Get Mystery Box with random crypto!

ኒው ዮርክ የሰው ልጅን አስክሬን ወደ ብስባሽ አፈር መቀየር የሚፈቅድ ሕግ አጸደቀች። ይህን ተከት | Our World

ኒው ዮርክ የሰው ልጅን አስክሬን ወደ ብስባሽ አፈር መቀየር የሚፈቅድ ሕግ አጸደቀች።

ይህን ተከትሎ ሰዎች ሲሞቱ አስክሬናቸው ወደ ብስባሸ አፈርነት እንዲቀየር መናዘዝ ይችላሉ።

አስክሬንን በሳጥን አኑሮ ግብዓተ መሬቱን መፈጸም ወይም ሬሳን ማቃጠል ለአካባቢ ጥበቃ መልካም አይደለም ይላሉ ተመራማሪዎች።

ይህን ችግር ለመቅረፍ አዲስና ዘመናዊ የሬሳ ማስወገጃ ሥራ ተግባር ላይ ማዋል አስፈልጓል።

በእንግሊዝኛው ናቹራል ኦርጋኒክ ሪዳክሽን ("natural organic reduction") የሚባለውና አስክሬንን ወደ ብስባሽ አፈር የሚቀይረው ይህ ዘመናዊ ሂደት ሬሳዎችን አሽጎ በማቆየት የሚፈጸም አካባቢን የማይበክል ሂደት ነው ይላሉ ተመራማሪዎች።

ከአራት ዓመት በፊት ዋሽንግተን ተመሳሳይ ደንብን ሕግ አድርጋ አጽድቃ እንደነበር ይታወሳል።

ኮሎራዶ፣ ኦሪገን፣ ቬርሞንት እና ካሊፎርኒያ ዋሽንግተንን ተከትለው ይህንን ሕግ አጽደቀዋል።

ኒው ዮርክ አስክሬንን ወደ ብስባሽ አፈርነት መቀየር የሚፈቅድ ሕግ ስታጸድቅ ስድስተኛዋ የአሜሪካ ግዛት ናት።

ይህን ረቂቅ የኒው ዮርክ ገዥ የሆኑት ዲሞክራቷ ካቲ ሆኩል ሕግ እንዲሆን ፈርመውበታል።

ይህ ሬሳን ወደ ብስባሸ የሚቀይረው ሳይንስ ከመሬት ከፍ ብሎ በሚቀመጥ የሳጥን በርሜል የሚፈጸም ነው።

አስክሬኖች ዝግ በሆነ በርሜል መሰል ማስቀመጫ ከተጋደሙ በኋላ የእንጨት ፍቅፋቂ፣ ሳር፣ አፈርና እና ሌሎች ንጥረ ነገሮች ይርከፈከፉባቸዋል። ከዚያ አስክሬን አብሮ ይቀየጣል።

ማንኛውም ተላላፊ በሽታ እንዳይኖር ከፍ ያለ ሙቀት ይደረግበታል።

ከአንድ ወር በኋላ ብስባሽ አፈር ሆኖ ለቤተሰብ ይሰጣል። ቤተሰብ ይህን አፈር ተቀብሎ ለጓሮ አትክልት ሊያውለው ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, RECOMPOSE/MOLT STUDIOS

ሪኮምፖስ የሚባል አንድ የአሜሪካ ኩባንያ እንደሚለው ይህ ሂደት የካርበን ልቀትን በብዙ ደረጃ ቀንሶ የአካባቢ ብክለትን የሚከላከል ሁነኛ ዘዴ ሲል አሞካሽቶታል።

የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት ለዓለም አየር ንብረት መለወጥ አንድ ሁነኛ ምክንያት ነው።

ይህም የመሬትን ከባቢ በማፈን ሙቀትን ስለሚፈጥር ነው።

ባሕላዊው ሬሳን የመቅበሪያ ዘዴ በርካታ ሳጥን መፈለጉና ለዚህም ሲባል በርካታ የደን ምንጣሮ ስለሚያስፈልግ ነው።

ከምንጣሮ ሌላ መካነ መቃብርም በርካታ ቦታ ይይዛል። በከተሞች አካባቢ ይህ ትልቅ ፈተና ሆኗል።

የዚህ ሬሳን ወደ ብስባሽ አፈርነት የመቀየር ሂደት ደጋፊ የሆኑ ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ዘዴ በተለይ መሬት ውድ ለሆነባቸው የዓለም ከተሞች ሁነኛ መፍትሄ ነው።

በተቃራኒው ሌሎች የሞራል ጥያቄን ያነሳሉ።

የኒው ዮርክ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቄስ “የሰው ልጅ ክቡር ነው፤ አስክሬኑ እንደቆሻሻ ብስባሽ አይደረግም፤ ነውር ነው’ ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ይህን ሬሳን ብስባሽ የማድረግ ሂደት ከተለመደው ቀብር የማስፈጸሚያ በዋጋ አነስተኛ ቢሆንም እስከ 7ሺህ ዶላር ወጪ ያስወጣል።

የሰውን አስክሬን ወደ ብስባሽ አፈር የመቀየር ሂደት በስዊድን ሕጋዊ ነው።

በዩኬ ደግሞ አስክሬንን ያለ ሬሳ ሳጥን መቅበር ይፈቀዳል።