውን ሲሰሙ ተበድያለሁ ብሎ የሚያስበው ሰው ጋር ሄደው እግር ላይ ወድቀው እና እግር አጥበው ይቅርታ እንዲያደርጉ ይለምናሉ።

“ከሳሽ እና ተከሳሽ እኔ ቢሮ ከመጡ በኋላ ከሳሹን ተንበርክኬ እግር አጥባለሁ። እሱ ‘እንደዚህ ያለ ዕድሜ ኖረው፤ እንደዚህ ያለ ኮንትራክተር የነበሩ፤ እንዲህ ያሉ የልጆች አባት ሆነው እግር ያጥባሉ ብለው እሺ’ ይላሉ’” ብለዋል።

ቁጥሩን በትክክል ባያውቁትም የተለያዩ ባለትዳሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን በዚህ መልኩ ወደ እርቅ መመለሳቸውን ይናገራሉ።