Get Mystery Box with random crypto!

መልእክተኛውን ሰው ጌታው ወደንጉሡ አስተዳደር በላከው ጊዜ ሦስት ቀን የሚያስኬደውን ሩቅ መንገድ በ | ቤተ ቅዱስ ሚካኤል

መልእክተኛውን ሰው ጌታው ወደንጉሡ አስተዳደር በላከው ጊዜ ሦስት ቀን የሚያስኬደውን ሩቅ መንገድ በአንዲት ሰዓት ውስጥ አድርሰህ የመለስከው ኃያሉ ሰማዕት ፀሐይ ዘልዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ! እኛንም በአማላጅነትህ የምታመን ልጆችህን ከእርኩሰት የበደል ጎዳና በረድኤትህ መልሰን!
ሚያዝያ 23 ቀን የልዳው ፀሐይ የቅዱስ ጊዮርጊስ የሰማዕትነቱ ፍጻሜው ነውና እጅግ የበዛውን ገድሉን በጥቂቱ ብንመለከተው ለበረከት ይሆነናል፡፡ ይኸውም ታላቅ ሰማዕት ለጣኦት ካልሰገድክ ብለው 70 ነገሥታት በጋራ ሆነው ለ7 ዓመታት እጅግ አሠቃቂ መከራዎችን ያደረሱበት አጥንቱንም ፈጭተው ደብረ ይድራስ ተራራ ላይ የበተኑት ነው፡፡ ሦስት ጊዜ ሲገድሉትም ጌታችን ሦስት ጊዜ ከሞት እያስነሣው ከሃድያንን ያሳፈረ ሲሆን ሰማዕትነቱን ፈጽሞ አንገቱ ሲቆረጥም ደም ውኃና ወተት ከአንገቱ ፈሰሰና ብዙዎችን አሳመ፡፡
ዳግመኛም በዚኽ ዕለት ጌታችን ተገልጦለት ከንዳድ በሽታ የሚጠብቅ ታላቅ ቃልኪዳን የገባለት ጻድቁ አባ ርቆ ዕረፍቱ ነው፡፡ ረድኤት በረከቱ ይደርብን በጸሎቱ ይማረን!!
ሊቀ ሰማዕታት ፀሐይ ዘልዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ፡- ጊዮርጊስ ማለት ‹‹ኮከብ ብሩህ፣ ፀሐይ›› ማለት ነው፡፡ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀገሩ ፍልስጤም ልዩ ስሟ ልዳ ሲሆን የተወለደው በ277 ዓ.ም ጥር 20 ቀን ነው፡፡ ጊዮርጊስ ማለት ኮከብ፣ ብሩህ፣ ሐረገ ወይን፣ ፀሐይ ማለት ነው፡፡ አባቱ ዞሮንቶስ ወይም አንስጣስዮስ የልዳ መኳንንት ሆኖ ተሹሞ ይኖር ነበር፤ እናቱ ቴዎብስታ ወይም አቅሌስያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሌላ ማርታና እስያ የሚባሉ ሁለት ሴት ልጆችን ወልዳለች፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ዐሥር ዓመት በሆመው ጊዜ አባቱ ስለሞተ ሌላ ደግ ክርስቲያናዊ መስፍን ወስዶ አሳደገው፡፡ መድፍኑም በጦር ኃይል አሰለጠነው፡፡ ሃያ ዓመትም በሞላው ጊዜ መስፍኑ የ15 ዓመት ቆንጆ ልጅ ነበረችውና እርሷን አግብቶ ሀብቴን ወርሶ ይኑር ብሎ ድግስ ሲያስደግስ ጌታችን ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዚህ አላጨውምና የመስፍኑን ነፍስ ወሰደ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ኀዘኑን ጨርሶ ወደ ቤሩት ሀገር ሄደ፡፡ በቤሩት ደራጎንን ያመልኩና ሴት ልጆቻቸውን ይገብሩለት ስለነበር ሰማዕቱ ደራጎኑን በኃይለ መስቀል ድል ነስቶት ሕዝቡን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር አስገብቷቸዋል፡፡

ወደፋርስ ቢመለስ ዱድያኖስ ሰባ ነገሥታት ሰብስቦ ሰባ ጣዖታት አቁሞ ሲሰግድ ሲያሰግድ ቢያገኛቸው ለሃይማኖቱ ቀናዒ ነውና ከቤተመንግስቱ ገብቶ በከሃዲያኑ ሰባው ነገሥታት ፊት ክርስቲያን መሆኑን በመመስከር የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት መሰከረ፡፡ ዱድያኖስም ማንነቱን ከተረዳ በኋላ ‹‹አንተማ የኛ ነህ በዐሥር አህጉር ላይ እሾምሃለሁ የኔን አምላክ አጵሎንን አምልክ›› አለው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ‹‹ሹመት ሽልማትህ ለአንተ ይሁን እኔ አምላኬ ኢየሱስ ክርስቶስን አልክደውም›› አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዱድያኖስ እጅግ ተናዶ ብዙ አሠቃቂ መከራዎችን አደረሰበት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ጌታችንን ‹‹ይህን ከሃዲ እስካሳፍረው ድረስ ነፍሴን አትውሰዳት›› በማለት መከራውን ይታገስ ዘንድ ለመነው፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶ ፈቃዱን ይፈጽምለት ብዙ በመከራው ሁሉ ጽናትን ሰጥቶታል፡፡ ሦስት ጊዜም ከሞት አስነሥቶታል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም የደረሱበት እጅግ አሠቃቂ መከራዎች የሰው ኅሊና ሊያስባቸው እንኳን የማይችላቸው ናቸው፡፡

በመጀመሪያም ዱድያኖስ በእንጨት ላይ ካሰቀለው በኋላ ሥጋውን በመቃን አስፈተተው፣ ረጃጅም ችንካሮች ያሉበት የብረት ጫማ አጫምቶት ሂድ አለው፡፡ ጌታችንም ቅዱስ ሚካኤልን ልኮለት ፈውሶታል፡፡ ዳግመኛም በሰባ ችንካሮች አስቸንክሮ በእሳት አስተኩሶ አናቱን በመዶሻ አስቀጥቅጦ በሆዱ ላይ የደንጊያ ምሰሶ አሳስሮ እንዲያንከባልሉት አደረገ፡፡ ሥጋውንም በመጋዝ አስተልትሎ ጨው ነሰነሰበት፡፡ ሥጋውም ተቆራርጦ መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈቀ ሌሊት በእጁ ዳስሶ ከፈወሰውና ‹‹ገና ስድስት ዓመት ለስሜ ትጋደላለህ፣ 3 ጊዜ ትሞታለህ፣ በ4ኛውም ታርፋለህ›› ካለው በኋላ በመከራውም ሁሉ እርሱ እንደማይለየው ነገረው፡፡

ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከዚያ ካደረሰበት አሠቃቂ መከራዎች ሁሉ ድኑ ፍጹም ጤነኛ መሆኑን በተመለከተ ጊዜ እጅግ ደንግጦ ‹‹የሚያሸንፍልኝ ቢኖር ብዙ ወርቅ እሰጠዋለሁ›› ብሎ ተናገረ፡፡ አትናስዮስ የተባለ መሰርይ አንዲትን ላም በጆሮዋ ሲያንሾካሹክባት ለሁለት ተሰንጥቃ ስትሞት ለንጉሡ አሳየውና ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲሚያሸንፍ ምልክት አሳየ፡፡ ንጉሡም ያሸንፍልኛል ብሎ ደስ አለው፡፡ መሰርይውም ሆድ በጥብጦ አንጀት ቆራርጦ የሚገድል መርዝ ቀምሞ አስማተ ሰይጣን ደግሞበት እንዲጠጣው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጠው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ቢጠጣው እንደ ጨረቃ ደምቆ እንደ አበባ አሸብርቆ ተገኝቷል፡፡ በዚህም ጊዜ ጠንቋዩ ማረኝ ብሎ ከእግሩ ሥር ወደቀ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም መመለሱን አይቶ የቆመባትን መሬት በእግሩ ረግጦ ውሃን አፍልቆ ወደ ጌታችን በጸሎት ቢያመለክት ሐዋርያው ቶማስ በመንፈስ መጥቶ አጠመቀው፡፡ እርሱም ስለጌታችን አምላክነት መስክሮ ጥር 23 ቀን አንገቱን ለሰይፍ ሰጥቶ በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን በመንኰራኩር አስፈጭቶ ከትልቅ ጉድጓድ ጥሎት ደንጊያ ዘግቶበት አትሞበት ሄደ፡፡ ጌታችንም የተፈጨውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ሥጋ በእጁ ዳስሶ ፈውሶታል፡፡ ወደ ከሃዲውም ንጉሥ ተመልሶ ‹‹አምላኬ ከሞት አዳነኝ›› በማለት መሰከረ፡፡ ንጉሡም ዳግመኛ በብረት አልጋ አስቸንክሮ ከበታቹ እሳት አነደደበት ነገር ግን እሳቱ ደሙ ሲንጠባጠብበት ጠፍቷል፡፡ ጌታችንም ፈወሰው፡፡ ከዚህም በኋላ ዱድያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ‹‹ኢየሱስ አምላክ መሆኑን አሳየኝ›› ቢለው የለመለሙትን ዕፅ አድርቆ፣ የደረቁትን ደግሞ አለምልሞ፣ ከሞቱ 430 ዓመት የሆናቸውን ሙታንን አስነሥሰቶ አሳይቶታል፡፡ ነገር ግን ንጉሡ ልቡ ክፉ ነውና በርኃብና በጽም ይሙት ብሎ ምንም ከሌላት መበለት ቤት አሳስሮታል። እርሷም የሚቀመስ ስትፈልግ ቤቷን በእህል አትረፍርፎ የታሰረበትን ግንድ ማለትም የቤቱን ምሰሶ አለምልሞታል፡፡ ልጇም ጆሮው የማይሰማ ነበርና ፈወሰላት፡፡ መበለቲቷንም ከነልጆቿ አጥምቆአቸው መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ከእስራቱ ፈትቶት ተመልሷል፡፡

ዳግመኛም ንጉሡ ዱድያኖስ ጭፍሮቹን ‹‹በመንኰራኩር ፈጭታችሁ አጥንቱን ደብረ ይድራስ ተራራ ላይ ወስዳችሁ ዝሩት›› ብሎ አዘዛቸው፡፡ ጭፍሮቹም የቅዱስ ጊዮርጊስን ሥጋ በመንኰራኩር ፈጭተው ወስደው በተራራው ላይ ቢረጩት ሥጋው ያረፈበት ሳር፣ ቅጠሉ፣ ደንጊያው፣ እንጨቱ ሁሉ ‹‹ጊዮርጊስ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር፣ ጊዮርጊስ ሰማዕቱ ለእግዚአብሔር›› እያሉ አመስግነዋል፡፡ አሁንም ጌታችን ለሦስተኛ ጊዜ ከሞት አስነሣውና ሥጋውን ፈጭተው በተራራም ላይ ሥጋውን በትነውት ወደ ንጉሡ የሚመለሱትን ወታደሮች በመንገድ ከኋላቸው ሄዶ ደረሰባቸውና ‹‹ቆዩኝ ጠብቁኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም እጅግ ደንግጠው ይህ እንዴት እንደሆነ ሲጠይቁት ‹‹አምላኬ ከሞት አዳነኝ›› አላቸው፡፡ ጭፍሮቹም እጅግ ደንግጠው ከእግሩ ስር ወድቀው ይቅር በለን ብለው በአምላኩ እንደሚያምኑ መሰከሩለት፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከመሬት ላይ ውሃ አመንጭቶ በጸሎት ጌታችንን ቢጠይቅ ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ አጥምቋቸዋል፡፡ እነርሱም በንጉሣቸው ፊት ሄደው ስለጌታችን በመመስከር በሰማዕትነት ዐርፈዋል፡፡