Get Mystery Box with random crypto!

ሚያዝያ 23 - እንኳን ለሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ( | ቤተ ቅዱስ ሚካኤል

ሚያዝያ 23 - እንኳን ለሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ

( በገብረ ሥላሴ)
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አሜን
ሚያዝያ 23 ‹‹ጸሎቱና በረከቱ ለሁላችን ይደረግልንና ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገው ተአምር ይኽ ነው፡

ብባ ከምትባል አገር ሰዎች ወገን የሆነ አንድ አረማዊ ሰው ነበረ፡፡ መካ የሚገኘውን መስጊድ ለመጎብኘት ወደ ምድረ ኅልዛዝ ሄደ፡፡ በዚኽም ቦታ ዲያብሎስ ከነሠራዊቱ ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀበት ነው፡፡ ዳግመኛም የአትሪብን አገር ነቢይ መቃብር ይጎበኝ ዘንድ ሄደ፡፡ ጉብኝቱንም ከፈጸመ በኋላ ከጓደኞቹ ጋር ወደ ሀገሩ ተመልሶ እየሄደ ሣለ ወደኋላ ዘግይቶ ቆየና በዱር ብቻውን ቀረ፡፡ መሪር ልቅሶንም አለቀሰ፡፡ መድሪቱም በጣም በረሃ ናትና ምንም የለባትም፣ ይልቁንም የዘላን ወይም የሽፍታ መኖሪያ ነበረች፡፡ አረማዊውም ወደ ነቢያቸውና ወደ ጓደኞቹ ቢጮኽ ማንም ለእርዳታ የሚደርስለት አላገኘም፡፡ በዚኽም ጊዜ በጭንቅና በፍርሃት ሆኖ በመከራ ጊዜ ስሙ ሲጠራ ይሰማው የነበረውን የቅዱስ ጊዮርጊስን ስም እየጠራ እንዲረዳው እየጮኸ ለመነ፡፡ ወዲያውም ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ መጥቶ በፈረሱ ላይ አፈናጠጠውና እንደ ዓይን ጥቅሻ ፈጥኖ ብባ ከምትባለው ሀገሩ አደረሰውና ከእርሱ ተሰወረ፡፡ የመጣበትም ሀገር ጎዳና ሦስት ወር ያህል የሚያስኬድ ነበር፡፡ ሰውየውም ይኽን ታላቅ ተአምር ከተመለከተ በኋላ ልቡ ተሰወረ፣ እንደሕማም ሆነበት፡፡ አእምሮውንም ካወቀ በኋላ ግን ተነሥቶ ወደ ቤቱ ገባ፡፡
‹የሀገሩ ሰዎችም ሌሎቹ ሰዎች ወይም ጓደኞችህ ከመምጣታቸው በፊት ከዚያ ከሩቅ አገር አንተ ብቻህን እንዴት መጣህ?› ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ በፈረሱ ላይ አፈናጦ በቅጽበት ወደ ሀገሩ እንዳመጣው ነገራቸውና ምልክትም ትሆነው ዘንድ ከመካ ያመጣትን ከሸክላ የተሠራችና የሰጎን እንቁላል የምትመስል ነገር አሳያቸው፡፡ እነርሱም በሰሙት ነገር እጅግ ተደነቁ፡፡ ሰውየውም ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይዞ ሄዶ ያችን ምልክት ለኤጲስ ቆጶሱ ሰጠውና ኃያሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገለትን እርዳታ ከሩቅ አገር እንዴት አድርጎ እንደዐይን ጥቅሻ በቅጽበት እንዳመጣው ነገረው፡፡ እስከመጨረሻውም ድረስ ለዚኽ ተአምር መታሰቢያ ሆኖ ይኖር ዘንድ ከቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ይሰቅለው ዘንድ ለመነው፡፡ ኤጲስቆጶሱም በቅዱስ ጊዮርጊስ ሥዕል አንጻር መጻሕፍት እንደሚነበቡባቸው ያለ ከፍተኛ ቦታ ላይ አስቀመጣት፡፡ በወቅቱም የቅዱስ ጊዮርጊስን ገድል የጻፈው ሰውም ወደዚያች ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ያችን ምልክት እንዳያት በጻፈው የሰማዕቱ ገድል ላይ ጠቅሶታል፡፡ ያች እንቁላል መሰል ሸክላ በመካ ሀገር ከሚገኝ መስጊድ በስተቀር ሌላ የትም ቦታ ላይ አትሰቀልም ነበር፡፡ የገድሉ ጸሐፊም ይህን ጠቅሶ ኤጲስቆጶሱን እንዴት ይህችን ሸክላ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደሰቀሏት ጠየቀው፡፡ ኤጲስቆጶሱም ኃያሉ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአረማዊው ያደረገለትን ተአምር ከምድረ አልኅዛዝ በፈረሱ ላይ አፈናጦ እንደዐይን ጥቅሻ ወደ ሀገሩ በማምጣት ከሞት እንዳዳነው ነገረው፡፡ ያችንም እንቁላል መሰል ሸክላ በመታሰቢያ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ እንዲሰቅልለት አረማዊው እንደለመነው ነገረው፡፡
የገድሉ ጸሐፊም በቅዱሳን አድሮ ድንቅ ድንቅ ነገርን የሚሠራ ልዑል እግዚአብሔርን እያመሰገነ ታሪኩን ከገድሉ ጋር ጻፈው፡፡ የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎቱ በረከቱ ለሁላችን በዕውነት ይደረግልን አሜን!››
ዳግመኛም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዚያ አረማዊ ሰው ታላቅ ተአምር ባደረገባት በዚያች ብባ በምትባል አገር የሚኖር አንድ አረማዊ ነበር፡፡ እርሱም ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚወድ በየዓመቱም በዕረፍቱ ዕለት ሚያዝያ 23 ቀን ብዙ በግና ፍየል እያረደ ዝክሩን የሚዘክር ነው፡፡ ለበዓሉም የሚያስፈልጉትን ሁሉ እያዘጋጀ ያቀርባል፡፡ በሥራውም ሁሉ በቅዱስ ጊዮርጊስ ይታመናልና ስለዚህም ነገር አረማውያን ጓደኞቹ ቀኑበት፡፡ ክርስቲያኖችን ወደሚጠላው አገረ ገዥ ዘንድ ሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስን በዓልም እንዳያደርግ ከሦስት ቀን በፊት ከሰሱት፡፡ ገዥውም ፈጽሞ በመቆጣት ደብዳቤ ጻፈና አትሞ አሽጎ ለዚያ የቅዱስ ጊዮርጊስ በዓል ለሚያክር አረማዊ ሰው ሰጠውና እልቅሐራ ወደምትባል ሩቅ አገር ደብዳቤውን በፍጥነት ወስዶ በዚያ ላለው ገዥ ይሰጥ ዘንድ አዘዘው፡፡ እንዲከታተሉትም ወታደሮችን አብረው እንዲሄዱ አዘዘ፡፡ ይኽንንም ያደረገው በዓሉን እንዳያደርግ ሊያስታጉለው ፈልጎ ነው፡፡
ያ አረማዊና ጭፍሮቹም መጓዝ ጀምረው ከከተማው ውጭ እየሄዱ ሣሉ አረማዊው ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ! የበዓልህን መታጎል ተመልከት…›› እያለ ጸለየ፡፡ ወዲያውም ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ተገለጠለትና ‹‹አይዞህ አትፍራ ና›› ብሎ እጁን ይዞ ከፈረሱ ላይ አስቀመጠውና እንደዐይን ጥቅሻ በቅጽበት ወስዶ ገዥው ካዘዘበት እልቅሐራ አገር ከገዥው ደጃፍ አደረሰው፡፡ ዳግመኛም ‹‹ሂድ ግባ የተላከውን ደብዳቤ አድርስ፣ መልሱንም ጽፎ ይሰጥሃል፣ እኔም እስክትመለስ ድረስ ከዚህ ቆሜ እጠብቅሃለሁ›› ብሎ ላከው፡፡
ገዥውም የተጻፈለትን ደብዳቤ ካነበበ በኋላ መልሱን ጽፎ ሰጠው፡፡ እርሱም ፈጥኖ ወደውጭ ቢወጣ ቅዱስ ጊዮርጊስን በፈረሱ ላይ እንደተቀመጠ እየጠበቀው አገኘውና እጅግ ደስ አለው፡፡ ሰማዕቱም ዳግመኛ ከፈረሱ ላይ አፈናጠጠውና በቅጽበት አረማዊውን ወደመጣበት አገር አደረሰውና ‹‹ወደቤትህ ግባና እንደልማድህ የበዓሌን መታሰቢያ አድርግ›› አለው፡፡ ያም አረማዊ ሰው በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኝቶ ወደቤቱ ሄዶ ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ሁሉ ከቀድሞ አስበልጦ አዘጋጀና ወስዶ ለኤጲስቆጶሱ ሰጠው፡፡
እነዚያ መጀመሪያ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስን በዓል እንዳያደርግ ለማስታጎል ብለው የከሰሱት አረማውያን ሰዎችም ዳግመኛ ወደገዥው ዘንድ ሄደው ‹‹እነሆ ያ ወደሩቅ ሀገር ደብዳቤ ይዞ እንዲሄድ ያዘዝከው ሰው በአንተ ላይ ተዘባበተብህ፣ ሳይሄድ ቀርቶ እርሱ ግን የጊዮርጊስን በዓል ለማክበር ይዘጋጃል›› ብለው ዳግመኛ ከሰሱት፡፡ ገዥውም እጅግ ተናዶ አስመጥቶ ጠየቀው፡፡ ሰውየውም ‹‹ጌታዬ ወደላከኝ አገር መልእክትህን አድርሻለሁ፣ የመልእክትህም መልስ እነሆ›› ብሎ የመልሱን ደብዳቤ ሰጠው፡፡ ገዥውም የመልሱን ደብዳቤ ባነበበው ጊዜ እርሱ ጽፎ በላከበት ዕለት የተጻፈ ደብዳቤ መሆኑን አረጋገጠ፡፡ በዚህም እጅግ ተገርሞ ‹‹ይህ መንገድ ለ3 ቀን ያህል የሚያስኬድ በጣም ሩቅ አገር ሆኖ ሳለ አንተ እንዴት በቅጽበት ደረስህ/›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ሰውየውም ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረገለትን ድንቅ ነገር በዝርዝር ነገረው፡፡ እነዚያ አብረውት ይሄዱ ዘንድ የተላኩት ጭፍችሮችም ከ6 ቀን በኋላ ተመልሰው መጥተው አረማዊው ከእነርሱ በዕለቱ ተለይቶ እንደነበር እነርሱ ግን ወደታዘዙብ አገር ደርሰው እንደመጡ ተናገሩ፡፡ አገረ ገዥውም ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ታላቅ ተአምርና ገናናት ፍርሃት አደረበት የሚቀስፈው መስሎታልና፡፡ የአገሩ ሰዎችም ሁሉ በተደረገው ታላቅ ተአምር ተደንቀው ፍርሃት አደረባቸው፡፡ ገዥውም ኤጲስቆጶሱን ጠርቶ ሁልጊዜም በየዓመቱ የቅዱስ ጊዮርጊስን በዓል ማክበሪያ የሚሆን ብዙ ገንዘብና ለበዓሉ ዝግጅት አስፈላጊ የሆነውን ሁሉ አሟልቶ ለቤተ ክርስቲያኑ ሰጠ፡፡