Get Mystery Box with random crypto!

+++ 'በስሙ ጥራው' +++ ሰይጣን የሰው ልጆችን የክፋት እስረኛ ከሚያደርግበት ዘዴው አንዱ ኃ | ራስን ማግኘት!!!

+++ "በስሙ ጥራው" +++

ሰይጣን የሰው ልጆችን የክፋት እስረኛ ከሚያደርግበት ዘዴው አንዱ ኃጢአትን "ኃጢአት" ብለን እንዳንጠራት ማለሳለስ ነው። ከዚያ ይልቅ መልካም በሚመስልና ቢሰማም ብዙ በማይቆረቁር ስም እንድንጠራው ያደርገናል። ለምሳሌ በትዳር ሳይወሰኑ እንዲሁ ከአገኙት ጋር በዝሙት መውደቅ "ነጻ ፍቅር" ("free love")፣ በሚስት እና በባል ላይ መሄድ ደግሞ "ባለጉዳይ"ነት (affair) ተሰኝተዋል። ይህን የሚያደርጉትም ኃጢአቱን ያለ ምንም መሳቀቅ መሥራት እንዲችሉ ስሙን ያሳምሩታል።

ሰው የትኛውንም ኃጢአት ከመስራቱ በፊት ኃጢአቱን የሚጠራበት ስም ይለያል። ኃጢአትን የምንጀምረው በጎ ዓላማ እና ጥሩ ስም ያለው አስመስለን ነው። የሚሰክረው ከስካሩ በፊት ምን ልታደርግ ነው? ቢሉት "ልዝናና ነው" ይላል። የሚሳደበውና የሚራገመውም ከስድቡ በፊት ምን ልታደርግ ነው? ቢሉት "ልመክር" ወይም "እርማት ልሰጥ ነው" ይላል፤ ሌሎቹንም እንዲሁ። ጌታችን በመሰለው የጠፋው ልጅ ምሳሌ ላይ ያለውን ልጅ ከአባቱ ቤት ከመውጣቱ በፊት አግኝተን "ለምን ንብረት ተካፍለህ ከአባትህ ቤት ርቀህ ትሄዳለህ?" ብለን ብንጠይቀው፣ "ዓለምን ለማየት" ይላል እንጂ "ኃጢአት ስላማረኝ" እንደማይል ጥርጥር የለውም።

ከኃጢአት መራቅ ትፈልጋለህ? እንግዲያስ ልታደርግ ያሰብከውን ክፋት በስሙ ጥራው። አታድበስብስ፣ አታለስልስ፤ በቃ ኃጢአት ነው። ስለዚህ አትጀምረው። ገብተኽበትም እንደሆነ ስሙን እያሽሞነሞንክ ራስህን አትዋሸው። በደል እንደ ሆነ አምነህ በትክክለኛው ስሙ እስክትጠራውና እስክትጋፈጠው ድረስ መድኃኒት የለህም። መዝሙረኛው ዳዊት በኦርዮ ሚስት ተሰነካክሎ ከወደቀ በኋላ ዳግመኛ የተነሣው "አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ" ብሎ መጸለየ በጀመረ ጊዜ ነው።(መዝ 51፥4)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ሐምሌ 2፣ 2014 ዓ.ም.
ሻሸመኔ

@RasenMagyet3679
@RasenMagyet3679