Get Mystery Box with random crypto!

+++ 'ክረምትን ለምን ፈራሁ?' +++ በጋና ክረምትን እያፈራረቀ የሰውን ልጅ ሁሉ የሚመግብ እ | ኦርቶዶክሳዊ አእምሮ

+++ "ክረምትን ለምን ፈራሁ?" +++

በጋና ክረምትን እያፈራረቀ የሰውን ልጅ ሁሉ የሚመግብ እግዚአብሔር ነው። በክረምት ገበሬው ይዘራል፣ እግዚአብሔር ደግሞ ከሰማይ ጠሉን ይልክለታል። በክረምቱ ጊዜ ተዘርቶ ያደገው ሰብል እንዲበስል ፈጣሪው የበጋውን ፀሐይ ያወጣለታል። ትጉሁ ገብሬም የደረሰውን አዝመራ ሊሰበስብ በበጋው ማጭዱን ይዞ ይታያል። ክረምት ለገበሬው የሥራ ጊዜ ነው።

ለእኔ ግን ክረምት ያስፈራኛል። እንዳልጽፍ እጆቼ በብርዱ ቆፈን ይያዛሉ፣ እንዳላነብ አይኖቼ በእንቅልፍ ሽፋሽፍት ይፈዝዛሉ። ማልጄ በቤቴ መስኮት የማያት ፀሐይ በደመና ስትሸፈን ቀኑ የጀመረ ሌሊቱም የነጋ አይመስለኝ። ከአልጋዬ ተነሥ ተነሥ አይለኝም።  ውጪው ሲጨልም ቤቴም ይደበዝዝብኛል። ወጥቼ ሥራዬን እንዳልሠራ፣ ከወዳጆቼ ጋር ተገናኝቼ እንዳላወጋ ዝናቡ አላላውስ ይለኛል። ለእኔ ክረምት ያስፈራኛል።

ግን ለምን ክረምትን ፈራሁት? እንደ ገበሬው የዝናብን በረከት ማየት ስላቃተኝ ይሆን? ወይስ የምዘራው ዘር በእጄ ስለሌለ? እንዲጸድቅ የምፈልገው ተክል፣ ልምላሜውን ማየት የሚያጓጓኝ እጽ የለኝ ይሆን?

በሥራ እና በግል ጉዳዮቼ ተጠምጄ ከራቅኋቸው ከቤቸሰቦቼ ልብ ላይ የምዘራው ብዙ የፍቅር ዘርማ አለኝ። በሰዎች ሆታ እና ጩኸት ስከበብ የዘነጋሁት በመልካም ሰብእና እንዲጸድቅና እንዲለመልም የምፈልገው እኔነት አለኝ። ታዲያ ለራሴ የሚሆን በቂ ጊዜ አግኝቼ ውስጤን አርስ፣ እመረምርና አለሰልስ ዘንድ ክረምት የመጣው፣ ዝናቡስ የዘነበው ለእኔ ብሎ አይደል?

ለካ የብርዱ ቆፈን የበረታብኝ፣ የአይኖቼ ሽፋሽፍት በእንቅልፍ የደከሙብኝ ክረምትን ስለማልወደው ሳይሆን የክረምትን በረከት ማስተዋል ስላልቻልኩ ነው። ለካስ ክረምቱ የደበተኝ "ደግሞ ሊመጣ ነው" ብዬ ቀድሜ ስላወገዝኩትና ራሴን ለሥራ ስላላዘጋጀሁ ነው። ሰማዩ ሲደምን እና ዝናቡ አላስወጣ ብሎ ሲዘንብ በእኔ ውስጥ ያለችውን ፀሐይ ፈልጌ እንድገልጣት እድል እየሰጠኝ ነው። ክረምት የደረቀው እጽ መልሶ የሚያቆጠቁጥበት ብቻ ሳይሆን ያረጀውና ሊወድቅ ያዘመመው ውስጤ የሚታደስበትና የሚጠገንበት ጊዜ ነው። ለካስ ክረምት ለገበሬ ብቻ የመሰለኝ ስህተት ነው። ክረምት ለእኔም ነው!

(ክረምት ሲገባ እና ፀሐይ አዘውትራ መታየት ስታቆም ከዚህ ጋር ተያይዞ  "Seasonal affective disorder" የተባለ ድባቴ ውስጥ ለሚገቡ ሁሉ መታሰቢያነት የተጻፈ)

ዲያቆን አቤል ካሳሁን
ሰኔ 26፣ 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero