Get Mystery Box with random crypto!

ጣዝማ እጅግ ብልሕ ናት። መሬት ቀዳ ገብታ እንደዚያ ያለ መድኃኒት የሚሆን ማር ትሠራለች። ምነው እ | መልካም አስተሳሰብ ™

ጣዝማ እጅግ ብልሕ ናት። መሬት ቀዳ ገብታ እንደዚያ ያለ መድኃኒት የሚሆን ማር ትሠራለች። ምነው እናንተ ሰዎች ወይ ከፈጣሪ ወይም ከሰው ብልሐትን አትፈልጉምን?
ማር ሁለት ጊዜ ያገለግላል አንድ ጊዜ መጠጥ አንድ ጊዜ መብራት ሆኖ። ምነው ቢሉ፥ የብልሕ ሥራ ነውና አሰርም የለው።
ቅቤ ለመጽሐፍ ዘመዱ አይደለም።መጽሐፍ ግን ለሰው ቅቤ ነው።
ነገስታት እና መምህራን እንደ ውሃ ቢሆኑ ወንጌል በዓለም ሁሉ በተሰበከ ነበር።የውሃም መልካምነቱ እንደዚህ ነው።ከምድር ላይ በፈሰሰ ጊዜ ሁሉን አብቅሎ ምግብና ልብስ ይሆናል፤ዱቄቱን አርሶ እንጀራ ያደርገዋል፤የደረቀውን እርሾ ለስላሳ ያደርገዋል፤ያደፈውን አጥቦ ንጹሕ ያደርገዋል፤መምህራንም እንዲህ ቢሆኑ ዓለም ሁሉ አንድ አካል አንድ አምሳል በሆነ ነበር።
የረሀብ ጌትነቱ መቼ ነው እህል በታጣ ጊዜ ነው ምነው ቢሉ የሌለውን አምጡ ይላልና። የማጣትስ ጌትነቱ መቼ ነው የፈለጉት ነገር በታጣ ጊዜ ነው። የጥጋብስ ጌትነቱ መቼ ነው መብልና መጠጥ በተገኘ ጊዜ ነው። የመብላትስ ትርፉ ምንድር ነው ጥጋብ ነው።
ሰው ፍሪዳን አብልቶ አብልቶ ያሰባዋል በመጨረሻውም ይበላዋል።ምነው ቢሉ አብልቶ መብላት ገበያ ነው። (capitalism )
ማርና እሬትን ቢመዝኑ ማን ይደፋል እሬት ምነው ቢሉ ክፉ መራራ ነውና።ከብዙ ቀን ደስታ ያንድ ቀን መከራ ይበልጣል።
ሕዝብና ሕዝብ ደጋና ቆላ ናቸው ንጉሡ ግን ገበያ ነው ሁሉን ያገናኛልና።ሸክላ ከተሰበረ በኋላ ገል ነው መኳንንትም ከተሻሩ በኋላ ሕዝብ ናቸው።
ሸክላ እጅግ ክፉ ነው ውሀ አርሶ አሠርቶት መከታ እየሆነ እሳትን ያስወጋዋል።ክፉም ሰው እንደዚያ ነው። ወንፊት ዱቄትን እንዲነፋ ዘርዛራም ሸማ ጠጅን እንዲያወርድ ባለቤቱም ያልቻለውን ምሥጢር ሌላው ሰው አይችለውም።
ቅቤ ካይብና ካጓት እንዲለይ በላይም እንዲሆን ጻድቅም ሰው እንደዚያ ነው።
ማሽላን ወፎች ራስ ራሱን ሲሉት አይቶ ባቄላ ፍሬውን በጎኑ አዝሎ ክንፉን አልብሶ ይኖራል።ውሃ ወርዶ ወርዶ ባይመቸው ኩሬ ይሆናል።ብልህም በጨነቀው ጊዜ ሞኝ ይሆናል።
መሳል መልካም ነው፤ብረትን ይስለዋልና።መጽሐፍም መልካም ነው፤ልብን ያበራዋልና።
ፀሐይ ለኢያሱ ለምን ቆመችለት መድሐኒቱን ኢየሱስ መስሏት ይሆን?ኢየሱስ መድሐኒቱ ሰውም አይገድል፤ያድናል እንጂ
አይሁድ ጾማቸውን አጥርጠው ይጾማሉ፤ክርስቲያኖች ግን ጦማቸው የጠራ አይደለም፤አርብ የታረደውን የበግ ስጋ ይበላሉና።አይሁድ ከእንስሳት እንኳን ለይተው ነው የሚበሉት፤ክርስቲያኖች ግን ወንድማቸውን ይበላሉ።