Get Mystery Box with random crypto!

#ለምስጋና_ተመለሱ “ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን ? ዘጠኙስ ወዴት አሉ ? ከዚህ ከልዩ ወገ | Apostolic Church of Ethiopia (የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን)

#ለምስጋና_ተመለሱ
“ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን ? ዘጠኙስ ወዴት አሉ ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ ። ” ሉቃ. 17፡17-18 ።የለምጽ በሽታ እንደ ዛሬው ያለ የቆዳ በሽታ አልነበረም ። የመጀመሪያ ተላላፊበሽታ ነው ። ሁለተኛ ከርኩሰት ጋር የተያያዘ ነው። ለምጽ ያለበት ሰው በካህኑ አዋጅ ራሱን ከሕዝቡ ለይቶ በምድረ በዳ ይኖራል ። ከተፈወሰ ሲመለስ ፣ ካልተፈወሰ በዚያው ይሞታል። የሚወዳቸው ቤተሰቦቹም ቤዛ ሊሆኑለት አይችሉም ። “ርኩስ ነኝ” ብሎ በራሱ ላይ ያውጃል ፣ ሰው ከቀረበውም እየሮጠ ይሸሻል ። ከባድ ጭንቅ ነው ። ጌታችን በሰማርያ ሲያልፍ አሥር ለምጻሞችን በምድረ በዳ አገኘ ። እነዚህ ለምጻሞች
ያገናኛቸው ኑሮ ሳይሆን ችግር ፣ ከተማ ሳይሆን ምድረ በዳ ነው ። ሐኪም ቤትና ስደት ያፋቅራል ።ችግሩ ያ ሲያልፍ መረሳሳት ይመጣ ይሆናል ። የችግር ቦታዎች ጥላቻና ራስ ወዳድነት የሚገረዝባቸው የግርዛት ኮረብታዎች ናቸው።ጌታችንን ባገኙት ጊዜ አልሮጡም ፣ እንደውም እየጮኹ ቀረቡት ። እርሱ የሚያነጻ ነውና ርኩሶችን አይሸሽም ። የሰው ቅድስና ግን ከራሱ አልተርፍ ስትል መሸሽ ይጀምራል ። “ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን አሉት ። ማረን ቢበድሉም ባይበድሉም ትልቅና የመጨረሻ ጸሎት ነው ። ቢታመሙም ባይታመሙም ሐኪም ጋ መሄድ መልካም ነው ። ስለ መፈወስ ቢለምኑ አንድ ልመና ነው ። እርሱ ከማራቸው ግን ሁሉም ጸጋ የእነርሱ ነው ። ማረኝ የጸሎት አባ ጠቅል ነው ። ምሕረት ያለውን ጌታ ማረኝ አሉት ። ማረኝ የሚባልም እርሱ ብቻ ነው ። ሰው ይቅር ይላል ፣መማር ግን የአንድ አምላክ ግብር ነው። ሰው ይተዉልናል ፣ እግዚአብሔር ግን እንዳልበደለ አድርጎ ይቀበለናል ። ጌታችን “ራሳችሁን ለካህን አሳዩ” አላቸው ። ለምጻም ናችሁ ብሎ ያረጋገጠውና በአዋጅ የለያቸው ካህኑ ነውና የሚመልሳቸውም ካህኑ ነው። ፈውሱን ጌታ አደረገና አዋጁን ግን ለባለሥልጣኑ ካህን ተወለት ። እግዚአብሔር ራሱ የሠራውን ሥርዓት ራሱ አያፈርስም ። “እነሆም ሲሄዱ ነጹ” ይላል ። በጣም ድንቅ ነገር ነው ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ ጌታችንን ሊያመሰግን ወደ ኋላ ተመለሰ ። ሌሎቹ ግን ቤተሰቦቻቸውንና የተለዩትን መንደር ለማግኘት ገሰገሱ ። አንገታቸው ወደፊት እንጂ ወደኋላ ዞር ብሎ የሚያይ አልነበረም ። ይህ አንዱ ሰው በጌታ እግር ላይ ወድቆ ማመስገን ጀመረ።ያ ሰው ግን የተናቀ ሳምራዊ ነበረ ። ከተናቀው ሰው የከበረ ምስጋናና ውለታ አክባሪነት ወጣ ። በማይጠበቅ ቦታ የማይጠበቅ ግብር ይገኛል። ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ብዙ አሉ ፣ ይህ ሰው ግን በቀትር የዘነበ ምስጋና አለው ። ድብልቅ ከሚባል ሕዝብ የጠራ ምስጋና ወጣ። ወገኑ ሳምራዊ ሳለ እንዴት አብሯቸው ከረመ ብንል የከፋ ችግር የሚያንሰውን ዘረኝነት አስረስቷቸው ነው ። በዘረኝነት የሰከሩ የባሰ ችግር ሲመጣ ይረሱታል ። “እዬዬ ሲዳላ ነው” ይባላል ። ሰው በጦርነት መሐል ልቅሶ አይቀመጥም ። ተደላድሎ ሲቀመጥ ግን ስለሞተው ወንድሙ ማልቀስ ይጀምራል ። ካልበሉ እንባም አይመጣም ። “ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን ? ዘጠኙስ ወዴት አሉ ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ ።” ለምስጋና የሚመለስ ከአሥር አንድ መሆኑ ይገርማል ። ዘጠኙ ተፈውሰዋል
ውለታው የነካው ግን አንዱ ነው ። ዛሬም ከአሥሩ አንዱ ብቻ ለምስጋና ይመለሳል ። እነዚያ ዘጠኙ የገሰገሱት ግን ወደ ሚያልፉት ወዳጆቻቸው ነው። ደግሞም ርኩስ ብላ ወደ ገፋቻቸው ዓለም ነው ። ዛሬም ሰዎች ሲፈወሱ ወዳወገዘቻቸው ዓለም ይመለሳሉ ። ለምስጋና የሚመለሱ ጥቂቶች ናቸው ።የሚበዛው የምስጋና ዕዳ ያለበት ነው ። ወዳጆቼ ትልቁ በደል የእግዚአብሔርን ውለታ መርሳት ነው ። መቃብራችሁ የተደፈነላችሁ ፣ ከጫካ ሕይወት ወጥታችሁ ከሰው ቊጥር የተደመራችሁ ፣ የክረምትን ያህል በእንባ የታጠባችሁ ፣ ከሩቅ አገር ወደ ክርስቶስ የመጣችሁ ፣ … ለምስጋና ተመለሱ። ፈውስም ማግኘትም ዘላለማዊ አይደሉም ። ዘላለማዊ እግዚአብሔር ብቻ ነው ።
@onegodonlyjesus
Join & Share