Get Mystery Box with random crypto!

በፍቅር መድፈር ምንጭ ፦ ህያውነት (ኦሾ) ትርጉም ፦ ሀብታሙ ተስፋዬ በጥልቀት ካፈቀራችሁ ፍር | ኑ እናንብብ

በፍቅር መድፈር

ምንጭ ፦ ህያውነት (ኦሾ)
ትርጉም ፦ ሀብታሙ ተስፋዬ

በጥልቀት ካፈቀራችሁ ፍርሃት ድራሹ ይጠፋል፡፡ ፍርሃት እጦት፣ አሉታዊ ነገር ነው፡፡ ይህንን በጥልቀት ልትገነዘቡት ይገባል፡፡ ይህን ግንዛቤ ካልጨበጣችሁ የፍርሃትን ባህርይ ልትረዱ አትችሉም፡፡ ፍርሃት እንደጨለማ ነው:: ጨለማ የሌለ ቢሆንም ያለ ይመስላል፡፡ ጨለማ የብርሃን እጦት ነው:: ብርሃን ግን አለ፤ ብርሃኑን ካስወገዳችሁት ጨለማው ብቅ ይላል::

ጨለማ የለም፤ ጨለማን መግፈፍ አትችሉም፤ የፈለጋችሁትን ነገር ብታደርጉ ጨለማን ማስወገድ አትችሉም፣ ልታመጡት ወይም ልትወረውሩት አትችሉም፡፡ ጨለማን አንድ ነገር ማድረግ ከፈለጋችሁ ብርሃንን መጠቀም ይኖርባችኋል፣ ምክንያቱም አንድ ነገር ማድረግ የምትችሉት ህያው የሆነን ነገር ነው:: መብራቱ ስታጠፉት ጨለማ ይሆናል፤ መብራቱን ስታበሩት ጨለማ አይኖርም - በብርሃን አንድ ነገር ማድረግ ትችላላችሁ፡፡ ጨለማን ግን ምንም ማድረግ አትችሉም፡፡

ፍርሃት ጨለማ ነው፣ የፍቅር እጦት ነው፡፡ ምንም ልታደርጉት አትችሉም። ልታስወግዱት ብዙ በጣራችሁ ቁጥር የበለጠ ፈሪ ትሆናላችሁ- ምክንያቱም የበለጠ የማይቻል ይሆንባችኋል፤ችግሩ ይበልጥ ውስብስብ ይሆናል፡፡ ጨለማን ከታገላችሁት ትሸነፋላችሁ፡፡ ጐራዴ ይዛችሁ ጨለማን ልትገድሉት ብትሞክሩ ትርፉ ድካም ብቻ ነው፡፡ በመጨረሻም አዕምሮ “ጨለማ ሃይለኛ ስለሆነ ነው የተሸነፍኩት” ይላል፡፡

ይሄን ጊዜ ነው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ስህተት የሚሆነው፡፡ ሁኔታው ፍፁም ስነ-አመክኖያዊ ነው ከጨለማ ጋር ታግላችሁ ልታሸነፉ ወይም ልታጠፉት ካልቻላችሁ “ጨለማ በጣም፣ በጣም ሃይለኛ ነው፡፡ እኔ ከእሱ ጋር ስነፃፀር ደካማ ነኝ” ብሎ ማሰብ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ እውነታው ግን የተለየ ነው፡፡ እናንተ ሳትሆኑ ጨለማው ነው ደካማ፡፡ በእርግጥ ጨለማው እዚያ ስለሌለ ነው ልታሸንፉት ያልቻላችሁት፡፡ የሌለን ነገር እንዴት ማሸነፍ ይቻላል?

ከፍርሃት ጋር አትታገሉ፣ አለበለዚያ የበለጠ ፈሪ ትሆናላችሁ፡፡ አዲስ ፍርሃት በውስጣችሁ ይገባል፡፡ ፍርሃትን መፍራት ነው በጣም አደገኛው ነገር፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርሃት እጦት ነው፡፡ ሁለተኛው ነገር ፍርሃትን ፍራቻ፣ እጦትን ማጣት ነው፡፡ ከዚያም ወደ እብደት ታመራላችሁ!

ፍርሃት ምንም ሳይሆን የፍቅር እጦት ነው፡፡ ፍርሃትን እርሱትና በፍቅር አንድ ነገር አድርጉ፡፡ በደንብ ካፈቀራችሁ ፍርሃት ይጠፋል፤ በጥልቀት ካፈቀራችሁ ፍርሃት ድራሹ ይጠፋል፡፡

ለአንዲት ቅፅበት እንኳን አንድን ሰው አፍቅራችሁ ፈርታችሁ ታውቃላችሁ? ሁለት ሰዎች ተገናኝተው በጥልቅ ፍቅር ከወደቁ - ለአንዲት ቅፅበት እንኳን ቢሆን በመሃላቸው ፍርሃት አይኖርም፡፡ መብራት በርቶ ጨለማ ሳይኖር አነድ ሚስጥራዊ ቁልፍ አለ - ፍቅር፡፡

በህያውነታችህ ውስጥ ፍርሃት እንዳለ ከተሰማችሁ የበለጠ አፍቅሩ። በፍቅር ድፈሩ፣ ደፋር ሁኑ፤ የፍቅር ጀብደኛ ሁኑ፡፡ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የበለጠ አፍቅሩ፣ የበለጠ ባፈቀራችሁ ቁጥር ፍርሃታችሁም የዚያኑ ያህል ይቀንሳል፡፡

ፍቅር ስል ከፆታ እስከ ሳማዲ ያሉትን እርከኖች ማለቴ ነው፡፡ በጥልቀት አፍቅሩ።

በፆታዊ ግንኙነት በጥልቀት ካፈቀራችሁ ከአካላችሁ ብዙ ፍርሃት ይወገዳል፡፡ ሰውነታችሁ በፍርሃት የሚንቀጠቀጥ ከሆነ የፆታ ፍርሃት አለባችሁ ማለት ነው፤ ከዚህ በፊት በጥልቅ የፆታዊ ግንኙነት ውስጥ አልነበራችሁም፡፡ አካላችሁ ሲንቀጠቀጥ ሰውነታችሁ አልተረጋጋም ማለት ነው፡: .

በጥልቀት አፍቅሩ - ወሲባዊ እርካታ ፍርሃታችሁን በሙሉ ጠራርጐ ያጠፋባችኋል፡፡ ፍርሃታችሁ ተጠራርጐ ይጠፋል ማለት ደፋር ትሆናላችሁ ማለት አይደለም፡፡ ደፋሮች የፈሪዎች ግልባጮች ናቸው:: ፍርሃት በሙሉ ተጠራርጐ ይጠፋል ስል ፍርሃትም፣ ድፍረትም አይኖሩም ማለቴ ነው፡፡

ደፋር የምትሉዋቸውን ሰዎች ተመልከቷቸው:: በውስጣቸው ጥልቅ የሆነ ፍርሃት እንዳለባቸው ትገነዘባላችሁ፣ ከውጭ ሸፋን አበጅተው ነው ደፋር የመሰሉት፤ ድፍረት ፍርሃት አልባነት አይደለም:: ድፍረት ጥሩ መከላከያ፣ ከለላ፣ ጥሩር ያለው ፍርሃት ነው፡፡ "

ፍርሃት ሲጠፋ ፍርሃት አልባ ትሆናላችሁ፡፡ ፍርሃት የሌለበት ሰው በማንም ላይ ፍርሃትን አይለቅም፤ ሌላም ሰው ፍርሃት እንዲያሳድርበት አይፈቅድም፡፡

ጥልቅ የሆነ ወሲባዊ እርካታ አካልን ያረጋጋል፡፡ ሰውነት ምሉዕነት - ስለሚሰማው በጣም፣ በጣም ጥልቅ የሆነ ጤንነት በአካላችሁ ይሰራጫል፡፡

ሁለተኛው ደረጃ ፍቅር ነው። ሰውን ያለ ገደብ አፍቅሩ በአእምሮአችሁ ውስጥ አንድ የሚገድባችሁ ነገር ካለ ማፍቀር አትችሉም። እነዚያ ሁኔታዎች እንቅፋት ይሆኑባችሗል። ፍቅር አስፈላጊያችሁ ከሆነ ስለ ሁኔታዎቹ ለምን ትጨነቃላችሁ? ያለ ገደብ በጥልቀት ማፍቀር በጣም አስፈላጊ ነው - በምላሹ ምንም አትጠይቁ ሰዎችን በመውደድ ምክንያት ብቻ ፍርሃት አልባነትን ማዳበር ከቻላችሁ ለደስታችሁ ስትሉ ብቻ ታፈቅራላችሁ?

ተራ ሰዎች ሁኔታዎቻቸው ሲሟሉሏቸው በቻ ያፈቅራሉ፡፡ “እንዲህ ከሆነክ ብቻ ነው የማፈቅርህ” ይላሉ፡፡ እናት ልጅዋን “ፀባየኛ ከሆንክ ብቻ  እወድሃለሁ” ትለዋለች፡፡ ሚስት ባሏን “እንዲህ ከሆንክ አፈቅርሃለሁ” ትለዋለች፡፡ ሁሉም ሰው ቅድመ - ሁኔታ ሲያስቀምጥ ፍቅር ይጠፋል፡፡

ፍቅር ወሰን የሌለው ሰማይ ነው! ልታጠቡት፣ ልትወስኑት አትችሉም፡፡ ቤታችሁ ውስጥ ንፁህ አየር አስገብታችሁ መስኮቶቻችሁንና በሮቻችሁን ብትቆላልፉ ብዙም ሳይቆይ የታመቀ ይሆናል፡፡ ፍቅር የሚመጣው በነፃነት ነው፡፡ ያን ንፁህ አየር ወደቤታችሁ አስገብታችሁ እንደቆለፋችሁበት ወዲያውኑ ሁሉም ነገር የታመቀ፣ ቆሻሻ ይሆናል።

ይህ የጠቅላላ ሰው ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሰዎች በፍቅር ሲወድቁ ሁኔታዎችን ስለማይደረድሩ ሁሉም ነገር መልካም ይመስላል፡፡ የተፈቀሩት ሰዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይቀራረባሉ፡፡ ከተረጋጉ በኋላ፣ ፍቅር መሰጣጠት ከጀመሩ በኋላ፣ ቅድመ - ሁኔታዎች ይመጣሉ፡፡ ፍቅር የገበያ ዕቃ ይመስል “ይሀን ካልመሰልክ፣ እንዲህ ካልሆንሽ” ይባባላሉ፡፡

በሙሉ ልባችሁ ካላፈቀራችሁ እየተደራደራችሁ ነው:: ሌላኛውን ሰው የሆነ ነገር ካላደረግክልኝ እያላችሁ እያስገደዳችሁ ነው፡፡ ይህ ቅድመ ሁኔታችሀን ካልተሟላ ፍቅራችሁን ትከዳላችሁ፡፡ አሁን እያፈቀራችሁ ሳይሆን ፍቅራችሁን እንደ መቅጫ፣ እንደማስገደጃ እየተጠቀማችሁበት ነው:: ፍቅር ተቀባይ ወይም ፍቅር ሰጪ ብትሆኑም በሁለቱም መንገድ ፍቅር መጨረሻ አይደለም፡፡

ያገባችሁ ከሆነ ለሚስታችሁ ስጦታ ይዛችሁላት ትሄዳላችሁ - ይሄን ጊዜ ደስ ብሏት እያቀፈች ትስማችኋለች፡፡ ወደ ቤታችሁ የሆነ ነገር ይዛችሁ ካልገባችሁ ግን መራራቅ ይፈጠራል፡፡ እንኳን ልትስማችሁ አጠገባችሁ አትደርስም፡፡ እንደዚህ አይነት ነገር ስታደርጉ ፍቅር ለሌሎች ብቻ ሳይሆን ለእናንተም ጠቃሚ እንደሆነ ዘንግታችኋል ማለት ነው፡፡ ፍቅር የሚጠቅመው አፍቃሪዎችን ነው፤ የተፈቀሩትንም ይጠቅማል፡፡

ሰዎች ወደ እኔ ይመጡና “ጓደኛዬ አያፈቅረኝም” ይላሉ፡፡ “እኔ አላፈቅረውም ብሎ የሚመጣ የለም:: ፍቅር ማስገደጃ ሆኗል፡፡ “ጓደኛዬ አያፈቅረኝም።" ስለሌላው እርሱ! ፍቅር እጅግ ድንቅ ክስተት ነው፡፡ ስታፈቅሩ ደስተኛ ትሆናላችሁ፡፡

ብዙ ባፈቀራችሁ መጠን ደስተኛ መሆናችሁም በዚያው ልክ ይጨምራል። ፍቅራችሁ ባነሰ ቁጥር ሌሎች እንዲያፈቅሯችሁ ትጠብቃላችሁ፤ ደስተኛነታችሁ ይቀንሳል፤ የበለጠ ውስን ትሆናላችሁ፤ የራስ ኩራታችሁ ጥገኛ ትሆናላችሁ::

@Zephilosophy
@Zephilosophy