Get Mystery Box with random crypto!

የተንዚህ መከታ ተጨባጭ መረጃ መሰረታዊ ግንዛቤ እና እውነታ፣ ክፍል 6 | የ ኡስታዝ ሀቢብ ኑሩ የድምፅ ፋይሎች

የተንዚህ መከታ ተጨባጭ መረጃ
መሰረታዊ ግንዛቤ እና እውነታ፣
ክፍል 6
==========

በዐረብኛ ቋንቋ "ኢስተዋ"
የሚለው ቃል
ትርጉም
"ኢስተዋ" የሚለው ቃል በዐረብኛ ቋንቋ የተለያዩ ትርጉሞችን ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ገመናቸው የማይወጣ መስሏቸው ወሀቢያዎች ይህ ቃል አንድ ትርጉም ብቻ ነው ያለው እያሉ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ መስተዋሉ ነው፡፡ እስቲ ይህ አባባላቸው ውድቅ እንደሆነ ለማሳየት ያክል ብቻ ከትርጉሞቹ መካከል የተውሰኑትን ለመመልከት እንሞክር
መመቻቸት ወይም
መደላደል
አሏህ በቁርአን ላይ የነቢዩሏህ ኑህን(ዐለይሂሰላም) መርከብ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል
"واستوت على الجودي" سورة هود:٤٤
ትርጉም "(የነቢዩሏህ ኑህ መርከብ) ጁዲይ በሚባል ተራራ ላይ ተደላደለች"(ሱረቱ ሁድ፥44)
የዐረብኛ ቁንቋ ምሁራን እንደተናገሩት አንድ ሰው ከመጓጓዣው ጀርባ ላይ "ኢስዋእ አደረገ" ከተባለ ተደላደለ ማለት ነው
ልብ ይበሉ፡- እንግዲህ ወሀቢያዎች አሏህን ዐርሽ ላይ ተደላደለ እያሉ መግለጻቸው አሏህ በቁርአን ላይ መርከቧን የገለጸበትን ባህሪ ለአሏህ እየሰጡ ነው ታዲያ ይህ እምነት ተሽቢህ(አሏህን ከፍጡራን ጋር ማመሳሰል) ካልሆነ ተሽቢህ(አሏህን ከፍጡራን ጋር ማመሳሰል) ማለት ምን ማለት ሊሆን ነው!?
ታዲያ አሏህ በቁርአን ላይ
ليس كمثله شىء
ትርጉም "እርሱን (አሏህን) የሚመስል ምንም ነገር የለም"(ሱረቱ ሹራ፥11) ብሎ ማንንም ምንንም እንደማይመስል ከመናገር በላይ ምን ብሎ ቢነግራቸው ይሆን አሏህን ከፍጡራን ጋር ከማመሳሰል የሚቆጠቡት አሏህ ይጠብቀን
መስተካከልና ቀጥ ማለት
አሏህ እንዲህ አለ
فاستوى على سوقه سورة الفتح:٢٩
ትርጉም " (አዝርኢቱ) በአገዳው ላይ ቀጥ ባለ እና በተስተካከለ ጊዜ"(ሱረቱ አል-ፈትህ፡29) በዚህ የቁርአን አንቀጽ ላይ "ኢስተዋ" የሚለው ቃል "ቀጥ አለ፥ተስተካከለ" የሚል ትርጉም ይዞ ነው የመጣው!
ታላቁ የተፍሲር ምሁር አቡ ሀያን አል-አንደሉሲይ "አል በህሩል ሙሂጥ" በተሰኘው የተፍሲር ኪታባቸው እንዲህ ብለዋል "(እዚጋ) ኢስተዋ ማለት አዝርኢቱ አገዳው ላይ እድገቱ ሞልቶ በቆመ ጊዜ ማለት ሲሆን 'ሱቅ' የሚለው ደግሞ 'ሳቅ' የሚለው የዐረብኛ ቃል ብዙ ቁጥር አመልካች ሲሆን ስሩ ለማለት ነው"(አል በህሩል ሙሂጥ ክፍል 8/ገጽ 103)
በይዷዊይ የተባሉት የተፍሲር ምሁር ደግሞ "አንዋሩ አል-ተንዚል" በተሰኘው የተፍሲር መጽሀፍቸው እንዲህ ብለዋል "(ኢስተዋ) ማለት አዝርኢቱ አገዳው ላይ ቀጥ ባለ ጊዜ ማለት ነው"(አንዋሩ አል-ተንዚል 5/86)
ነሰፊይ የተባሉት የተፍሲር ምሁርም እንዲሁ በተፍሲር መጽሀፋቸው (4/64) ላይ ተመሳሳይ ነገር አስፍረዋል፡፡
ታዋቂው የተፍሲር ምሁርም ኢማም አል-ቁርጡቢይ በተፍሲር ኪታባቸው 16/295 ላይ ተመሳሳይ ትርጉም አስቀምጠዋል፡፡
ታላቁ የቋንቋ ምሁር ኢብኑ መንዙር ደግሞ "ሊሳኑል ዐረብ" በተሰኘ መጽሀፋቸው እንዲህ ብለዋል "አንድ ነገር ኢስተዋ ከተባለ ተስተካከለ ለማለት ይሆናል"(ሊሳኑል ዐረብ 14/414)
ሱብሀነሏህ! እነዚህ ሁሉ ዑለማኦች እንግዲህ ኢስተዋ የሚለው ቃል ቀጥ ማለትና መስተካከል በሚል ትርጉም እንደሚመጣ እየተናገሩ ወሀቢያዎች ግን አንድ ትርጉም ብቻ ነው ያለው እያሉ አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ፡፡ ለነገሩ ማገናዘብ አለመቻላቸው እንጅ አንድ ኢማም ወደ ሶላት
ከመግባቱ በፊት ሰዎቹ ሶፋቸውን እንዲያስተካክሉ ሲያስታውሳቸው "ኢስተዉ" አይደለም እንዴ የሚለው ጉድ በነሱ አባባል እንግዲህ ኢስተዋ ማለት መደላደል የሚል ትርጉም ብቻ ቢኖረው ሰጋጆች ተስተካክለው በመቆም ፋንታ ተደላድለው ይቀመጡ ነበር አቤት ውርደት
መሙላት
ሌላኛው "ኢስተዋ" የሚልው ቃል ትርጉም "ሞላ" ማለት ነው፡፡አሏህ እንዲህ አለ
ولما بلغ أشده واستوى سورة القصص:١٤
ትርጉም "(ነቢዩሏህ ሙሳ) አካላዊ ጥንካሬያቸው በሞላ ጊዜ"(ሱረቱ አል-ቀሶስ፥14)
ታላቁ የቋንቋ ምሁር ፈይሩዛባዲይ "በሷኢሩ ዘዊ አል-ተምዪዝ" በተሰኘ መጽሀፋቸው እንዲህ ብለዋል
"ولما بلغ أشده استوى"
ማለት ጠነከረ ፥በረታ ማለት ነው"(በሷኢሩ ዘዊ አል-ተምዪዝ 2/106)
ተቆጣጠረ
ታላቁ የቋንቋ ምሁርና 237ተኛው አመተ ሂጅሪያ ያለፉት ዓሊም ዐብዱሏህ ኢብኑ የህያ ኢብኑል ሙባረክ "ገሪቡል ቁርአኒ ወተፍሲሩሁ" በተሰኘ መጽሀፋቸው እንዲህ ብለዋል الرحمن على العرش استوى
" ማለት ተቆጣጠረ ማለት ነው"(ገሪቡል ቁርአኒ ወተፍሲሩሁ ገጽ 113)
በተመሳሳይ 333ተኛው አመተ ሂጅሪያ ያለፉት የአህሉሱና መሪ የሆኑት አቡ መንሱር አል ማቱሪዲይ "ተእዊላቱ አህሊሱና" በተሰኘው መጽሀፋቸው እንዲህ ብለዋል الرحمن على العرش استوى
ማለት ዐርሽን ተቆጣጠረው ማለት ነው" (ተእዊላቱ አህሊሱና 1/85)
ያስተውሉ፡- ወሀቢያዎች እንግዲህ ከነዚህ ታላላቅ ዑለማኦች እንበልጣለን ብለው ነው ማለት ነው ኢስተዋ የሚለው ቃል ኢስተውላ(ተቆጣጠረ) በሚለው ትርጉም ሊመጣ አይችልም እያሉ ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ የሚደመጠው
"ኢስተዋ" የሚለው ቃል "ኢስተውላ(ተቆጣጠረ)" በሚለው ትርጉም እንደሚመጣ የተናገሩትን ዑለማኦች በዚች አጭር ጹሁፍ መጨረስ ቀርቶ ማጋመስ እንኳ አይቻልም፡፡ የተጠቀሰውም ግን በትክክል ማገናዘብ ለሚችል በቂ ነውና አሏህ ሰፊ ግንዛቤን ይስጠን እያልኩ ለዛሬው በዚህ አበቃሁ
ወሰላሙ ዐለይኩም ወረህመቱሏሂ ወበረካቱህ
••••••••••••••••••••••••••••••••••••
ዒልሙዲን ኢስላማዊ ስቱድዮ
ክፍል 6
https://t.me/elmudinIslamicstudio/13761