Get Mystery Box with random crypto!

ወጣቶችን አጋቡ ============= ወላጆች በልጆቻችሁ ጉዳይ አላህ ፊት ትጠየቃላችሁ። እነር | ሰላም አለይክ TUBE

ወጣቶችን አጋቡ
=============
ወላጆች በልጆቻችሁ ጉዳይ አላህ ፊት ትጠየቃላችሁ። እነርሱ የናንተ ሐቅ እንዳለባቸው ሁሉ፤ እናንተም የነርሱ ሐቅ እንዳለባችሁ አትዘንጉ። ከሐቆቃቸው መካከል አንዱ በጊዜ መሰተር ነው። በተለይ ሴት ልጆች ያሏችሁ፣ በተለይ ኒቃብ ለባሽ ከሆኑ፤ ወላጆች ለነዚህ ልጆቻችሁ ሷሊሕ የትዳር አጋር በጊዜ አፈላልጋችሁ መዳር አለባችሁ።

ከወላጆች በተጨማሪ ትልቅ ወንድም፣ ትንሽ ወንድም፣ ያገባችሁ እህትና ወንድሞች ለታናናሾቻችሁ ጥንዳቸውን መፈለግ አለባችሁ። አባት ባይኖር ኖሮ ወልይ ሆነህ የምትድራት'ኮ አንተ ነህ። እንዳትነግርህ ሐያእ አድርጋ ፈራችህ። እና ራሷ ፈልጋ ታምጣ? ምን እያሰብክ ነው ብሮ? በቃ የራስህን ካገባህ ለሌላው አታስብም? ከወላጆቿና ካንተ ውጭ ይህቺን ልጅ የመዳር ቅድሚያ ኃላፊነት ያለበት ማነው? በዙሪያህ ብዙ ጓደኞች አሉህ። በነርሱ ዙሪያ ብዙ ጓደኛ አላቸው። ይሄን ሰንሰለት ተጠቅመህ ለእህትህ አንድ ሷሊሕ ወንድ አጥተህ ነው?


እናትና አባት ሆይ! ሌላው ቢቀር በእናንተ የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎችን ታውቃላችሁ። አንዳቸው ለትዳር የደረሰ ልጅ ካለውና የሚመጣጠኑ፣ መስፈርቱን የሚያሟሉ ከሆነ በግልፅ «ልጅህን ለልጄ!» ማለት ምን ያሳፍራል? የሚያሳፍረውስ በዝሙት ድቃላ አርግዛ አስወረደች ሲባል ወይም ወለደች ሲባል! ፈልጎ ከመዳር ይልቅ ያ ተሻላችሁ እንደ? ነገሮች ከመከሰታቸው በፊት ለምን በአላህ ላይ ተመክታችሁ ሰዋዊ ሰበቦችን አታደርሱም?


ዘመኑ የፊትና ዘመን ነው። የፊትና አቅርቦት በ4ቱም አቅጣጫ የተሟላ ነው። ከቤታችን ሳንወጣ ቁጭ ባልንበት ሁሉ የፊትና አቅርቦት በሽ ነው። አንዳንዱ ፊትና ሲባል የግድ የተሟላውን ዝሙት መፈጸም ብቻ ይመስለዋል። እንደዛ አይደለም ነገሩ። ምላስ ዝሙት ይሠራል፣ እግር ዝሙት ይሠራል፣ እጅ ዝሙት ይሠራል፣ ዓይን ዝሙት ይሠራል፣ ጆሮ ዝሙት ይሠራል። እነዚህ የሰውነት ክፍሎቻችን በተናጠል የሚፈጽሙት ዝሙት ከተደጋገመና ድካውን ካለፈ፤ አንድ ቀን ሁላቸውም በጥምረት የሚፈጽሙት ኦርጂናሉ ዝሙት ይሠራል። ያ እስከሚሆን ነው የምትጠብቁት? አላህን አትፈሩትም?


ልጆቻችሁ ቢከበሩና በጊዜ ተሰትረው ለወግ ማዕረግ ቢበቁ፤ የምትከበሩት እናንተ ናችሁ። አላስፈላጊ ሙድ ውስጥ ገብተው ለብዙ ነገር ይበቃሉ ተብለው በጉጉት ሲጠበቁ የነበሩት ልጆች በዚህ ጉዳይ ተጨናግፈው መክነው ሲቀሩ ውርደቱ ለናንተም ነው። «የእገሌ ልጅ፣ የእግሌ እህት፣ የእገሌ ወንድም…» መባል አለ'ኮ! ታዲያ ምን ትጠብቃላችሁ? እነርሱ አፍ ወጥተው እንዳይነግሯችሁ አፈሩ። እንዳይተዋችሁ ያው ዝምም ሆነ። ጭራሽ ምንም አያሳስቧችሁ። ሐቂቃ አስቡበት!


በተጨማሪም ለገንዘብ ብላችሁ አታጋቡ። አዎ! ዛሬ ላይ ተመርቀሽ ሥራ ስታጪ፣ ዳግም ቤተሰብ ጋ መሆን ሲደብርሽ፣ ጓደኞችሽ ሥራ ይዘውም አግብተው ወልደውም ስትመለከቺ ሊከፋሽ ይችላል። ግን በዚያ ተነሳስተሽ አንድን ሰው ዱንያ ስላየሽበት ብቻ ዘው ብለሽ እሺ ብለሽ አታግቢ። ዱንያ ትሄዳለች፣ ትመጣለች። ለርሷ ብለሽ ዘላቂ መስፈርቶችሽ ላይ ከተንሸራተትሽ፤ ከጊዜ በኋላ ክፍተቶች ጎልተው ይታይሹና እስከ መፋታት ሊደረስ ስለሚችል አስቢበት።


በተረፈ ግን ወላጅ፣ ወንድምና እህት ወዘተ የሌለው ሰው ጓደኛንና መሰል አማራጮችን ይጠቀም። እንዲህ አይነት አማራጮች ከሌሏችሁ ግን፤ መልካም ሰው ብላችሁ ለምታስቡት/ቧት ሸሪዓውን ባማከለ መልኩ ቀጥታ መጠየቅ ትችላላችሁ። ግን በተለይ ሴት ከሆንሽ ከመጠየቅሽ በፊት ስለምትጠይቂው ሰው በቂ መረጃ ይኑርሽ።

የአሁን ጊዜ ሰው ስትጠይቁት ይኮራል፣ ይንቃችኋል። ምናልባትም'ኮ ሌላ ወንድ እንኳን ጠይቀሽው በየት በኩል በጠየቅኳት/ባስጠየቅኳት እያለ ጠብ እርግፍ እያለልሽ ይሆናል። ይሄኛው ግን ቀጥታ ስለጠየቅሽው ብቻ፣ ሳይወጣ ሳይወርድ ስላገኘሽ ብቻ፣ ይንቅሻል። እንዲህ አይነቱ ወንድ ቀድሞውኑም ብስለት ይጎድለዋልና ሞራልሽን እንዳይጎዳው ተቆጠቢ።


ዋናው ቁልፍ ነገር ዱዓእ ነው። ጉዳይን ወደ አላህ ማስጠጋት። ከናንተ የሚጠበቀው ሰበብ ማድረስ ብቻ! ውር ውር ስላላችሁ የሚፈጠር ነገር የለም። ቢፈጠርም አያዋጣም።



አላህ ሸባቦቻችንን ከሐራም ነገር ቆጥቦ በሐላሉ ያብቃቃልን።