Get Mystery Box with random crypto!

ንጉሡም ዳግመኛ ቅዱስ ጊዮርጊስን ‹‹በመንግሥቴ ልሹምህ ለአጵሎን ስገድ›› ቢለው ቅዱስ ጊዮርጊስም | ቤተ ቅዱስ ሚካኤል

ንጉሡም ዳግመኛ ቅዱስ ጊዮርጊስን ‹‹በመንግሥቴ ልሹምህ ለአጵሎን ስገድ›› ቢለው ቅዱስ ጊዮርጊስም ሊያሾፍበት በማሰብ ‹‹እሺ›› ብሎ ወደ ንጉሡ ቤተ መንግሥት ገብቶ የንጉሱን ሚስት ንግሥቲቱን እለእስክንድርያን አስተምሮ አሳምኗታል፡፡ በነጋም ጊዜ ንጉሡ በአዋጅ ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ ‹‹ጊዮርጊስ ለጣዖቴ ሊሰግድ ነውና ኑ ተመልከቱ›› ብሎ ተናገረ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም በተሰበሰበው ሕዝብ መካከል አንድን ብላቴና ጠርቶ ‹‹የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ጊዮርጊስ ይጠራሃል ብለህ ለጣዖቱ ንገረው›› ብሎ ላከው፡፡ ብላቴናውም ወደ ጣዖት ቤቱ ገብቶ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዳለው ተናገረ፡፡ በዚህም ጊዜ በጣዖቱ ላይ ያደረው ሰይጣን እየጮኸ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለበት ቦታ ድረስ መጣ፡፡ በንጉሡና በሕዝቡም ሁሉ ፊት አምላክ አለመሆኑን ይልቁንም አሳች ሰይጣን መሆኑን በመናዘዝ ከተናገረ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሬት ተከፍታ እንድትውጠው አደረገው፡፡

ይህንንም ተዓምር ያዩ ሁሉ ብዙዎች ‹‹በጊዮርጊስ አምላክ አምነናል›› እያሉ በጌታችን አመኑ፡፡ የንጉሡም ሚስት እለእስክንድርያ በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ካመነች በኋላ ባሏን ከክፋቱ ተመልሶ እንዲያምን ብትለምነውና ብትመክረውም አልሰማት አለ፡፡ ይልቁንም ንጉሡ በአደባባይ በሕዝቡ ሁሉ ፊት የገዛ ሚስቱን አሠቃይቶ ሰውነቷን ቆራርጦ ሰቅሎ አንገቷን በመሰየፍ ሰማዕትነት እንድትቀበል አደረጋት፡፡ ቅድስት እለእስክንድርያም ቅዱስ ጊዮርጊስን ‹‹ሳልጠመቅ አልሙት›› ስትለው እርሱም ‹‹ደምሽ ጥምቀት ሆኖልሻልና እነሆ የክብር አክሊል እየጠበቀሽ ስለሆነ አይዞሽ›› ብሎ አጽንቷታል፡፡ በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ታላቅ ቃልኪዳን ከተቀበለ በኋላ በ27 ዓመቱ በሚያዝያ 23 ቀን ሰማዕትነቱን በድል ፈጽሞ የክብር አክሊልን ተቀዳጀ፡፡ አንገቱም ሲቆረጥ ውሃ፣ ደምና ወተት ወጥቷል፡፡ ከሥጋውም እጅግ ብዙ አስገራሚ ተአምራት ተፈጽመው ታይተዋል፡፡ የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!!
(ምንጭ፡- ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ስንክሳር ዘወርሃ ሚያዝያ)
https://t.me/saint_mikael