Get Mystery Box with random crypto!

አገር እንቁጣጣሽ አገር እንቁጣጣሽ የ'ዳ ክንድሽ አቅፎኝ ያሳር ክንፍሽ አቅፎኝ ዕንቁሽን | ኑ እናንብብ

አገር እንቁጣጣሽ

አገር እንቁጣጣሽ
የ'ዳ ክንድሽ አቅፎኝ
ያሳር ክንፍሽ አቅፎኝ
ዕንቁሽን ስመኘው፥ ጣጣሽ ብቻ ተርፎኝ
መኖርን ስፈራ፥ መሞትም ስፈራ
ካየር ንብረት በቀር፥ ንብረት ሳላፈራ
ወሩ ተጠራቅሞ፥ አንድ ደርዘን ሞልቶ
እንደባለጌ ልጅ፥ በሩን በግሩ ከፍቶ
አዲስ ዘመን ገባ፤


አዲስ አመት ገባ
ያለ መስቀል ወፎች፥ ያለ ዓደይ አበባ
በግዜርሠራሽ ማማ
ቁራ ብቻ ሰፍሯል
የመስቀል ወፍማ
ወይ አገር ለውጧል
ወይ ልብሱን ቀይሯል፤


አዲስ አመት ገባ
በቄጤማ ምትክ፥ ብሎኬት ጎዝጉዞ
በቅፍ ዓደይ ምትክ፥ ጉንጉን ሽቦ ይዞ
በሉባንጃ ምትክ፥ አቧራ እያጤሰ
በፈንድሻ ምትክ፥ ጠጠር እያፈሰ፤


አዲስ አመት ገባ
እንዲህ እንደዋዛ
ተፈጥሮ በውበት፥ መንፈሴን ሳይገዛ
በመአዛው ሳይዋጅ
መስከረም መግባቱን በሬድዮ ልስማው?
እንደ መንግሥት አዋጅ።
............
እንቁጣጣሽ
............