Get Mystery Box with random crypto!

​​​​ቅድስት (የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት) «ቅድስት» ማለት የዘይቤ ፍችው « የተቀደሰች የተለ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

​​​​ቅድስት (የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት)

«ቅድስት» ማለት የዘይቤ ፍችው « የተቀደሰች የተለየች » ማለት ነው። ምስጢራዊ መልእክቱ ግን የምስጢረ አድኅኖት ታላላቅ ሥራውን ለመጀመር መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ከቆመ ሳያርፍ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ የጾማት የአርብዓው ቀንና ሌሊት ልዩ የሆነችና ክብርት ጾም የምትጀመርበትን ሁለተኛ ሳምንት ከልብ ያሳስበናል፡፡ ማቴ. 4-2

ቅድስት የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሰንበት ስያሜ ነው፡፡ ስያሜውም ከኢትዮያዊው የዜማ ሊቅ ከቅዱስ ያሬድ የተገኘ ነው። ከዚህ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን ታስተምርበታለች ፡፡

በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው ምስባክ ፤ የሚነበቡ መልዕክታት ፤የሐዋርያት ሥራ ና ወንጌል ስለ ቅድስት የሚያስተምሩ ናቸው፡፡

‹‹ቅዱስ›› ማለት ልዩ፤ ክቡር ማለት ነው፡፡እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ ቅዱስ ነው፡፡ ይህም ቅድስና ከማንም ያላገኘው የባሕርይ ገንዘቡ ነው። መጻሕፍትም የባሕርይ ቅድስናውን ተባብረው መስክረዋል፡፡ ባባሕርዩ ቅዱስ ስለሆነ ‹‹ቅዱስ፡ቅዱስ፡ቅዱስ›› እየተባለ ይመሰገናል፡፡ ( ኢሳ 6፡1-3፤40፡25 ራዕ 15፡4 ፤ 1ሳሙ2፡2-3፡፡) እኛም ቅዱስ ልጁ በሥጋ ተገልጦ እንዳስተማረን በየዕለት ጸሎታችን ‹‹ስምህ ይቀደስ›› እንለዋለን፡፡

የቅድስና ምንጭ ፡ ቅድስናን የሚሰጥ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ‹‹ ቅዱስ ›› የሚለው ቃል ለሰዎች ፡ለመላእክት ፡ ለቦታ ፡ለዕቃ: ለዕለታት … ቢቀጸልም ቅድስናቸው በባሕርይው ቅዱስ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተገኘ ነው፡፡ ይህም የጸጋ ቅድስና ይባላል፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ በመልኩና በምሳሌው አክብሮ የፈጠረንን እኛም ቅዱሳን እንድንሆን ይፈለጋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁን›› ተብሎ ስለተጻፈ የጠራቸው ቅዱስ እንደሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ ›› ያለንም
ይህንን ሲያስተምረን ነው። ከመፈጠራችን አስቀድሞ መጠን በሌለው ፍቅር የወደደን እግዚአብሔር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣን ፤ ለውርደት ሳይሆን ለክብር፤ ለርኩሰት ሳይሆን ለቅድስና፤ ለሞት ሳይሆን ለሕይወት ነው፡፡ የመፈጠራችንም ዓላማ በፊቱ በፍጹም ምግባርና ሃይማኖት በመመላለስ ከእርሱ ጋር እንድንኖር ነው፡፡ ብርሃን ከጨለማ፡ ጽድቅ ከኃጢአት፡ ጋር ኅብረት የለውምና ከእርሱ ጋር ለዘላለም ነግሰን ለመኖር በቅድስና መኖር ይጠበቅብናል፡፡

ቅድስናችን በኑሮአችን ሁሉ እንዲሆን ታዘናል (1ጴጥ1፡15)፡፡ ስለዚህ በተሰማራንበት የሥራ መስክ ፣ በማኅበራዊ ኑራአችን ፣በምንበላው ምግብ ፣በምንለብሰው ልብስ ፣ በንግግራችንና በመሳሰለው ሁሉ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኘውን በማድረግ እግዚአብሔርን በሚሞት ሥጋችን እናክብረው፡፡ ‹‹እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ የኃጢአትንም ጭንቀት ከእኛ አስወግደን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስት እንሩጥ፡፡

የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን እንከተለው፤ እርሱ ነውርን ንቆ ፣ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል ›› ተብሎ እንደተጻፈ ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ ተጋድሎ አድርገን ከኃጢአት ርቀት በቅድስና እንድንኖር ይገባናል (ዕብ 12፡1)።

ሥጋዊ ምኞታችንንና መሻታችንን ሰቅለን አሮጌው ሰዋችንን አስወግደን ንስሐ ገብተን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን በቅድስና እንድናኖር ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur