Get Mystery Box with random crypto!

አንዳንድ ገፅ '''''''''''''''''''''''' የኔነቴ ምዕራፍ ልክ እንደ መፅሀፍ ጠፍተው | ኑ እናንብብ

አንዳንድ ገፅ
"""""""'''''''''''''''""

የኔነቴ ምዕራፍ
ልክ እንደ መፅሀፍ
ጠፍተው የተረፉ ሰባት ገፆች አሉት፤
የኔና አንቺን ህይወት በግልፁ የሚያትት።

ማውጫ የለው መግቢያ
ጥራዝ የለው ሽፋን
ወና ....ቤት አልባ ገፅ፤
እንዲህ ይነበባል
በባለ ታሪኩ ታሪኩ ሲገለ'ፅ።

(ገፅ አንድ)

በሰፈሬ መንገድ ቁልቁለቱን ስወርድ፤
አንቺ ደሞ ወደላይ ስትወጪ አቀበት፤
እንቅፋት ሳይነካኝ ልቤ አለ ሸርተት፤
አልገባኝም ነበር?
ከየት አመጣጡ? ደርሶ ይሄ ስሜት።

አቀበት ሆኖብሽ
ደካክሞሻል አንቺ ያለሽበት መንገድ፤
ድካም ነው ቁንጅናሽ?
አልገባኝም ከቶ ደርሶ የልቤ መራድ።

መንገዱ ሲወስደኝ የልቤ መረበሽ፤
መንገዱ ሲይለፋሽ እንዲያ ተደካክመሽ፤
ድጋሚ አልገባኝም?
ጎን ለጎን ስንደርስ
ለምን ተሽኮረመምሽ? ለምን ስቀሽ አለፍሽ?

(ገፅ ሁለት)

እኔ እንቅልፋሙ
የሞትኩ የምመስለው ጎኔ ሲነካ አልጋ፤
አልገባኝም ዛሬም?
አልጋው ኮሰኮሰኝ ስገላበጥ ነጋ።

ውሎዬ አላማረ
እንዲሁ ስነጫነጭ ባህሪዬ ከፍቶ፤
"ምን ሆነሀል?" ሲለኝ
መጤ ባህሪዬን ሰዉ ተመልክቶ።
አላውቅም ምንድነው?
ልገልፀው አልቻልኩም ያናደደኝ ነገር፤
ቆይቼ ሲገባኝ
ገፅ አንድ ላይ ያለው አሳሳቅሽ ነበር!

(ገፅ ሶስት)

ድንገት ያየሁሽ ቀን
በደስታ ባህር ውስጥ ልቤ ሲረግጥ ጮቤ፤
ያላየሁሽ ለታ
ተከፍቼ ስገኝ ሀዘኔን ደርቤ፤
ለተመልካች ሁሉ
እኔ አንቺን መውደዴ አሳበቀ ቀልቤ፤
ልቀርብሽ ፈለኩኝ
የወንድነት ወኔ ድፍረቴን ሰብስቤ።

(ገፅ አራት)

ሰላም ተባባልን
ትንሽ ተንተባተብኩ አንቺም ተዋወቅሽኝ፤
ፍርሃቴም ቀነሰ
ተለማመድንና ቀርቤሽ ቀርበሽኝ፤
ግን ሌላ ምጥ ያዘኝ
እንደ ጓደኛ እንጂ በፍቅር አላየሽኝ፤
ድጋሚ አማጥኩኝ
ትንሽ ጉድጓድ ስዘል ትልቅ ገደል ሆንሽኝ።

(ገፅ አምስት)

ምንም አይገባሽም
ላሳይሽ ብሞክር ፍቅሬን በተግባር፤
የፍቅር አኩኩሉ
እየተጫወትኩኝ  ተደብቄ ነበር፤
ደንታም አልነበረሽ
በስስት ማየቴ ለማሳይሽ ነገር፤
ግን ስፈራ ስቸር
ልነግርሽ ወሰንኩኝ በቃል የኔን ፍቅር።

(ገፅ ስድስት)

የነገርኩሽ ለታ
እንደ መሳቅ እያልሽ
"እንዴት ነው ያየከኝ?" የሚል ወጣ ካፍሽ
"ስሜት የለኝ ላንተ"
በምትለዋ ቃል በሰቀቀን ጥለሽ መንፈሴን አደማሽ
ታዲያ ገፅ አንድ ላይ
ምን አሽኮረመመሽ?...ለምን ስቀሽ አለፍሽ?

(ገፅ ሰባት)

ገብቶሻል ስሜቴ
አትምሰይ እባክሽ ይሄ የማይገባሽ፤
ጨንቆኝ የቀረብኩሽ
እህት ፈልጌ አይደል
ያልገባው አትምሰይ ገብቶሻል እባክሽ።

አሁን በይምሰልሽ አውቀሽ ልትመልሽኝ፤
ሳቅሽ ቀመር ነበር
ዳገቱም ነው ቀመር
አካሄድሽ ቀመር አውቀሽ ነው የታየሽኝ።

(ገፅ ስምንት)

ገፅ ስምንት ላይ
"አውቀሽ ነው የታየሽኝ..." በከፊሉ ይላል.....

የወረቀቱ ገፅ በግማሽ ተቀዷል
               .
               .
               .
               .
ውድቆ ቀርቷል እንጂ ታሪኩ ይቀጥላል

አብራሀም

https://t.me/nuenanbib