Get Mystery Box with random crypto!

ብቻቸውን ሲኖዶስ የነበሩት ብፁዕ አባታችን፦ ከ1960 መባቻ እስከ 1998 ዓ.ም የካሪቢያንና | ኦርቶዶክሳዊ አእምሮ

ብቻቸውን ሲኖዶስ የነበሩት ብፁዕ አባታችን፦

ከ1960 መባቻ እስከ 1998 ዓ.ም የካሪቢያንና ጃማይካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል።
ከመደበኛ ሀገረ ስብከታቸው ውጭ ያጠመቁት ሕዝብ ሳይቆጠር፥155 ሺህ ምእመናናንን አስተምረው አጥምቀው አቁርበዋል። ከሰባ በላይ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸዋል።
'የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ' እንዲሉ ካስተማሩት ሕዝብ አብራክ የተገኙ 300 የሚሆኑ መምህራንን በክህነትና ስብከተ ወንጌል እንዲያገለግሉ አሠልጥነው ሾመዋል።
ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ፥ ብቻቸውን ሲኖዶስ የነበሩ አባት!

ሰሞኑን ባነበብኩት ጽሑፍ፥ ማኀበረ ቅዱሳን እንኳ እንደ ግዙፍ ተቋምነቱ፣ እንዳለው የሰው ኀይልና የተሻለ አደረጃጀት፥
እስከአሁን ባለው አገልግሎቱ ወደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የሰበሰባቸው ነፍሳት 350 ሺህ ናቸው።
ሆኖም፥እኛን በበላይነት ከሚመራን ተቋም አንጻር፥ የተቀመጠና የሚሮጥ ሰውን ያህል ልዩነት አለን።
እንደ ተቋም፣ የጠፉትን መፈለግ፣ የአሉትን አማኞች ማጽናት የተተወ ነገር ሆኗልና።
ተቋሙ ከመሠረታዊው የክህነት አገልግሎት አፈንግጦ፤ በግለሰባዊና ቡድናዊ ትብትቦች የሚያባክነው ዘመን ያሳዝናል።

ለዚህ አይነቱ ተቋማዊ ድንዛዜ፥ ፍቱን መፍትሔ የሚሆን አምጦ መውለድ ነው።
ቤተክርስቲያን እንደ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ያሉትን አምጣ ካልወለደች የወላድ መካንነቷ ይቀጥላል።
እንደ እርሳቸው ያሉትን አባቶች ሲሾሙ ማየት ያልቻልን፥ሰዎቹ ስለሌሉ አይመስለኝም፤ ስላልቀረቡ እንጂ።
አዎ! እነሱ ራሳቸውን ለቤተክርስቲያን የሠጡ እንጂ ቤተክርስቲያንን ለራሳቸው የቀሠጡ አይደሉም።
እናም ቤተክህነቱን ለሥልጣን ደጅ አይጠኑም፤አሹሙን እያሉ በብፁዓን አባቶች ደጅ አይኳትኑምና ብዙ አናውቃቸውም።

የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ ከወንዝ አልፎ ውቅያኖስን ተሻግሮ እንደ ቀድሞው በክብርና በሞገስ ይቀጥል ዘንድ
ይስሐቆችን ለሹመት አምጦ መውለድ የብፁዓን አባቶች ድርሻ ብቻ አይደለም። ምእመናን መምህራን ሁሉ ድርሻ አላቸው።


(ሊቀ ሊቃውንት ስሙር አላምረው)

https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero
https://t.me/OrthodoxAmero