Get Mystery Box with random crypto!

ኢንዶሚ ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው በአገራችን በህጋዊ መንገድ ከውጪ አገር የሚገባ የኢንዶሚን ም | አገልግል

ኢንዶሚ ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው
በአገራችን በህጋዊ መንገድ ከውጪ አገር የሚገባ የኢንዶሚን ምርት የለም ተብሏል

በካንሰር የመያዝ እድልን የሚያስከትል ንጥረ ነገርን ይዟል በተባለው ኢንዶሚን ኑድልስ ላይ የተለያዩ አገራት ምርመራ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ማሌዥያና ታይዋን በኢንዶሚን ላይ “ኢቲሊን ኦክሳይድ” የተባለውን ካንሰር አምጪ ንጥረ ነገር በማግኘታቸው ምርቶቹን ከገበያ ላይ እንዲሰበሰቡ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን፣ በህጋዊ መንገድ ተመዝግቦ ከውጪ አገር የሚገባ የኢንዶሚን ኑድልስ ምርት አለመኖሩን አመልክቷል፡፡ የባለስልጣኑ ምግብ ተቋማት ቁጥጥር ሃላፊ አቶ በትረ ጌታሁን ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በባለስልጣኑ ተመዝግቦ በህጋዊ መንገድ ከውጪ አገር የሚገባ ኢንዶሚን የተባለ ምርት አለመኖሩን ጠቁመው፤ በአገር ውስጥ የሚመረትና በባለስልጣኑ ቁጥጥር የሚደረግበት ምርት አለ ብለዋል። ጉዳዩ እንደተሰማ በዚሁ የአገር ውስጥ ምርት ላይ ምርመራ መደረጉን የገለፁት ሃላፊው በምርቱም ላይ የተባለውን ዓይነት ለጤና ጎጂ የሆነ ንጥረ ነገር አለመገኘቱን አመልክተዋል፡፡ በካንሰር የመያዝ እድልን ያስከትላል የተባለውን ንጥረ ነገር ይዟል በተባለው የኢንዶሚን ምርት ላይ ምርመራ ማድረግ ከጀመሩ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ናይጄሪያ ስትሆን፤ ከኢንዶሚን ኑድልስ ምርት የተለያዩ ናሙናዎችንና ቅመማ ቅመሞችን በመውሰድ ኢቲሊን አክሳይድ የተባለው ንጥረ ነገር መኖር አለመኖሩን ለማወቅ ምርመራ እያደረገች መሆኑን አስታውቃለች፡፡በማሌዥያና ታይዋን ልዩ የዶሮ ጣዕም ባለው የኢንዶሚን ምርት ላይ ካንሰር አምጪው አደገኛው ንጥረ ነገር በመገኘቱ ምርቶቹ ከገበያ እንዲሰበሰቡ ተደርገዋል፡፡
ኢንዶሚን የተባለውን ኑድልስ የሚያመርተው የኢንዶኔዥያው ግዙፍ የምግብ አምራች ተቋም “ኢንዶፍድስ” የምግብ ምርቱ ጤናማ መሆኑን በመግለፅ እየተከራከረ ነው፡፡