2022-11-25 17:19:25
የሙሾ ያለህ!
“የማረኩን በዚያ [በባቢሎን] የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፤ የወሰዱንም፦ የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን። የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?” (መዝ. 137፥3-4)
ይህን ክፍል ሳነብ ብዙውን ጊዜ ጥያቄ ይፈጠርብኛል። የእግዚአብሔርን መዝሙር በባዕድ ምድር መዘመር ምን ክፋት አለው? መዝሙር የሚዘመረው በእስራኤል ምድር ብቻ ነውን? በባዕድ ምድር አይዘመርም? ነቢዩ ዳንኤል በባዕድ ምድር ይጸልይ አልነበር? በምርኮ ምድር ያሉት እስራኤላውያን ስለ ባቢሎን ሰላም እንዲጸልዩ ተነግሯቸው አልነበር? ታዲያ ምርኮቹ እስራኤላውያን የጽዮንን መዝሙር እንዲዘምሩ ባቢሎናውያኑ ቢጠይቁ ምን ክፋት አለው?
አሁን እንደ ተረዳሁት ከሆነ ባቢሎናውያኑ ምን ዐይነት መዝሙር እንዲዘመር ነው የጠየቁት? የሚለውን ከተረዳን የእስራኤላውያኑን እምቢታና ሐዘን ምክንያት ለመረዳት በተሻለ ቦታ ላይ እንሆናለን። እስቲ በሌሎች ትርጉሞች እንመልከተው (የዕብራይስጡን ሐሳብ በደንብ ይገልጣሉና)፤
“የማረኩንና ሥቃይ የሚያሳዩን ሰዎች በመዘመር እንድናስደስታቸው ‘ከጽዮን መዝሙሮች አንዱን ለእኛ ዘምሩልን’ አሉን” (አዲስ ትርጉም)።
“የማረኩን በዚያ እንድንዘምርላቸው ጠየቁን፤ የሚያሠቃዩን የደስታ ዜማ ፈለጉብን፤ ደግሞም፣ ‘ከጽዮን መዝሙሮች አንዱን ዘምሩልን’ አሉን” (አመት)።
“የሚያስጨንቁን ማራኪዎቻችን ግን፣ ‘እስቲ ከጽዮን ዝማሬዎች አንዱን አሰሙን’ እያሉ የደስታ ዝማሬ እንድንዘምርላቸው አጥብቀው ወተወቱን” (ሕያው ቃል)።
በእነዚህ ትርጉሞች፣ “እንድናስደስታቸው፤ የደስታ ዜማ፤ የደስታ ዝማሬ” ከሚሉት አገላለገጦች እንደምናስተውለው ባቢሎናውያኑ ከተማራኪዎቻቸው የፈለጉት መዝሙር የደስታ መዝሙር ነው። ማራኪዎቹና አስጨናቂዎቹ ባቢሎናውያን ተማራኪዎቻቸው የደስታ መዝሙር እንዲዘምሩላቸው ነበር የፈለጉት። ይህ ደግሞ ሰው የሞተበት ሐዘንተኛ የሰርግና የድል መዝሙር እንዲዘምር ጥያቄ ከማቅረብ አይተናነስም። ባቢሎናውያኑ የእስራኤላውያኑ ሐዘን ምክንያት ናቸው፤ ነገር ግን ሐዘንተኞቹ የደስታ መዝሙር እንዲዘምሩላቸው ይፈልጋሉ። ምን ጉዶች ናቸው!?
የእግዚአብሔር ሰዎች ሐዘን ውስጥ ሆነው “አፌን ሣቅ ሞልቶታል” በማለት እንዲዘምሩ የሚጠብቁ ሰዎች ዛሬም በዙሪያችን ሊኖሩ ይችላሉ። መጽሐፈ ምሳሌ 25፥20 ለዚህ የሚሆን መልእክት አለው፤ “ለሚያዝን ልብ ዝማሬ የሚዘምር፣ ለብርድ ቀን መጎናጸፊያውን እንደሚያስወግድ፣ በቁስልም ላይ እንደ መጻጻ እንዲሁ ነው።" አዲሱ መደበኛ ትርጉም እንዲህ ይለዋል፤ “ላዘነ ልብ የሚዘምር፣ በብርድ ቀን ልብሱን እንደሚያወልቅ፣ ወይም በሶዳ ላይ እንደ ተጨመረ ሆምጣጤ ነው።" እናም ላዘነ ሰው የደስታ መዝሙር መዘመር በብርድ ሰዓት ልብስን እንደ ማውለቅ ነው። የደስታ መዝሙር ለሐዘን ወቅት አይሆንምና!
ታዲያ በእንዲህ ዐይነት ወቅት ምን ዐይነት ዝማሬ ነው የሚዘመረው? ሰቆቃወ ኤርምያስን ማንበብ ነዋ! መዝሙረ ዳዊትም ለዚህ የሚሆኑ ምዕራፎች አሉት። ለእስራኤላውያኑ የሙሾ ወቅት ነበርና የሐዘንና የዋይታ ሙሾ ነበር የሚያስፈልጋቸው። ከዚህ በፊት፣ በሰቆቃወ ኤርምያስ ላይ አንድ መልእክት ሳቀርብ አቅርቤው የነበረውን ጥያቄ ደግሜ አቀርባለሁ። አገር በጣር ውስጥ፣ በታላቅ ሐዘን ውስጥ ስታልፍ የምንዘምረው መዝሙር አለን? ሙሾ አለን? ጌታችን በመስቀል ላይ ሆኖ መዝሙር 22ን ይጠቅስ ነበር። ነቢዩ ኤርምያስ ሰቆቃወ ኤርምያስን ነበር ያዜመው፤ ይህም ሙሾ ነው።
እኛስ? እንደ ቤተሰብ፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ አገር ለሐዘን ጊዜ የሚሆን ምን ያህል ሙሾ አለን? ወይስ ሁሌም መዝሙራችን “አፌን ሣቅ ሞልቶታል” ነው?
https://t.me/PaulosFekadu
460 viewsedited 14:19