Get Mystery Box with random crypto!

የመከራውን ጎርፍ በትእግስት ጀልባ እናቋርጠው! ~ ~ ~ ~ ~ ~ ~~~~ ~ ~ ~ ፈተና የአላህ | የምስራቅ እስቴ ወረዳ ሰለፍዮች ቻናል።

የመከራውን ጎርፍ በትእግስት ጀልባ እናቋርጠው!
~ ~ ~ ~ ~ ~ ~~~~ ~ ~ ~
ፈተና የአላህ ሱና ነው። መልኩ ቢለያይም ደረጃው ቢፈራረቅም ማንም የማያመልጥበት የሆነ ወጥመድ። ጌታችን አላህ "ሰዎች አመንን ስላሉ ብቻ ሳይፈተኑ ሊተው ያስባሉን?" ሲል እስትንፋሳችን ዱንያን እስከምትሰናበት ድረስ ከፈተና እንደማናመልጥ እቅጫችንን ነግሮናል። ኧረ እንዲያውም “ከፍርሃትና ከረሃብም በሆነ ነገር፤ ከገንዘቦች፣ ከነፍሶችና ከፍሬዎች በመቀነስም በእርግጥም እንፈትናችኋለን” ሲል አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ታዲያ ብልጦቹ ይታገሳሉ፡፡ ሽልማታቸውንም ያፍሳሉ፡፡ ቂሎቹ ደግሞ ይወራጫሉ፣ ምንም ጠብ ላያደርጉ የትእግስትን እድል በማሳለፍ ከሁለት ያጣ ይሆናሉ፡፡
በርግጥ የዋሆች ባያስተውሉትም ፈተና ማለት ቅስማችንን የሚሰብረን ነገር ብቻ አይደለም፡፡ ፈተና ስቃይ እንግልቱ፣ መከራው መአቱ ብቻ ሳይሆን ድሎት ምቾቱም፣ ሁሉም የአላህ ፈተና ነው። ታዲያስ "ከዚያም ከ(ተዋለላችሁ) ፀጋዎች ሁሉ በርግጥም ትጠየቃላችሁ" ማለቱ ምንድን ነው የሚያመላክተን? እንዲያውም ነብዩ ﷺ ከማጣት ይልቅ የማገኘትን ፈተና ሰግተውልናል። ጌታችን በክፉ ከተፈተነው ትእግስትን፤ በበጎ ከተፈተነው ምስጋናን ይጠብቃል። የኛ ነገር ግን ሲበዛ ግራ ነው። ብናገኝ ጥጋባችን መከራ። ብናጣ ምሬታችን ፈተና። ቢደላን ምስጋናውን አናውቅበት፡፡ ቢከፋን ትእግስቱን አንችልበት።
በህይወታችን ላይ የሚያጋጥመን እያንዳንዱ ነገር ቢከፋም ቢለማም ሁሉም ከአላህ ነው። ይሄ ከስድስቱ የኢማን ምሰሶዎች የአንዱ መሰረታዊ መልእክት ነው፣ ቀደር። በቀደር ማመን በመርህ ደረጃ ከማስተጋባት ባለፈ በተጨባጭ በህይወታችን ላይ ልናስገኘው የሚገባ አንኳር የሙእሚን መለያ ነው። በቀደር ማመን አማኞችን ጀግና ያደርጋል። "አላህ ከወሰነው ውጭ ምንም አይደርስብኝም" ብሎ የቂን ብሎ የሚያምን አካል የፍጡራን ሴራ አያሸብረውም። ሞራሉንም አይሰብረውም፡፡ የዘወትር መፈክሩ "አላህ ለኛ የፃፈብን እንጂ ፈፅሞ አያገኘንም" የሚለው መለኮታዊ ቃል ነው። በቀደር ስታምን ሰው ጂኑ ከጥንት እስከ ዛሬ ባንድ አብረው ቢዘምቱ አላህ ከፃፈብህ ውጭ ቅንጣት ታክል ምንም እንደማያደርሱብህ ስለምታምን በፍጡር አትሸበርም፣ ከፍጡር አትከጅልም። በቀደር ስታምን አንዴ በተከሰተ ነገር በከንቱ አትብከነከንም፣ በባዶ አትቆዝምም። የሆነውን ላትቀይር ነገር "እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ" እያልክ የቂል ፀፀት ውስጥ አትገባም። ለምን ቢባል "ቢሆን ኖሮ" ነብዩ ﷺ እንዳሉት “የሸይጧንን ስራ ትከፍታለችና፡፡” አላህ አለምን ከመፍጠሩ ከሃምሳ ሺ አመት በፊት የወሰነውን ውሳኔ በቢሆን ኖሮ አትቀይረውምና ለአላህ እጅ ስጥ። “አላህ ቀደረው፣ የሻውንም ፈፀመ” በል። የሙእሚን መታወቂያው ይሄው ነው፡፡ “የሙእሚን ነገሩ አስገራሚ ነው፡፡ ነገሩ ሁሉ ለሱ መልካም ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለአማኝ እንጂ ለማንም አይደለም፡፡ (ሙእሚን) አስደሳች ነገር ቢያገኘው ያመሰግናል ይህ ለሱ መልካም ነገር ነው፡፡ ጎጂ ነገርም ቢያገኘው ይታገሳል ይህም ለሱ መልካም ነገር ነው” ይላሉ ውዱ ﷺ፡፡ [ሙስሊም]
ነብዩ ﷺ የሚወዱትን ነገር ሲመለከቱ "ምስጋና ለአላህ ይሁን በፀጋው በጎ ነገሮች ይፈፀማሉ" ሲሉ "የሚጠሉትን ሲመለከቱ ደግሞ "በማንኛውም ሁኔታ ምስጋና ለአላህ ይሁን" ይሉ ነበር። እኛ ግን በሚደርሱብን ነገሮች ከትእግስት ይልቅ ብስጭትን፣ ተስፋ መቁረጥን፣ ቀንን መራገምን ምርጫችን የምናደርገው ቀላል አይደለንም፡፡ በሚደንቅ ሁኔታ አላህን እስከማማረር አልፎም እስከመሳደብ የሚደርሱም አሉ፡፡ ሱብሓነላህ! ወንድሜ ሆይ! እህቴ ሆይ! እስኪ የነብዩን ﷺ ታሪክ እናስታውስ። ገና በናታቸው መሀፀን ሳሉ አባታቸውን አጡ። ይቺን ምድር ሲቀላቀሉ አባት አልባ የቲም ነበሩ። ገና የልጅነት ጊዜያቸውን ቦርቀው ሳይጨርሱ እናታቸውን አጡ። እዚህ ላይ ወላጅ አልባውን ሙሐመድን ﷺ አስቡ። አስር አመት እንኳ ሳይሞላቸው አሳዳጊ አያታቸውን አጡ። ትዳር ይዘው ሲኖሩ የጠላት ፈተና እጅጉን በከበደበት ጊዜ መከታ የሆነላቸው አጎታቸው አቡ ጧሊብን እና ብርታት የሆነቻቸውን ውድ ባለቤታቸው ኸዲጃን በሞት አጡ። ከሰባት ልጆቻቸው ውስጥ ስድስቱ እሳቸው በህይወት እያሉ ነው የሞቱባቸው። ምን ያክል የሀዘን መከራ እንደተፈራረቀባቸው ተመልከቱ። ከሶሐቦቻቸውም ውስጥ እነ ሐምዛን፣ ሙስዐብን፣ ጀዕፈርን፣ ዐብደላህ ብኑ ረዋሐን፣ ሰዕድ ብኑ ሙዓዝን፣ ... በስንቱ ሃዘን ተጎድተዋል? እስቲ ለአፍታ መካ ላይ፣ ጧኢፍ ላይ በሙሽሪኮች የደረሰባቸውን አስቡ። ለመቋቋም በሚከብድ ሁኔታ ክብራቸው ተጠልሽቷል። አካላቸው ተደብድቧል። የሸተተ እንግዴ ልጅ ላያቸው ላይ ተጥሎባቸዋል። ድፍን ሃገር አድሞ ከነቤተሰባቸው በረሃብ አለንጋ ተገርፈዋል። ለስደት ሲወጡ የታወጀባቸውን ዘመቻ አስታውሱ። መዲና ላይ በሙናፊቆችና በየሁዶች፣ የኡሑድ ዘመቻ ላይ ጥርሳቸው መሰበሩን፣ እራሳቸው መድማቱን እናስታውስ እስኪ፡፡ አለም ከተፈጠረች ጀምሮ ካለፉ ፍጡሮች ሁሉ የምርጦች ሁሉ ምርጥ፣ የታላቆች ሁሉ ታላቅ ከመሆናቸው ጋር፣ ከአላህ ዘንድ ከየትኛውም ፍጡር በተለየና በበለጠ የተወደዱ ከመሆናቸው ጋር ነገር ግን ይህን ሁሉ መከራ አስተናግደዋል። ደረጃችንን ከደረጃቸው ፈተናችንን ከፈተናቸው ጋር እናነፃፀር እስቲ! እዚህ ግባ የሚባል ደረጃ አለን? ከዚህ ሁሉ ፈተና አንፃር የኛ ፈተና ምን አለው ወገኖቼ?
ወገኔ ሆይ! ምንም ቢደርስ ታገስ! እርግጠኛ ሁን በትእግስት ምንም የምታጣው ነገር የለም፡፡ እንዲያውም ትእግስቱን ከቻልክበት ካሰብከው ትደርሳለህ፡፡ ያለምከውን ታሳካለህ፡፡ ድል ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ታገስ፡፡ “እወቅ ድል ከትእግስት ጋር ነው” ብለውሃል ነብዩ ﷺ፡፡ እርዳታ ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ታገስና ወደ ጌታህ ተመለስ፡፡
(وَٱسۡتَعِینُوا۟ بِٱلصَّبۡرِ وَٱلصَّلَوٰةِۚ)
“በትእግስትና በሶላት ታገዙ” እያለ ነው ጌታህ፡፡ [አልበቀራህ፡ 45]
ካለህበት ጭንቅ መውጣት ትፈልጋለህ? እንግዲያውስ ታገስ፡፡ ይበልጥ በተጨነቅክ ቁጥር ይበልጥ ፍጡርን እየተወክ ይበልጥ በጌታህ ላይ ተስፋህን እየጣልክ ትመጣለህ፡፡ ያኔ እፎይታን ታገኛለህ፡፡ “እፎይታ ወይም ግልግል ከጭንቅ ጋር ነው” ይላሉ መልእክተኛው ﷺ፡፡ ታገስ! በትእግስት የጠላት ውስብስብ ሴራዎች ይበጣጠሳሉ፡፡ ታገስ! በትእግስት እብሪተኛ አንባገነኖች ይፈራርሳሉ፡፡ ታገስ! በትእግስት ደካሞች ድሎትን ይጎናፀፋሉ፡፡ ወገኔ ሆይ እወቅ! በፈተና እኛ የመጀመሪያዎች አይደለንም፡፡ ቀደምቶች በዲናቸው ሳቢያ በመጋዝ ለሁለት ተሰንጥቀዋል፡፡ ቀደምቶች በዲናቸው ሳቢያ አይናቸው እያየ ከሚንቀለቀል እሳት ውስጥ ተማግደዋል፡፡ ቀደምቶች በዲናቸው ሳቢያ ከፈላ ዘይት ውስጥ ተነክረዋል፡፡ ቀደምቶች ነፍሳቸው እያለ በስለት ተዘልዝለዋል፣ ተመትረዋል፡፡ ቆስለዋል ደምተዋል፡፡ ይሄ ወደፊትም የማይቋረጥ የጌታችን ሱና ነው፡፡ ጌታችን አላህ እንዲህ ይላል፡-
(لَتُبۡلَوُنَّ فِیۤ أَمۡوَ ٰ⁠لِكُمۡ وَأَنفُسِكُمۡ وَلَتَسۡمَعُنَّ مِنَ ٱلَّذِینَ أُوتُوا۟ ٱلۡكِتَـٰبَ مِن قَبۡلِكُمۡ وَمِنَ ٱلَّذِینَ أَشۡرَكُوۤا۟ أَذࣰى كَثِیرࣰاۚ)