Get Mystery Box with random crypto!

ስለዚህ መንፈሳዊ ንባብ ማለት ራሳችንንም የሚሰሙንንም ለማዳን - አስተውሉ! ለማዳን - መጽሐፍ ቅዱ | ረከብኪ ቲዩብ | Rekebki Tube

ስለዚህ መንፈሳዊ ንባብ ማለት ራሳችንንም የሚሰሙንንም ለማዳን - አስተውሉ! ለማዳን - መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ የአበው ድርሳናትን፣ ትርጓሜያትን፣ ምክሮችን፣ ገድሎችን፣ ታሪኮችን ማንበብ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የማንበብ ግቡ እኛ ራሳችን እግዚአብሔርን ወደ መምሰል እንድናድግ ሌሎችንም ወደዚህ ምንድግና እንዲመጡ ማድረግ ነው ማለት ነው፡፡ ንባብ ብቻ ሳይኾን የማንኛውም መንፈሳዊ ግብር ዓላማም ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትና አንድነት መፍጠር ነው፡፡
ከላይ ባነሣነው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል እንደምንመለከተው አንድ ኦርቶዶክሳዊ ኹልጊዜ በመደበኛነት ሊያነብ እንደሚገባው ያስረዳል፡፡ ጢሞቴዎስ ጳጳስ ነው፡፡ ቢኾንም ግን ማንበብ - ያውም ኹልጊዜ - መጻሕፍትን መመልከት እንዳለበት ተመከረ! ቅዱስ ጢሞቴዎስ ከሴት አያቱና ከእናቱ ከልጅነቱ አንሥቶ ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲያነብ ያደገ ነው (2ኛ ጢሞ.3፡14-15)፡፡ አሁንም ቅዱስ ጳውሎስ ተቀብሎ ይበቃሃል ሳይኾን “በማንበብ ተጠንቀቅ” አለው፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከጥንት አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ብዙ አበው ወእማት አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም የምታስተምረን እነዚህን ቅዱሳን አበው ወእማት በሕይወታቸው፣ በትምህርታቸው እንድንመስላቸው እንጂ እንዲሁ እንድንጠቅሳቸው፣ ወይም ጽሑፋቸውን እንድናጠና ብቻ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምታበረታታን እነርሱ ክርስቶስን እንደመሰሉት እኛም እነርሱን እንድንመስል ነው፡፡
ከእነዚህ ቅዱሳን ኹሉ የመጀመሪያውን ስፍራ የምትይዘውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ካነሣነው ርእሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እጅግ አንባቢ እንደ ነበረች ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል፡፡ የሉቃስ ወንጌል 1፡47-55 ያለውን ኃይለ ቃል ብናነብ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዕውቀቷ እንደ ምን ጥልቅና ምጡቅ እንደ ነበረ መገንዘብ እንችላለን፡፡
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ በአራተኛው መ.ክ.ዘ. የነበሩ አባቶች ለምሳሌ እነ ቅዱስ ኤፍሬም፣ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ፣ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ሦስቱም የቀጰዶቅያ አባቶች፣ እነ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ መጻሕፍትን ዕለት ዕለት በማንበብ ተጠቃሾቹ መኾናቸውን እናስተውላለን፡፡ ከኢትዮጵያ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን፣ ቅዱስ ያሬድ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ መምህር ኤስድሮስ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እንዲያውም መምህር ኤስድሮስ እስከ ሦስት መቶ መጻሕፍት እንዳነበቡ የታወቀ ነው፡፡
እነዚህ ኹሉ ቅዱሳን ከተለያየ አከባቢ፣ ከተለያየ ባሕል፣ ከተለያየ ቤተ ሰብእ የተገኙ ቢኾኑም ቅሉ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ግን አለ፡፡ እንደየአገራቸው በዚያ ዘመን ይሰጥ የነበረውን ትምህርት ለምሳሌ ፍልስፍናን፣ ሥነ ከዋክብትን፣ ሒሳብን፣ ፊዚክስን፣ እና ይህን የመሳሰለውን የተማሩ ቢኾኑም መንፈሳውያን መጻሕፍትን በማንበብ ረገድ ግን አንድ ናቸው፡፡