Get Mystery Box with random crypto!

«ምኞት በጥም የተቃጠለ ሰው የሚጠጣው ጨዋማ ውሃ ማለት ነው>> ምንጭ ፦ጥበብ ፭ ፀሀፊ ፦ ጲላጦ | ኑ እናንብብ

«ምኞት በጥም የተቃጠለ
ሰው የሚጠጣው ጨዋማ ውሃ ማለት ነው>>

ምንጭ ፦ጥበብ ፭
ፀሀፊ ፦ ጲላጦስ (ሀይለጊዮርጊስ ማሞ)

የሰው ልጅ ንፁህ የሆነውን የቡድሀ ተፈጥሮውን የሚያረክስበት ሁለት መንገድ እንዳለው የቡድሀ ትምህርት ያሳየናል። እነዚህ ሁለት መንገዶች በዓለማዊ ፍላጐት ከመያዝ እንደሚመነጩ የሚነግረን ቡድሀ እነሱም፡- «የመጀመሪያው፡- ሰው ስለእያንዳንዱ የሕይወት ጉዳይ የሚሰጠው ትርጓሜና ከዚያም በሚመነጨው ክርክር የሚደርስበት ውሳኔ ግራ መጋባትን ስለሚፈጥርበት የሕይወት መርከስ ውስጥ መግባቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በሕይወቱ ታላቅ ዋጋ ያለውን ጉዳይ በመጣል ስሜቱ እንደመራው ሲጓዝ እንዲሁ በግራ መጋባት ተጠምዶ እርኩሰትን መሞላቱ ነው» ይላል።

«እንግዲህ አስቀድሞ በፍላጐት በመወሰድ ቀጥሎም ያሰቡትን በመኖር የሚገባበት ግራ መጋባት የሰው ልጅ የመከራው ምክንያት መሆኑን ታውቁ ዘንድ ይገባል። ነገር ግን አሁንም የዚህ ሁሉ ርኩሰት ምንጩ «አላዋቂነት (ስንፍና) እና ከንቱ ምኞት ነው» የሚለን ቡድሀ፦ የሰው ልጅ በፍላጎቱ ተወስዶ የሚገባበት ግራ መጋባት መሠረቱ አላዋቂነት ሲሆን፣ በኑሮው የሚገባበት ግራ መጋባት ደግሞ መሠረቱ ከንቱ ምኞቱ ነው» ይላል፡፡ ...

የሁለቱ ተጣምሮ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ መገኘት ብዙዎች ለሚገኙበት መከራ ምክንያቱ እንደሆነ የሚያስተምረን ቡድሀ የሰው ልጅ ከእውቀት በራቀ መጠን በትክክልና እንደሚገባው ማሰብ እንደማይችልና ከምኞቱ ተጣብቆም እሱን ሲከተል ግራ መጋባትን ዕጣ ፈንታው አድርጐት እንደሚቀር ይነግረናል። ብዙዎች በልማድ ግራ መጋባት እየተነዱ ለጊዜያዊ ደስታ ሲራቡ የመስተዋሉ ምስጢርም ይኸው ነው፡፡ እንደቡድሀ ትምህርት አንዳንዶች የሥጋቸውን ሞት እስከመሻት የሚያደርሳቸው ይኸው የሕይወት ግራ መጋባት እንደሆነም ያሳየናል፡፡

«እንግዲህ» ይለናል ቡድሀ «የሰው ልጅ በፍላጐቱ በመወሰዱና በተወሰደውም በመኖሩ ስግብግብነት፣ ቁጣ፣ ስንፍና፤ አለመግባባት፣ ሐዘን፣ ቅናት፣ ሽርደዳ፣ ማታለል፣ ኩራት፣ ትዕቢት፣ ራስን መውደድ በየትውልዱ እየተገለጡ የሚታዩ የማንነቱ ተናጋሪ ሆነዋል» ይላል።

«የስግብግብነት ምንጩ ለራስ እርካታን ከማግኘት የሚመነጭ የተሳሳተ ሐሣብ ነው፤ ቁጣም እንዲሁ ከተሳሳተ ሐሣብና የሚገኙበትን ደረጃ ካለመረዳት የሚመነጭ የአስተሳሰብ ውጤት ነው፤ ስንፍናም ቢሆን ትክክለኛው ባህርይን ለይቶ ከአለማወቅ የሚወጣ ስሜት ነው» የሚለን ቡድሀ «ስግብግብነት፣ ቁጣና ስንፍና ሦስቱ የዓለም እሳቶች መሆናቸውን ተረዱ» ይለናል።

«የስግብግብነት እሳት ሁሉን ነገር ለራስ በመመኘት አእምሮአቸው የተዋጠ ሰዎችን የሚበላ ሲሆን፤ የቁጣ እሳት ደግሞ በሕይወት ጉዳይ በመብሰልሰልና በመናደድ ሕሊናቸው የተሸነፈ ሰዎችን ሲውጣቸው ይስተዋላል፡፡ የስንፍና እሳትም እንዲሁ የቡድሀን የሕይወት መንገድና ሐሣብ ባለመረዳት በራሳቸው መንገድ ሲሄዱ የሚሸነፉትን ሰዎች የሚያነድ ነው» ይላል ቡድሀ፡፡

እርግጥ ነው ይኸን ዓለም የሚያነዱ ለቁጥር የበዙና ዓይነታቸው የትየለሌ የሆነ የእሳት ዓይነቶች መኖራቸውን ቡድሀ ሲነግረን ከእነዚህም ውስጥ ከስግብግብነት፣ ከቁጣ፣ ከስንፍና ባሻገር ራስን የመውደድ፣ የሽምግልና፣ የበሽታና የሞት፣ የሐዘን፣ የሰቆቃ፣ የመከራና ስቃይ እሳቶች ዋነኞች ናቸው፡፡ በምድራችን አራቱም አቅጣጫ ይኸ እሳት እየነደደ ነው፡፡ እሳቱ ራስን ከማቃጠል አልፎም ለሌሎች ሐዘንና መከራን እንዲሁም ሰቆቃን ማትረፉን ስናስተውል በእሳቱም የተቃጠሉት ቁስል እያመረቀዘ የሚወጣው መርዝ በክፋት መንገድ አያሌዎችን ዘወትር ሲመራቸው ይኖራል፡፡

«የስግብግነት መዘዝ እርካታን ከመሻት፣ ቁጣ ደግሞ እርካታን ከማጣት የሚመነጩ የሰው ስሜቶች ሲሆኑ ስንፍና ደግሞ ከአደፈ አስተሳሰብ መመንጨቱን ልብ በሉ» የሚለን ቡድሀ «የስግብግብነት መንፈስ ጉድፉ ጥቂት ቢሆንም በቀላሉ የማይላቀቁት ችግር ነው፤ የቁጣ መንፈስ ደግሞ ጉድፉ እጅግ የበዛ ቢሆንም ለመላቀቅ ግን አስቸጋሪ አይሆንም፤ የስንፍና መንፈስ ጉድፉ የበዛ እንዲሁም ለመላቀቅ አስቸጋሪ መሆኑን ተረዱ» ይለናል፡፡

ስለዚህም የሰው ልጅ እውነተኛ እርካታን ለማግኘት የቡድሀን ትምህርትና ዕውቀት በማግኘት ቅንነትን፣ ባለው ረክቶ መኖርን እንዲሁም ታጋሽነትን እንዲለማመድና የራሱን የሰላም ዓለም መመስረት እንዲችል የሚነግረን ቡድሀ ለሰው ልጅ መከራ ውስጥ መዘፈቅ ስግብግብነት፣ ቁጣ እና ስንፍና ዋነኛ መሠረቶቹ እንደሆኑ በሚገባ እንድናውቃቸው በማስተማር ወደሌላ ርዕሰ ጉዳይ ይዞን ይሻገራል፡፡

«የሰው ልጅ ምኞት ገደብ የለሽ ነው፡፡ ምኞት በጥም የተቃጠለ ሰው የሚጠጣው ጨዋማ ውሃ ነው፤ ጨዋማ ውሃ የውሃ ጥምን አለማርካት ብቻ ሳይሆን ጥሙ እየጨመረ እንዲሄድ ማድረጉ የማይቀር ነውና። ስለዚህም የሰው ልጅ የእርካታ ምንጩ ከውስጡ ነው፤ በምኞቱ ግን አለመርካት ብቻ ሳይሆን ስቃዩም እየጨመረ ይሄዳል፡፡ እናም ለምኞትህ ልጓም አብጅለት:: ምኞትህ ከጨመረ ቁጣህ ደስታና እርካታ እየቀነሰና እየከፋ ከመሄዱም ባሻገር መጨረሻህ ወደ እብደት መድረስ ብቻ ይሆናል» የሚለን ቡድሀ «ምኞታቸውን ለማርካት ሰዎች ዘወትር ሲሮጡ ስንመለከት ውጤታቸው አንዱ በሌላው ላይ ማሴር፣ መንግሥት በሌላው ላይ ሠራዊት ማዝመት፣ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ መነሣት፣ ወንድም በወንድሙ ላይ ለጥፋት ማድባትና ወዳጅ የወዳጁን መቃብር መቆፈር ናቸው፡፡ በአጭሩ እርስ በርስ መጋደልና መጠፋፋት የዘወትር
ተግባራቸው ይሆናል» ይላል፡፡

«ልብ በሉ! ሰዎች ሕይወታቸውን የሚያለሙበትም ሆነ የሚያጠፉበት ዋነኛ ምክንያት ምኞታቸው ነው:: ማታለል፣ መስረቅ፣ ዝሙት፣ ከዚያም ተይዞ በውርደትና በሐፍረት መሰቃየት የምኞታቸው ዘር የሚያሳጭዳቸው አዝመራ ነው:: በራሳቸው ገላና ቃል ኃጢአትን ይፈፅማሉ:: በአእምሮአቸው የሚፈፅሙት ኃጢአት መጨረሻው በሥጋና ነፍሳቸው ሐዘንና መከራ እንደሚያተርፍላቸው ሲያውቁት እንኳን ይኸንኑ ከመፈፀም ወደኋላ አይሉም። መጨረሻቸውም በመከራ ዓለም ገብቶ በዚያ መካከም ይሆናል» ይላል ቡድሀ።

ቡድሀ ወደሌላው የከፋ ዓለማዊ ምኞት ሲወስደን የምናገኘው ጉጉትን ነው:: ለቡድሀ ሌሎች ዓለማዊ ምኞቶች ሁሉ የሚፈሱት በጉጉት ቦይ ውስጥ ነው:: ከፍ ያለ ጉጉት በሥጋህ ነፍስን ሲዘራ ሌሎች ምኞቶች የሚበቅሉበት ለም አፈር ይሆናል፡፡ ጉጉት የሰው ልጅ መልካም ተግባራትን ሁሉ በልቶ የሚጨርስ አንበጣ ነው፡፡ መልካሙ የአትክልት ሥፍራ የተንቀሳቀሰው የእባቡ መርዝ ይኸው ጉጉት ነው፤ ውበትን ብቻ በመሻት ወደዚያ የሚመጡትን ሁሉ ጉጉት ሲመርዛቸው ዘመናት ተቆጥረዋል። ጉጉት የሚያንቀው ነገር ከፊቱ እስኪቆም ድረስ እንደወይን ዛፍ ቅጠሉንና ቅርንጫፉን እያሰፋ የሚሄድ ተክል ነው። ጉጉት በሰው ልጅ ስሜትና ሐሣብ ውስጥ የሚሰነቀር ሰንኮፍ ሲሆን ልብንና አእምሮን በዝግታ የሚገድል መርዝም ነው፤ ጉጉት በክፉው ሰው መንፈስና በሰነፍ ሕይወት ውስጥ ተዘርቶ የሚበቅል ዘር ነው፡፡

«ይኸንን ተረዱ! ደረቅ አጥንትን በደም ለውሳችሁ ለውሻ ብትጥሉ ውሻው እስኪደክመው ድረስ ከአጥንቱ ጋር ታግሎ ጥሎት ይሄዳል፤ እንዲሁም ጉጉት ለሰው ልጅ ለውሻው እንደተሰጠው አጥንት ነው፤ ሕይወቱን በመከራ እንዲገፋ አድርጎት እንዲሁ ጥሎት እንዲሄድ ያደርጋል» ይላል ቡድሀ፡፡

@Zephilosophy
@Zephilosophy