Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ❀ ሚያዝያ ፳፯ ❀ ✞✞ | ቤተ ቅዱስ ሚካኤል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡

❀ ሚያዝያ ፳፯ ❀

✞✞✞ እንኩዋን ለታላቁ ሰማዕት "ቅዱስ ፊቅጦር" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

+*"+ ማር ፊቅጦር +"*+

=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደማቸውና በገድላቸው ያስጌጡ ብዙ ሰማዕታት አሉ:: ነገር ግን ከኮከብም ኮከብ ይበልጣልና ማን እንደ ጊዮርጊስና እስጢፋኖስ!

+ከእነርሱ ቀጥለው ከሚጠሩ ሰማዕታት ደግሞ አንዱና ዋነኛው ቤተ ክርስቲያን "ማር" የምትለው ቅዱስ ፊቅጦር ነው:: እስኪ ከበዛው መዓዛ-ገድሉ ጥቂት እንካፈል::

=>ቅዱስ ፊቅጦር አባቱ ኅርማኖስ ይባላል:: አረማዊና ጨካኝ ነው:: እናቱ ግን የተመሰገች ቅድስት ማርታ ትባላለች:: ልጇን እንደሚገባ አሳድጋው 20 ዓመት ሲሞላው የአንጾኪያ ንጉሥ የሠራዊት አለቃና በመንግሥቱ 3ኛ አድርጐ ሾመው::

+የድሮዋ አንጾኪያ (ሮም) እንደ ዛሬዋ አሜሪካ ዓለምን የተቆጣጠረች ሃገር ነበረች:: ቅዱስ ፊቅጦር ደም ግባቱ ያማረ: በጦርነትም ኃይለኛ ስለ ነበር ሁሉ ያከብሩት: ይወዱትም ነበር:: እርሱ ግን ቀን ቀን ሲጾም: ነዳያንን ሲያበላ ይውል ነበር::

+ሌሊት ደግሞ እኩሉን ሲጸልይና ሲሰግድ: እኩሉን የእስረኞችን እግር ሲያጥብ ያድር ነበር:: ይህ ሁሉ ሲሆንኮ እርሱ የንጉሡ 3ኛ: የሠራዊትም አለቃ ነው:: በዘመኑ የሚያገድፍ ምግብና የወይን ጠጅ በአፉ ዙሮ አያውቅም::

+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ካደ:: ዘመነ ሰማዕታትም ጀመረ:: አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ:: ከ47 ሚሊየን በላይ ክርስቲያኖች በመንኮራኩር ተፈጩ: በመጋዝ ተተረተሩ: ለአራዊት ተሰጡ: በግፍም ተጨፈጨፉ:: ቀባሪ አጥተውም ወደቁ::

+በዚሕ ጊዜ ማር ፊቅጦር እናቱን ቅድስት ማርታን በዕንባ ተሰናብቶ ወደ ንጉሡ ቀርቦ በክርስቶስ ስም ታመነ:: ክፉ አባትም በልጁ ላይ ሞትን መከረ::

+ከዚያም ቅዱሱን አፉን በብረት ለጉመው ወደ ምድረ
ግብፅ አወረዱት:: መሪያቸው እንዳልነበረ ወታደሮቹ
መኳንንቱ ሁሉ
ተዘባበቱበት:: እርሱ ከምድራዊ ንግሥና ሰማያዊ
መንግስትን: በሰዎች ፊት ከመክበር ስለ ክርስቶስ ሲል
መናቅን መርጧልና::

+ለቀናት: ለወራትና ለዓመታት መኳንንቱ እየተፈራረቁ
አሰቃዩት:: በርሱ ላይ ያልሞከሩት የስቃይ ዓይነት
አልነበረም::
አካሉን ቆራርጠዋል: ዓይኖቹን አውጥተዋል: ምላሱንም
ቆርጠዋል::

+በዚሕች ዕለት ግን በሰይፍ አንገቱን ቆርጠውታል::
ስለዚህም እናት ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ማክበር
ታከብረዋለች::
እግዚአብሔርም ለቅዱስ ፊቅጦር እንዲህ አለው:-

"እንደ
አቅሙ ስምህን የጠራ: መታሠቢያህን ያደረገ: ስምህን
ያከበረ:
የብርሃን ልብስ አጐናጽፌ ወደ መንግስተ ሰማያት
አስገባዋለሁ::"

❖ቸሩ አምላከ ፊቅጦር ሁላችንም ይማረን:: ከቃል ኪዳኑ
አሳትፎ ለርስቱ ያብቃን::

❖ሚያዝያ 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ጽኑዕና ኃያል ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
2.ቅድስት ማርታ (የፊቅጦር እናት)
3.ብጽዕት እስጢፋና (በክርስቶስ ስላመነች ከ2
ሰንጥቀው የገደሏት የ15 ዓመት ወጣት)
4.ቅዱሳን ሳሲማና አባ ኖባ (ሰማዕታት)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.የጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በዓለ
ስቅለት
2.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ) 4.ቅዱስ
ያዕቆብ ዘግሙድ
5.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
6.ቅዱስ
ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

++"+ እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ: እስከ
አሁንም ስለምታገለግሏቸው ያደረጋችሁትን ሥራ:
ለስሙም ያሳያችሁትን
ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመጸኛ አይደለምና:: በእምነትና
በትእግስትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ
እንጂ ዳተኞች
እንዳትሆኑ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን
ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን::+"+ (ዕብ.
6:10-13)

<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>

https://t.me/saint_mikael