2022-05-14 20:51:59
"
የዝማሬ አገልግሎት ወደ ክብሩ መመለስ አለበት"
‹‹… ቤተክርስቲያን ባለፉት ሁለት ሺህ አመታት መስቀሉን ማእከል ያደረገውን ወንጌል ስታበሥር ኖራለች፤ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን (1ቆሮ 1፡23( እያለች፡፡ የመንግስቱ ወንጌል ቤዝዎታዊ እውነቱ የሚታየው በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ በኩል ነው ነውና፡፡ ያልተዋጁ ንጉሡንም ኾነ መንግስቱን አያዩትም፡፡ ቤተክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ውጭ በኾነ ትምህርትና ኑሮ የመስቀሉን መልዕክት አዛብታ የተገኘችበት ወቅትም ነበረ፤ ዛሬም አለ፡፡ …… መስቀሉን ማእከል ካደረገው ወንጌል ይልቅ ቅምጥልነተን የሚያስፋፋውን ‹‹ዘመነኛውን ወንጌል›› ማስበለጣችንን›› ጋሽ ሰለሞን አበበ ገ/መድኅን ‹‹የደነበረው በቅሎ በተሰኘው መፅሃፋቸው ላይ አንስተዋል፡፡
እንደእውነቱ ከሆነ ‹‹ያለመስቀሉ ክርስትናን ማሰብ መሞከር አይታሰብም››፡፡ ዛሬ ዛሬ ላይ መስቀሉን ገሸሽ ያደረጉ ስብከቶች ወይም ትምህርቶች ላይ ብዙ ትኩረት ቢደረግም ዝማሬዎቻችንም ከዚህ በሽታ መላቀቅ አልቻሉም፡፡ የዛሬዋ ቤተክርስቲያን ትልቅዋ ችግርም ከክርስቶስ መስቀል ገለል ማለትዋ እና ለውጫዊው ገፅታዋ ትኩረት መስጠትዋ ነው፡፡
መስቀሉን ማእከል ያደረጉ ዝማሬዎች አይደመጡም መድረኮቻችን ላይም እምብዛም አይዘመሩም ከዛ ይልቅ ‹‹አቧራ የሚያስነሱ›› ዝማሬዎች መድረኩን ያጨናንቁታል፡፡ መንፈስ አልባ ዝማሬዎች እየገነኑ የዝማሬ አምልኮኣችን አቧራ ጨሰ ሆኗል፡፡ እግዚአብሔር የሌለበትን አምልኮ ለምደነዋል ክፋቱ ደሞ እግዚአብሔር እንዳለ ማሰባችን ነው፡፡ በአቧራ ውስጥ እግዚአብሔር የለም፡፡ ስሜትን በማሞቅ ውስጥ መንፈሱ የለም፡፡
በዕንባ የሚደመጡ ዝማሬዎች ነፍስን የሚያክሙ፤ ሸካራና ድንጋያማ ልብን የሚያለሰልሱ ዝማሬዎችን ሰምቶ ላገ ሰው ዛሬ ዛሬ ላይ ‹‹ላብን እንድናወጣ›› ታስበው ብቻ የሚዘመሩ ዝማሬዎችን መስማት ህመምን ይፈጥርበታል፡፡
‹‹አስይዘኝ መስቀሉን - ሁሌም አሳዝለኝ
ከመፋነን ግሳት - ሞቴ እንዲቀልልኝ፡፡››
የሚል ዝማሬ ይጨንቀናል፤ አናደምጠውም ከእንዲህ አይነት ዝማሬ ይልቅ ትከሻን ነቅነቅ የሚያደርግ ስሜትን የሚያነቃቃ ዝማሬ እንፈልጋለን፡፡ ክቡሩ በሌለበት አምልኮ ለምደናል ዘማሪው ለማስጨፈር አስቦ ስለሆነ መድረክ ላይ የሚወጣው የእግዚአብሔርን መገኘት በአብዞኛው መድረክ ላይ አናየውም፡፡ የመጨፈር ጥም እንጂ እግዚአብሔርን በዝማሬ የማምለክ ናፍቆት ተወስዶብናል፡፡ አንድ የሚያሳዝን እውነት አለ አብዛኛውን መድረክ ያጨናነቁ ዘማሪዎች ገበያ ተኮር የሆኑቱ ናቸው በጠጠሩበት ሁሉ የሚገኑ በተጠሩበት ሁሉ የማይታጡ ድምፅ እንጂ መቀላለፅ እንጂ ማድመቅ እንጂ ነፍስን የሚደርስ ዝማሬ የሌላቸው አዎ እነርሱ ናቸው ያጨናነቁን፡፡ አንዳንድ ቦታ የምንሰጣቸው በዝማሬ አገልግሎታቸው በብዙ የባረኩን ዘማሪዎችም የዚህ ሰለባ ሆነው ስናገኛቸው እናዝናለን፡፡
አዎን ዛሬም በዚህ ዘመን ዝማሬያቸው የክርስቶስን መስቀል፤ የእግዚአብሔርን ቃል ማዕከል ያደረጉ የሉም ማለት አይደለም ስለነርሱ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ ነገር ግን ዛሬ ዛሬ ላይ በቤተክርስቲያን የዝማሬ አገልግሎት ክቡርነቱን እያጣ መጥቶ የፕሮግራም ማዳመቂያ መሆኑን ማነገር ደግሞ ያስፈልጋል፡፡ … ሕይወት የሌለው ነፍስን የማይደርስ ልብን የማይፈውስ ለጭፈራ ብቻ የሚውሉ ዝማሬዎች በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ አይለዋል፡፡ ‹‹መደነስ ካልቻልክ ከፊቴ ዞርበልልኝ …. ፕሮፌቲክ ዳንስ ደንስልኝ እየተባለ የዝማሬ አገልግሎት ከማስጨፈር ከመደነስ ጋር አያይዘውታል፡፡ የዘማሪ ትልቁ ኳሊቲ ማስጨፈር እስኪመስል ድረስ ነገሮች እየተዘበራረቁ መጥተዋል አኹን ግን በቃ ልንል ይገባል፡፡ በዝማሬ የብዙዎቻችን ሕይወት ተለውጧል ብዙዎቻችን ተገርተናል በንስሃ ፍሬ ከአምላካችን ጋር ታርቀናል ተፅናንተናል ፀንተንበታል አምላካችንን አወድሰንበታል ከፍ አድርገንበታል፡፡ አዎን ሳንጨፍር ላብ ሳይወጣን እግዚአብሔርን ከፍ አድርገንበታል፡፡ እናም አንዳንድ ሳይኾን ብዙ ዘማሪዎቻችን እረፉ ወይም ጎራችሁን ለዩ ዝማሬን አታርክሱት ዝማሬን አታኮስሱት፡፡ የዝማሬን አገልግሎት የፕሮግራም ማዳመቂያ ለማድረግ የምትጥሩ ሁላችሁም ከዚህ መንገዳችሁ ተቆጠቡ ዘማሪዎቻችን ሆይ በሰው ልብ ላይ የሚውል ዝማሬ ዘምሩ ገባያ ተኮር ብቻ ሆናችሁ ኢየሱስ የሚል ቃል ብቻ እያስገባችሁ ቀሽም ዝማሬን አትዘምሩ የዝማሬ ፀጋ ማለት የድምፅ መኖር ማለት አይደለም ድምፅ ስላላችሁ ብቻ ለመዘመር አትውጡ የዝማሬ አገልግሎትን አክብሩ፡፡ ለማስጨፈር ከሆነ ዓላማችሁ ማይኩን ልቀቁና ውረዱ ወደ እልፍኛችሁ ግቡ እግዚአብሔር የራሳችሁን ዝማሬ/መልዕክት እንዲሰጣችሁ ተማፀኑ በብዙ እንባ በብዙ ፀሎት የተወለዱ ዝማሬዎች አታበላሹ፡፡
እኛም በቤተክርስቲያን ያለን ወጣቶች አባቶች እናቶች ሴቶች ወንዶች ሆይ በቤተክርስቲያን ከሚታየው የክርስቶስን መስቀል ካስወገደው ከሰው ልማድ አንፃር ተከፍተን ከቤተክርስቲያን ከመሸሸ ይልቅ የሁሉ መመዘኛ የሆነውን ቃሉን አንስተን በርሱ ላይ በመቆምና በመታነፅ በየቤተክርስቲያናችን የሚታዩ ኢ መፅሃፍቅዱሳዊ ትምህርቶችን ሆነ ዝማሬዎችን ልንሞግት ይገባል፡፡
በየአጥቢያችን የሚገኙ መሪዎችንን እረኞችን እየሞገትን ምመኑን ፉርሽካና ገለባ ከመመገብ መግታት አለብን፡፡ ወደ ቤቱ የምንመጣው ክርስቶስን ለማየት እንጂ የሰዎችን ችሎታ አይተን ለመሄድ አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል በራቁ ከመስቀል በጎደሉ ዝማሬዎችና ትምህርቶች ምክንያት የቤተክርስቲያን መልክ መደብዘዝ አቅምዋ መልፈስፈስ የለበትም፡፡ ተሃድሶ ያስፈልገናል ፤ ተሃድሶውን ከአጥቢያችን እንጀምር፡፡
(((‹‹መስቀሉን ወደ ዳር/ጠርዝ ገፍተን ማዕከሉን ለማን ልንሰጠው ነው? ደግሞም ከዘመናችን ስብከቶች ፣ ትምህርቶችና ዝማሬዎች ውስጥ የመስቀሉን ምልክት ምን ሰወረው? የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢ ነው፤ ልንነጋገርበትም ልንቆጭበትም የተገባ ይመስለኛል፡፡ የደነበረው በቅሎ 95››))) እንዳሉት ነውና ልንቆጭ ልንነጋገር የሚገባበት ጊዜ ነው፡፡
አዎን ‹‹የደነበሩ በቅሎዎች›› በየቦታው አሉና ‹‹የአስተምህሮ ልጓም ያስፈልጋቸዋል›› …የዝማሬ አገልግሎት ወደ ክብሩ መመለስ አለበት እስከመቼ የድሮ ዝማሬዎች እያልን እንቆጫለን? ለምን በእኛ ዘመንስ መስቀሉን ክርስቶስን ማዕከል ያደረጉ ዝማሬዎች አይበዙልንም?! ከእኛው እንጀምር መድረኮቻችንን በማጥራት እንጀምር፡፡
‹‹ትውልድ ሆይ ወደ እግዚአብሔር ቃልና ወደ ክርስቶስ መስቀል ተመልከቱ›› ይህ እውነት ለዝማሬ አገልግሎትም ይሰራል፡፡
887 views17:51