Get Mystery Box with random crypto!

ስንክሳር ነሐሴ 26 † እንኳን ለእናታችን ብጽዕት ሣራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረ | ስንክሳር በየቀኑ

ስንክሳር ነሐሴ 26

† እንኳን ለእናታችን ብጽዕት ሣራ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †

††† ቅድስት ሣራ ብጽዕት †††

† አበው እናታችን ሣራን " #ቡርክተ_ማሕጸን" ይሏታል:: (የቅዱሱ ዘር የይስሐቅ እናት ናትና) በዚያውም ላይ የደጉ ሰው የአብርሃም ሚስት ናት:: ልክ በዓለም ታሪክ "ከጠንካራና ስኬታማ ወንዶች ጀርባ ጠንካራ ሴቶች አሉ" እንደሚባለው ከአብርሃም አባታችን ስኬታማ የቅድስና ሕይወት ጀርባ ብጽዕት ሣራ አለች::

ለአብርሃም አባታችን መጽሐፍ የተናገረው ክብር ሁሉ ለቅድስት ሣራ ይገባታል:: አንድም ገንዘቧ ነው:: ቅድስቷ እናት ደጉ አብርሃምን ያገባችው ገና በከላውዴዎን (በ2ቱ ወንዞች መካከል) ሳለ ነው:: ገና ከልጅነቷ ጀምራ አብርሃምን "ጌታየ" እያለች ታገለግለው እንደ ነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል:: (1ዼጥ. 3:5)

በዚህም ከብራበታለች: ገናበታለች እንጂ አልተጐዳችበትም:: አብርሃም ወደ ካራን ሲወጣ "ለምን?" አላላችም:: እንዲሁ ለፈቃደ እግዚአብሔር ታዘዘች እንጂ:: በካራን ታራን ቀብረው: በፈጣሪ ትዕዛዝ ወደ #ከነዓን ሲፈልሱም ቅድስት ሣራ አልተቃወመችም::

ለፈጣሪዋ ትዕዛዝና ለባሏ ስትል ርስቷን: ሃገሯን: ዘመዶቿን ሁሉ ትታ ሔዳለች:: ይሔውም በጐ ምናኔ ነው:: እናታችን ሳራ በከነዓን የተመቸ ነገር አልገጠማትም:: ከአንዴም ሁለቴ በረሃብና በድርቅ ምክንያት ወደ ግብጽ እና #ጌራራ ተሰደዋል::

በዚያም ፈርዖን "እነካለሁ" ቢል እግዚአብሔር ተቆጥቶ: ፈርኦንንና ግብጽን በደዌ መታ:: በዚህም ክብረ ሣራን ተመለከትን:: ከስደት መልስም በኬብሮን (በተመሳቀለ መንገድ ላይ) ድንኩዋን ሠርተው የወጣ የወረደውን ሲያበሉ: እንግዳ ሲቀበሉ ኑረዋል:: (ልብ በሉልኝ ይህን ትጋትና ደግነት ያሳየችውን ቅድስት ሣራን ልናከብራት ይገባል)

እድሜ ዘመኗን ያሳለፈችው እንግዳ በመቀበል: እግዚአብሔርን በማምለክ ነው:: ምንም እንኩዋ ማሕጸኗ ለጊዜው ቢዘጋ ተስፋ አልቆረጠችም:: ለአብርሃምም ከአጋር እንዲወልድ ፈቃድ ሰጥታለች::

ዕድሜዋ 89 ዓመት በሆነ ጊዜ ሰይጣን እንግዳ እንዳይመጣ ለ3 ቀናት ቢያስቀርባቸው እንደ ባሏ እርሷም 3 ቀናትን ያለ ምግብ አሣልፋለች:: በ3ኛው ቀን ሥላሴን በቤቷ አስተናግዳለች:: ስለ ክብሯም ከ3 መሥፈሪያ ዱቄት ለውሳ ያዘጋጀችውን እንጐቻ ሥላሴ በልተውላታል:: (ምንም ሥላሴ ምግብን ባይመገቡም)

የሥላሴ በዚያች ድንኩዋን ውስጥ መስተናገድ ታላቅ ምሥጢር አለው:: ከግብዣው በሁዋላም እግዚአብሔር አለ:- "አመ ከመ ዮም እገብእ ኀቤከ . . . እንዲሁ ከርሞ እመለሳለሁ: ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች" አለው::

ያን ጊዜ ሣራ በውሳጤ ሐይመት (በድኩዋኑ ውስጥ) ሆና ሰምታ ሣቀች:: ለምን ሳቀች ቢሉ:- እጅግ ደስ ቢላት! አንድም ቢገርማት:: ይሕስ በምን ይታወቃል ቢሉ:- ልጇ " #ይስሐቅ" የተባለው "ለእናቱ ሣቅን: ደስታን ያመጣ" ለማለት ነውና::

ሥላሴም:- "ምንት አስሐቃ ለሣራ በባሕቲታ: እንዘ ትብል ዓዲየኑ እስከ ይእዜ: ወእግዚእየኑ ልሕቀ: ቦኑ ነገር ዘይሰዓኖ ለእግዚአብሔር - ሣራን ምን አሳቃት? ለእግዚአብሔርስ የሚሳነው ነገር አለን" ብለዋል::

ቅድስት ሣራ በ90 ዓመቷ ይስሐቅን ወልዳ በቀሪ ዘመኖቿ በደስታ ኑራለች:: በዚህች ቀንም በመልካም ሽምግልና ዐርፋ: አባታችን #አብርሃም ከታላቅ ሐዘን ጋር ቀብሯታል:: ሐዋርያው #ቅዱስ_ዻውሎስ ብጽዕት ሣራን በበጐ ምሳሌ መስሏታል:: (ዕብ. 11:11)

† ቅዱሳን ሞይስስና ሣራ †

† እነዚህ ቅዱሳን ግብጻውያን የአንድ እናት: የአንድ አባት ልጆች ሲሆኑ የነበሩትም በዘመነ ሰማዕታት ነው:: ከወላጆቻቸው ጋር በሥርዓተ ክርስትና አድገው ዕድሜአቸው ለአካለ መጠን ሲደርስ ወላጆቻቸው ሞቱባቸው::

ያን ጊዜ ቅዱስ_ሞይስስ እህቱን ቅድስት ሣራን ጠርቶ "እህቴ! እኔ ወደ ገዳም መሔዴ ስለሆነ አንቺ ባል አግብተሽ: ሃብት ንብረቱን ወርሰሽ ኑሪ" አላት:: #ቅድስት_ሣራ ግን መልሳ "እንዴት እኔን በዚህ ዓለም ወጥመድ ውስጥ ትተወኛለህ? ሁለታችንም ከአንድ ማሕጸን ነን:: ስለዚህ ላንተ የምትፈልገው ሁሉ ለእኔም ያስፈልገኛልና እኔም መናኝ ነኝ" አለችው::

ቅዱስ ሞይስስ የልቡናዋን መጨከን ሲያይ ነዳያንን ሰበሰበ:: ገንዘቡን: ቤቱን: ሃብቱንና ንብረቱን ሁሉ በየስልቱ ለነዳያን አካፈለ:: ሳይዘገይም እህቱን ይዞ ወደ በርሃ ተጉዋዘ:: እርሷን ከደናግል ገዳም አስገብቶ እርሱ ከወንዶች ገዳም ውስጥ መነኮሰ::

ለ10 ዓመታት ሁለቱም ለፈጣሪያቸው በጾምና በጸሎት: ከስግደት ጋር ሲገዙ: ለአባቶችና እናቶች ደግሞ በትሕትና ሲታዘዙ ኖሩ:: በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አንድም ቀን ተገናኝተው አያውቁም ነበር:: አንዱ ለሌላኛው ተግቶ መጸለይን ግን ቸል አላሉም::

ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የመከራ) ነውና መከራው እየገፋ ሲመጣ ቅዱስ ሞይስስ አንድ ነገር አሰበ:: በክርስቶስ ስም ደሙን ለማፍሰስም ወሰነ:: ወደ ከተማ ከመውጣቱ በፊት ግን ለቅድስት ሣራ መልዕክት ላከባት:: "እኔ ወደ ምስክርነት እየሔድኩ ስለሆነ ቸር ሁኚ" የሚል ነበር መልእክቱ::

እርሱ ይህንን ብሎ ወደ ከተማ ሲሔድ ግን መንገድ ላይ እህቱን አገኛት:: ገርሞት የፍቅር ሰላምታን ከተለዋወጡ በሁዋላ "እንዴት መጣሽ?" ቢላት "ወንድሜ! ቀድሞም ነግሬሃለሁ:: ላንተ የምትፈልገው የድኅነት መንገድ ሁሉ ለእኔም ያስፈልገኛል" አለችው::

ሁለቱም ተያይዘው ወደ መከራ አደባባይ ደረሱ:: በዚያም ስመ ክርስቶስን ሰብከው: ብዙ መከራንም ተቀብለው በዚህች ቀን ሰማዕት ሆነዋል::

† አምላከ ቅድስት ሣራ ደግነቷን: መታዘዟን ያሳድርብን:: ከበረከቷ: ከሌሎችም ቅዱሳን በረከትን ይክፈለን::

† ነሐሴ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ብጽዕት ሣራ (የአብርሃም ሚስት)
2.ቅዱሳን አባ ሞይስስና እህቱ ሣራ (ሰማዕታት)
3.ቅዱሳን አጋቦስና ቴክላ (ሰማዕታት)

† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.ቅዱስ አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †


ቤተሰብ ይሁኑ

https://t.me/Sinksar
https://t.me/Sinksar
https://t.me/Sinksar