Get Mystery Box with random crypto!

ሰማሺኝ አለሜ ? መሄድ እሚሉት ቃል ፥ ከሀገር የሰፋ የትርጉም ኩታንኩት ፥ ጉንጭን እሚያለፋ መሄድ | ከመጻሕፍት ዓለም 🇪🇹

ሰማሺኝ አለሜ ?
መሄድ እሚሉት ቃል ፥ ከሀገር የሰፋ
የትርጉም ኩታንኩት ፥ ጉንጭን እሚያለፋ
መሄድ ሲሉ ሰምተሽ !
እንደ ያሬድ ዜማ ፥ እንደ እግዜር ያለ እረፍት
እንደ ቀን ቅዳሴ ፥ እንደ ሌ'ት ማህሌት
የ 6 ቀን እድሜ ፥ በ 60 አመት ሀሳብ
ያ'ንድ ቅፅበት ቀመር ፥ እንደ ህያው ጥበብ
ያነፅነውን ፍቅር !
ባ'ንድ የስልክ ጩኸት ፥ ባ'ልፈልግህም ቃል
ፍቅርሽን ገፈሺኝ ፥ እኔነቴ ወልቋል
የመውደድ ግርማዬ ፥ በሀፍረት ተራቁቷል ።

ሰማሺኝ አለሜ ?
መሄድ የሚሉት ቃል ፥ የማጣት ታላቁ
የክፋቱ ክፋት ፥ ከኔ አንቺን ማራቁ
ባ'ንቺ 1 መሄድ ውስጥ ፥ ሺ ጥሎኝ የሄደ
ክንድሽ ያረፈበት ፥ ጎኔ እየነደደ
አቅሜ እንዳለልነበርሽ
ዛሬ አቅም ቢከዳኝ አካሌ እየራደ
መሄድሽን ረግማለሁ !
ደግሞ እጠይቃለሁ ?
በቅተኸኛል ያልሺን ፥ በባዶ ሀሳቤ
በተጎሳቆለው ፥ በድኩም ምናቤ
ቢመላለስብኝ
ልክ እንደ እግዚኦታ ፥ እንደ ቤተስኪያን ደውል፥ አንገቴን ደፋለሁ
አፍጦ ከሚያየኝ አቧራ መሬት ላይ ፥ መልስ እጠብቃለሁ

ሰማሺኝ አለሜ
ባ'ንቺ መሳቅ ቀኔ በርቶ ፥ በሀዘንሽ ሲጠፋብኝ
እውር ልቤ ባንቺነትሽ ፥ እንደሚያይ ሰው ሲዘልብኝ
ተዚያ ተቤተስኪን ፥
ከመላዕክት መቅደስ ፦ ከእግዜሩ ደጃፍ
እነኛን ጥዑም ቀን ፥
በመዋደድ ቅኔ ፥ አብረን ስናሳልፍ
እጅሽ እጄን ይዞ ፥ የተባባልነው ቃል
የልጆቻችን ስም ፥ ማን ትባል ማን ይባል
እንዳልነተረኩሽ ፥ እንዳልጨቀጨቅሺኝ
ዛሬ ግን የለሽም ፥
ብቻዬን ከ እግዜር ጋ ፥ ሄደሻል ጥለሺኝ !

ሰማሺኝ አለሜ ?
መሄዱንስ ሂጂ ፥ ብርሀን ይነጠፍልሽ
ይቃናልሽ መንገድ ፥ ክንፈ መላዕክት ይጠብቅሽ
ደግሜ ልሻለሁ ፥ ይቅናልሽ መንገዱ
ሊያገኝሽ ይጋደል ፥ ይሙትልሽ ወንዱ
ሌሊቱ እንዲረዝም ፥ እያልኩኝ ባልነጋ
እኔ ግን አለሁኝ ፥ ተኝቼ እየቃዠሁ በትዝታሽ አልጋ
ሰርክ እየደነገጥኩ ፥ ሰርክ እየባነንኩኝ
የመሄድሽን ህልም ፥
ልትመጣ ነው በሚል ፥ እየተረጎምኩኝ

እኔ ግን አለሁኝ
በትዝታሽ አልጋ ፥ ላልነቃ ተኝቼ
መሄድሽን ላልወቅስ ፥
ስላ'ንቺ ልሸነፍ ፥ ምዬ ተገዝቼ