Get Mystery Box with random crypto!

ጥምቀት ምንድን ነው? ተወዳጆች የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንኳን ለጌታ | ዝማሬ ዳዊት - Zimare Dawit

ጥምቀት ምንድን ነው?

ተወዳጆች የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንኳን ለጌታችንና ለአምላካችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ እያልን ነገረ ጥምቀቱን እንዲህ መናገር እንጀምራለን

ጥምቀት በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒያ በግእዝ አስተርዮ በአማርኛ መገለጥ ይባላል።

ጥምቀት “አጥመቀ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ፍቺውም በገቢር መንከር፣ መድፈቅ፣ መዘፈቅ፣ በተገብሮ መነከር፣ መደፈቅ፣ መዘፈቅ፣ መላ አካልን በውኃ ውስጥ ማስገባት ማለት ነው።

በሌላ አገላለጽ ጥምቀት ማለት በተጸለየበት ወይም በተለየና በከበረ ውኃ (ማየ ገቦ ወይም ማየ ሕይወት) ውስጥ በሥላሴ (በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ) ስም ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር መጥለቅ፣ መዘፈቅ፣ መነከር ማለት ነው። በመሆኑም የምንጠመቅበት ውኃ ተራ ውኃ አይደለም።

ጥምቀት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አንዱ ነው።

የጥምቀት በዓል ከዘጠኙ የጌታ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ ነው

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓተ አክብሮት መሠረት በየዓመቱ ከጥር አሥር እስከ አሥራ አንድ ቀን በደማቅ ሥነ ሥርዓት በካህናት፣ በምዕመናንና በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አገልግሎት ይከበራል።

በዓሉ የሚከበረው ጌታ በዕደ ዮሐንስ በማየ ዮርዳኖስ የተጠመቀበት ምሥጢረ ጥምቀትና ሥርዓተ ጥምቀትን የመሠረተበት ዕለት በመሆኑ ነው። ጌታ የተጠመቀው በተወለደ በሠላሳኛው ዓመት ሲሆን ያ ወራት ዮሐንስ መጥምቁ ሕዝቡን እየሰበሰበ የንስሐ ጥምቀት የሚያጠምቅበት ጊዜ ነበር:: ማቴ. 3:1

ታሪካዊ የጥምቀት በዓል አከባበር በኢትዮጲያ

ታላቁ የከተራ እና የጥምቀት በዓል ሲነሳ ኢትዮጵያውያን ሩቅ ዘመንን ተሻግረን የቅዱሳን ሰማዕት አባቶችን፣ የሊቃውንት አባቶችን አስተምሮት እናዘክራለን።

በቅዱስ ላልይበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውና እና በስብከተ ወንጌል ያገለግሉ የነበሩት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በመቐለና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል።

በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት (1260-1275 ዓ.ም) በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (1203-1204 ዓ.ም) አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዐተ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዐዋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና እንክብካቤ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ ወስነዋል።

የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና አድማሱ ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ።

ከዐፄ ገብረ መስቀል ጀምሮ የአደባባይ በዓል የሆነው የጥምቀት በዓል በ15ኛው ክ/ዘመን በደገኛው ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1426-1460 ዓ.ም) አማካኝነት ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ፣ አገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ ወሰኑ።

ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ (1486-1500) ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበት እና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት timqet celebration በዐዋጅ አስነግረው ነበር።

ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ካወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ጀመረ ።

ኢትዮጵያ ዜና ጥምቀተ ክርስቶስን ከሰማችበት ከመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን አንሥቶ በተለይም ከአጤ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት (6ኛው መ/ክ/ዘ) ወዲህ የጥምቀትን በዓል ዛሬ በሚታየው አኳኋን ስታከበር እንደ ቆየች ይታመናል።

በክብረ በዓሉ ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው ወደ ባሕረ ጥምቀት የሚወርዱት ታቦታት በካህናቱ ሃሌታ፣ በምእመናኑ እልልታ እና በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያኑ በተቋቋሙ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች መዝሙሮች ታጅበው በተመሳሳይ አኳኋን እንደሚመለሱ ይታወቃል።

እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን።

መዝሙረ ዳዊት ፻፶፥፮

ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል። የታቹም ወደ ታች ሸሽቷል። የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደ ክምር ተቆልሎ ቀርቷል።

ቅዱስ ዳዊት የተመለከተውም ይህንኑ ነው።

ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ፤ የታቹም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም የመጥፋቱ ምሳሌ ነው።

እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ መሔዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከኃጢአት ቍራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት ወደ ዕረፍት መንግሥተ ሰማያት አቅንተው ለመሔዳቸው ምሳሌ ነው።

ኢያሱ የጌታ፣

እስራኤል የምእመናን፣

ዮርዳኖስ የጥምቀት፣

ምድረ ርስት የገነት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው።

ታቦቱን አክብሮ የሚሔደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣

ታቦቱ የጌታችን፣

ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝ፣

ታቦታቱን አጅበው የሚሔዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው።

ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸውና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያጠይቃል።

‹‹ጥምቀት የሞቱና የትንሣኤው ምሳሌ ነው።

ከኃጥአን ጋር ተቆጥሮ እንዲጠመቅና እንዲሰቀል የተጻፈውን ቃል ንስሐና ጥምቀት የማያስፈልገው ሲሆን ነገር ግን ፍጹም ኃጥእ መስሎ በዮሐንስ እጅ ጥምቀትን ለመፈጸም በማየ ዮርዳኖስ እግር ተጠመቀ።››።

ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያን ዘንድ የዝናብ፣ የበረዶ ወራት ነው። ከወንዝ ዳር ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም። በመኾኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር። በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ ድንኳኖች ዳሶች ይጣላሉ።

በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በአክሱም የንግሥት ሳባ መዋኛን ‹‹ማይ ሹም›› በጎንደር የዐፄ ፋሲል መዋኛን፣ በላስታ የላሊበላ መዋኛን፣ በሸዋ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይን፣ አርባ አራት ታቦታት የሚያድሩበትን የሸንኮራ ሜዳን “ራቡቴ ወንዝ” በአዲስ አበባ ደግሞ ጃንሆይ ሜዳን /ጃንሜዳን/ ወዘተ ለአብሕርተ ምጥማቃት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። እኒህ ቦታዎች ዛሬም ድረስ ተከብረው ይገኛሉ።

እኛ በዚህ ወቅት ታቦት ይዘን፣ ከወንዝ ወርደን፣ ድንኳን ተክለን በማክበራችን ይፈጸማል፡፡

@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur
@ortodoxmezmur