Get Mystery Box with random crypto!

“ምናባዊ ንብረትን (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ | Our World

“ምናባዊ ንብረትን (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት ነው”:- ብሄራዊ ባንክ
ሰኞ ግንቦት 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ እንደ ክሪፕቶ ከረንሲ፣ ቢትኮይን እና የመሳሰሉ ምናባዊ ንብረትን (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ የገንዘብ መደብ ብር እንደሆነና በብሔራዊ ባንክ በሌላ አኳኋን ካልተፈቀደ በስተቀር በአገሪቱ የሚከናወኑ ማናቸውም የገንዘብ ግንኙነቶች ኹሉ የሚከፈሉት በብር እንደሚሆን የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 591/2000 በግልጽ እንደሚደነግግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።
በክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2003 መሠረት በየትኛውም የክፍያ መፈጸሚያ ሰነድም ሆነ ሥርዓት ያለ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ገንዘብ ነክ አገልግሎት መስጠት አይቻልም።
ነገር ግን ከጥናት ለመረዳት እንደተቻለው በአሁኑ ወቅት ከህግ እውቅና ውጪ የክሪፕቶ ከረንሲ፣ እንደ ቢትኮይን እና የመሳሰሉት የምናባዊ ንብረት (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብ) አገልግሎት በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መጥቷል ሲል ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል።
በተጨማሪም ይህ ተግባር ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ውጪ ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር የሚደረግበት እና በተለይም በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ለማሸሽ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል ነው ያለው ባንኩ።
ይህ እየተስተዋለ ያለው ምናባዊ ንብረትን (ዲጂታል መገበያያ ገንዘብን) ለግብይት ወይም ለክፍያ መጠቀም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ያልተሰጠው ድርጊት በመሆኑ ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ሕገ-ወጥ ተግባር እራሱን መጠበቅ ይኖርበታልም ብሏል።
በመሆኑም ይህን ፈጽመው በሚገኙ አካላት ላይ ብሔራዊ ባንክ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ የገለጸ ሲሆን፥ ህብረተሰቡም ይህንን ህገወጥ ተግባር የሚሠሩ አካላትን ሲመለከት ለብሔራዊ ባንክ እና ለሚመለከታቸው ሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪውን አቅርቧል።
_____