Get Mystery Box with random crypto!

[ሐምሌ 19 የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ቂርቆስ በዓል] ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ | ራዚኤል ዘኢትዮጵያ

[ሐምሌ 19 የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ቂርቆስ በዓል]

ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ

❖ሐምሌ 19 ዕለት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል አምላካቸው ክርስቶስን
አንክድም በማለታቸው የፈላ ጋን ውስጥ የተወረወሩት ቅዱስ ቂርቆስና እናቱን
ቅድስት ኢየሉጣ ተራድቶ ያዳነበት በዓል ነው።

❖ ይኸውም የቅድስት ኢየሉጣን ልጅ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ከሐዲው መኰንኑ
ይዞ “ስምኽ ማነው” ብሎ በጠየቀው ጊዜ “ነቅዕ ዘእምዐዘቅት ንጹሕ ወእማይ
ዘኢይማስን ክርስቲያን ስምየ” (ከንጹሕ ዐዘቅትና ከማይለወጥ ከማይጠፋ ውሃ
የተገኘ ስሜ ክርስቲያን ነው ሞክሼ ስም ከፈለግኽ ደግሞ እናቴ የሠየመችኝ
ቂርቆስ ነው) በማለት ክርስትናው መመኪያው የኾነው ይኽ ቅዱስ ሕፃን
መለሰለት፡፡

❖ መኰንኑም ለአማልክት ከሠዋኽ ስታድግ እሾምኻለኊ ክርስቶስን ካድ
ቢለው ቅዱስ ቂርቆስ ግን “የሰይጣን መልእክተኛ ለእውነትም ጠላቷ የኾንኽ
ከእኔ ራቅ” አለው፡፡ መኰንኑም ይኽነን ሰምቶ በመቈጣት የቅዱስ ቂርቆስ
ደሙ እንደ ውሃ እስኪፈስስ ድረስ እንዲጨምቁት እና ጨውና ሰናፍጭ በኹለቱ የአፍንጮቹ ቀዳዳዎች እንዲጨመሩ ቢያደርግበት፤ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የጠነከረው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን “ትእዛዝኽ ለጒረሮዬ ጣፋጭ ኾነ ከማርና ከሥኳርም ለአፌ ጣመኝ” እያለ አምላኩ ክርስቶስን አመሰገነ፡፡

❖ መኰንኑ በዚኽ ሳያበቃ እናትና ልጇ በክፉ አሟሟት እንዲሞቱ በማሰብ
የረዘሙና የተሳሉ በእሳትም እንደ ፍም የጋሉ ዐሥራ አራት የብረት ችንካሮች
እንዲመጡ አስደርጎ ሰባቱ በእናቱ አካላት፤ ሰባቱ በሕፃኑ ሰውነት ላይ
እንዲሰካ ቢያስደርግም በጌታችን ትእዛዝ ግለቱ ጠፍቶ እንደ በረዶ
በመቀዝቀዝ ምንም ምን ጒዳት ሳያደርስባቸው ቀረ፡፡

❖ ከዚያም ወደ ወኅኒ ቤት እንዲገቡና እንዲዘጋባቸው አደረገ፤ ከዚያም ሕፃኑና
እናቱ የሚሠቃዩበት ታላቅ መንኰራኲር ለ፵ ቀናት ተሠርቶ ካለቀ በኋላ
ኹለቱንም በደራቁ ራሳቸውን ላጭተው የእሳት ፍሕምን በላያቸው ላይ
ቢያደርጉም የእግዚአብሔር መልአክ ሥቃዮቹን ኹሉ ከእነርሱ አራቀላቸው፡፡

❖ የሕፃኑ ምላስ እንዲቈረጥ አዝዞ ቢያስቈርጠውም ጌታችን ምላሱን
መልሶለታል፡፡ “ወአዘዘ ካዕበ ያፍልሑ ማየ ውስተ ጽሕርት ዐቢይ ወይደይዎሙ
ለሕፃን ቂርቆስ ወለእሙ ኢየሉጣ” ይላል በታላቅ ጋን ውሃ አፍልተው ሕፃኑንና
እናቱን እንዲጨምሯቸው ሲያዝዝ ከሚፍለቀለቀው ውሃ ድምፅ የተነሣ ለጊዜው እናቱ ፍርሀት ሥጋዊ ቢያገኛትም ልጇም ወደ ጌታችን በጸለየላት ጊዜ ፍርሃቱ ርቆላት ከልጇ ጋር ስትገባ መልአከ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ ውሃውን አቀዝቅዞ ሐምሌ ፲፱ አውጥቷቸዋል፡፡

❖ በመጨረሻም የሰማዕትነትን አክሊል የሚያገኝባት ጊዜ ሲደርስ ጌታችን
ተገልጾለት ስሙን ለሚጠራ ኹሉ ቃል ኪዳንን ከሰጠው በኋላ ሥጋኽን
በኤልያስ ሠረገላ ላይ አኖርልኻለኊ አለው፤ ይኽነን በሰማ ጊዜ በእጅጉ
ተደሰተ፤ ከዚኽም በኋላ ጥር ፲፭ በሌሊቱ እኲሌታ ከእናቱ ጋር አንገቱ ተቈረጠ
የሰማዕትነትን ክብር ተቀዳጅተዋል።

❖ ጥር ፲፮ ደግሞ የቅዱስ ቂርቆስ ማኅበር የኾኑ ዐሥራ አንድ ሺሕ አራት
በሰማዕትነት ዐልፈዋል፡፡
ሊቁ አርከ ሥሉስም የቅዱስ ቂርቆስን ተጋድሎ በማዘከር፡-

“እግዚአብሔር ሤመ ረድኤቶ ለንእስናከ ዐቃቤ ወስምዖ መጥበቤ ፍትወ ምግባር ቂርቆስ ወምዑዘ ኂሩት እምከርቤ ለዘተጽዕረ በምንዳቤ ወለዘቈስለ በጥብጣቤ ለአባልከ ሰላም እቤ”
(እግዚአብሔር ረድኤቱን ለታናሽነትኽ ጠባቂን አስቀመጠ፤ ብልኅ የሚያደርግ
ምስክርነቱንም፤ ምግባርኽ ያማረ በጎነትኽ ከከርቤ ይልቅ የሚሸት ቂርቆስ፤
በመከራ የተቸገረ በግርፊያ የቈሰለ ለኾነ ሰውነትኽ ሰላም እላለኊ) እያለ
ሕፃኑን ሰማዕት ያወድሳል፡፡

❖ #ሊቁ_አባ_ጊዮርጊስ_ዘጋሥጫም_በመጽሐፉ፦
“ሰላም ለቂርቆስ ወሬዛ በመንፈስ
በልደት ንዑስ፤ ንጹሕ ከመ ዕጣን
ወፍሡሕ ከመ ወይን”፡፡
(በልደተ ሥጋ ታናሽ በመንፈስ ጐልማሳ፤ እንደ ዕጣን ንጹሕ እንደ ወይንም
አስደሳች ለኾነ ለቂርቆስ ሰላምታ ይገባል)

❖“ሰላም ለሰማዕታት እለ ምስሌሁ ፭፼ ወ፬፻፤ ፬፼ ወ፪፻፲ወ፬”፡፡
(ከርሱ ጋር ያሉ ፭፼ ከ፬፻፤ ፬፼ከ፪፻፲፬ ሰማዕታት ሰላምታ ይገባቸዋል) በማለት
አመስግኗል፨

[የሊቀ መላእክት የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት የቅዱስ ቂርቆስ የእናቱ
የኢየሉጣ፤ ስለአምላካቸው ስለ ክርስቶስ ፍቅር አንገታቸው በሰይፍ የተቆረጡት
የሰማዕታት በረከት ይደርብን፨
[ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ]
@razielethiopia