Get Mystery Box with random crypto!

ዕለተ ሠሉስ፣ ዕለተ ትምህርት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሠሉስ (ማግሰኞ) ስ | ሥርዓተ ቤተክርስቲያን Tube

ዕለተ ሠሉስ፣ ዕለተ ትምህርት

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሠሉስ (ማግሰኞ) ስለ ፍርድ ቀንና ስለ ቤተ መቅደስ መፍረስ ሲያስተምር ውሏል። በወንጌል እንደተጻፈው በማለዳ ሲያልፉ ቅዱስ ጴጥሮስ በዕለተ ሰኑይ የተረገመችው የበለስ ዛፍ ከሥሯ መድረቋን አይቶ “እነሆ የረገምካት በለስ ደርቃለች” አለው። ጌታችንም ከዚህ በመነሳት በዚህች ዕለት ስለ እምነትና ስለ ይቅርታ አስተምሯል። (ማር. ፲፩÷፳-፳፮)
ጌታችን ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች መጥተው ‹‹ከምድራውያን ካህናት አይደለህ፣ ከምድራውያን ነገሥታት ወገን አይደለህ፣ ይህን የምታደርግ በምን ሥልጣን ነው?›› ብለው ጠየቁት፤ እርሱም መልሶ ጠየቃቸው፤ ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነው?›› እነርሱም ከሰማይ እንዳይሉ አያምኑበትም፤ ከምድር እንዳይሉ ሕዝቡን ፈሩና ‹‹አናውቅም›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹እኔም አልነግራችሁም›› ብሎ ረታቸው፡፡
(ማቴ.፳፩፥፲፫-፳፫፣ማር.፲፩፥፳፯፣ሉቃ.፳፥፳፩-፵) ‹‹በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋልና ያዘዟሁን ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ፡፡ ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፤ እነርሱ ግን በጣታቸውስ እንኳ ሊነኩት አይወዱም›› በማለት እየወቀሰ ተናግሯል፡፡ በዚህም ዕለቱ የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” በማለት እንዳስተማረን በሃይማኖታችን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችንና በሥነ ምግባራችን የጥርጥርና የክፋት ትምህርት ከሚዘሩ ሰዎች ራሳችንን መጠበቅና መጠንቀቅ ይገባናል። (ማቴ.፲፮÷፯)

ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስ ረዥም ትምህርት በማስተማሩ ምክንያት ዕለተ ሠሉስ “የትምህርት ቀን” ይባላል።