Get Mystery Box with random crypto!

እግዚአብሔር አለ | ራስን ማግኘት!!!

እግዚአብሔር አለ ጊዜው ደርግ ማለትም ወታደራዊ መንግስት በኢትዮጵያ በሚገዛበት ወቅት ነው። አንድ በጥበቃ ስራ ይተዳደሩ የነበሩ ሰው ነበሩ። የእኒህ ሰው አሰሪያቸው ከወቅቱ ባለስልጣናት አንዱ ናቸው። ምስኪኑ ጥበቃ ለእንጀራ ብለው ስርዓቱን ቢጠጉም የወቅቱን ርዕዮተ ዓለም የማይቀበሉ ጠንካራ ክርስቲያን ነበሩ። ሰዉየው የባለስልጣኑን የመኖሪያ ገቢ በዘበኝነት ተቀጥረው እየጠበቁ እዚያው ውለው እዚያው ሲያድሩ በየጊዜው ለሚመላለሰው መኪና ቁጭ ብድግ እያሉ በር ከመክፈት ጀምሮ በቤትና ከቤትም ዉጭ በመላላክ ወዲህ ወዲያ ይላሉ። ይህ ሁሉ ቢሆንም ባለቻቸው ሰዓት ዳዊታቸውን ሳይደግሙ አይውሉም ነበር። ሲበዛ ጸሎተኛ ናቸው። ባለስልጣኑ ግን ይሄንን አልወደደላቸውም። ይልቁንም ዳዊታቸውን በእጃቸው ይዘው ማሕደሩን በትክሻቸው አንግተው ጸሎት ላይ ሆነው ሲያያቸው አርድ እንቀጥቅጡ ይነሳበታል። በላዩ ላይ ያለው የጥርጥርና ክህደት መንፈስ እያስጨነቀ ያስቆጣዋል፣ ያሳብደዋል፣ ያስጮኸዋል ስለዚህ በወጣ በገባ ቁጥር ጸሎት እንዳይጸልዩ ይከለክላቸዋል። ደግሞ ደጋግሞ እግዚአብሔር የሚባል የለም ይላቸዋል። አንድ ቀን ግን አምርሮ "አንተ ሽማግሌ ከዛሬ ጀምሮ ይህንን ዳዊትህን ስትደግም ባይህ አብዮታዊ እርምጃ ነው የምወስድብህ" ብሎ አስጠነቀቃቸው። ሰዉየው ግን ጸሎታቸውን በፍጹም አላቋረጡም። ስለዚህ በሌላ ጊዜ ሲጸልዩ ስላያቸው በጣም ተበሳጭቶና ተቆጥቶ ዳዊታቸውን ቀምቶ በጥፊ ከመታቸው በኋላ "አንተ ሽማግሌ ነግሬህ ነበር እኮ እግዚአበሔር የለም..." ብሎ ጮኸባቸው። ሰዉየው የዋዛ አልነበሩም እንኳንስ ሊፈሩት ከፊታቸው ወዲያ ገፈተሩትና ለጥበቃ ስራ የተሰጣቸውን መሳሪያ አቀባብለው ከደቀኑበት በኋላ "እኔ እኮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲያ ስታንቋሽሸኝ ታግሼ ዝም ማለቴ፣ ስሰድበኝ ያልሰደበኩህ፣ ስትመታኝም ያልመታሁህ እግዚአብሔር አለ ብዬ ስለማምንና እግዚአብሔርን ስለምፈራ ነው አሁን አንተ እንዳልከው እግዚአብሔር ከሌለማ ምን አለፋኝ?" ብለው ያቀባበሉትን መሳሪያ ተኮሱና ግንባሩን ብለው ጣሉት ይባላል።
ምንጭ "ምጥን ቅመም ቁጥረ 4" መጽሐፍ

@RasenMagyet3679
@RasenMagyet3679