Get Mystery Box with random crypto!

#በዓለ_ሆሣዕና ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው። አንድም ሆሣዕና ማለት አሁን አድን ማለት ነው | 7 ቁጥር

#በዓለ_ሆሣዕና

ሆሣዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው። አንድም ሆሣዕና ማለት አሁን አድን ማለት ነው። በዳዊት መዝሙር ቃሉ ተጠቅሷል "ኦ እግዞኦ አድህንሶ አቤቱ አሁን አድን (መዝሙር 117÷25) በአርያም የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነውን ሰማይ ያመለክታል።

የመጀመሪያው ከሮማውያን ቀኝ አገዛዝ አድነን የሚል የሥጋ ጩኸት ሲሆን ምስጢሩ ግን ከሞተ ሥጋ እና ከሞተ ነፍስ አድነን ማለታቸው ነበር።

ይህ በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቶ በመቅደሱ ዙሪያ ያሉትን ለዋጮችንና ሻጮችን ያስወጣበት፤
ቤተ መቅደሱ የጸሎት ቤት መሆኑን ያወጀበትና ክብሩን የገለጸበት በዓል ነው። ከዘጠኙ ዐበይት በዓላትም አንዱ ነው።

በዚህ ዕለት የእስራኤል ሕዝብ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ ሆሣዕና በማለት እየጮኹ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አጅበውታል። ትንቢቱም ይፈፀም ዘንድ ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል ተብሎ እንደተፀፈ (ዘፍጥረት 49 ዘካርያስ 11 9÷9 ኢሳይያስ 40÷20) ማለት ነው።

ቀደምት ነቢያት ዘመነ መዓት መምጣቱን ለማሰታወስ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው በከተማ ሲዘዋወሩ ዘመነ ሣህል (ዘመነ ምሕረት) መምጣቱን ለማሳየት ደግሞ በአህያ ላይ ተቀምጠው ይታዩ ነበር። ይህ ምሥጢርም በቅዱሳት መጻሕፍት በልዩ ልዩ መንገድ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በማቴዎስ ፳፩፥፩-፲፩፤ በማርቆስ ፲፩፥፩-፲፤ በሉቃስ ፲፱፥፳፰-፵ እና በዮሐንስ ፲፪፥፲፪-፲፭ በተጻፈው ኃይለ ቃል መሠረት መመልከት ይገባል።

ያን ጊዜ ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ላከና "በፊታችሁ ወደ አለ ሀገር ሂዱ አህያዋን ከውርንጭላዋ ጋር ታስራ ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ" አላቸው። (ሉቃስ ፲፰÷28)

ሰው ሁሉ ከማዕሠረ ኃጢአት ለመፈታተ እንደ ደረሰ ለማጠየቅ ነው። የሐዋርያት አገልግሎት የታሰሩትን በወንጌል ቃል መፍታት ነው። ሌቦች አጋንንት ያሠሯቸው ብዙ የኃጢአት እስረኞች አሉ። ጌታ የታሰሩትን እንደ እሱ እንዲፈቱ ደቀ መዛሙርቱን አዟቸዋል።

አህያ የተናቀች ናት ራሳቸውን ዝቅ ባደረጉ መንፈሳቸው ወደ ተሰበረ አምላክ እንደሚመለከት ያስተምራል (ኢሳይያስ 53÷23 ማቴዎስ 11÷29) አንተም የማትቆረቁር ሕገ ወንጌል ሰጠህን ሲሉ ልብሳቸውን ጎዝጉዘው ተቀብለውታል። "እም አፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሐት በእንተ ጸላዒ።,ከመ ትንስቶ ለጸላዒ ወለገፋዒ" (መዝሙር ፰÷፪)
ባለ አእምሮ ነን የሚሉት ልብ ሲታወር አንደበታቸው በሰይጣን ምክር ሲዘጋ የሕፃናት አንደበት ምስጋናን ያዘንብ ነበር።

ቤተ ፋጌ ማለት ደግሞ "የበለስ ቤት" ማለት ነው። በእኛ አባቶች ደግሞ "የተመሳቀለ ጎዳና" ተብሎ ተተርጉሟል። ጌታችን ከደብረ ዘይት ተራራ አካባቢ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አዕሩግና ሕፃናት ልብሳቸውን እንዲሁም የዘንባባ ዝንጣፊ በማንጠፍ "ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው" እያሉ ክብሩንና መድኃኒትነቱን ገልጠዋል (ሉቃስ 19÷38 መዝሙር ፰÷፪)።

በዚህም ዕለት ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝብ ይታደላል።