2021-10-17 07:58:58
የሕይወት ዋጋው ስንት ነው
ከዕለታት ባንዱ ቀን አንድ ታዳጊ አባቱን፦ “የሕይወት ዋጋው ስንት ነው?” ሲል ጠየቀው። አባትም መልስ በመስጠት ፈንታ ልጁን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “እንካ ይህንን የድንጋይ ቁራጭ፤ ወደ ገበያ ውሰደው። ሰዎችም ዋጋውን ከጠየቁህ በጣቶችህ ሁለት ቁጥርን ብቻ አሳያቸው እንጂ ምንም አትናገር!” አለው።
ልጁም ድንጋዩን ወስዶ፤ በገበያ መሃል ቆመ። አንዲት ሴትም መጣ፦ “ይህ ድንጋይ ዋጋው ስንት ነው? ብትሸጥልኝ ወስጄ ግቢዬ ውስጥ አስቀምጠዋለሁ።” አለችው። ልጁም እንደታዘዘው ምንም ሳይናገር ሁለት ጣቶቹን አሳያት። እሷም አለች “ሁለት ብር? እወስደዋለሁ!!!”
ልጁም ወደ ቤቱ ተመለሰ። በገበያ ያጋጠመውንም ለአባቱ ነገረው። አባትየውም፦ “አሁን ደግሞ ድንጋዩን ይዘህ ወደ ሙዚየም ሂድ። ዋጋውን ሲጠይቁህም ሁለት ጣቶችህን አሳይ።” አለው።
ልጁም ወደ ሙዚየም ሄደ። ገዢም መጥቶ ዋጋ በጠየቀው ጊዜ ሁለት ጣቶቹን አሳየው። ገዢውም “ሁለት መቶ ብር? እወስደዋለሁ!” አለው። ልጁም በድንጋጤ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ያጋጠመውንም ነገር ለአባቱ ነገረው።
አባትየውም ተናገረ፦ “አሁን ደግሞ በመጨረሻ ድንጋዩን ይዘህ ወደ የከበሩ ማዕድናት መሸጫ ሂድ። ለባለቤቱም አሳየው!” አለው።
ልጁም ሄዶ ለሱቁ ባለቤት አሳየው። የሱቁ ባለቤት በመገረም፦ “ይህ እኮ ዓለም ላይ እጅግ ውድ ከሆኑ የከበሩ ድንጋዮች አንዱ ነው።” አለ።
“ከየት አገኘኸው? ስንትስ ትሸጠዋለህ?” ሲል ጠየቀው። ልጁም ምንም ሳይናገር ሁለት ጣቶቹን አሳየ። የሱቁም ባለቤት፦ “ይህንን ድንጋይ በሁለት መቶ ሺህ ብር እወስደዋለሁ።”
ልጁም በመገረም እየሮጠ ወደ ቤቱ ተመልሶ ያጋጠመውን ለአባቱ ነገረው። አባትየውም፦ “ልጄ አሁን የሕይወትህ ዋጋ ተገልጦልሃል?!” አለው።
ቁምነገር!
አየህ የመጣህበት ቦታ፣ ዘርህ፣ ሃይማኖትህ፣ የቤተሰቦችህ ሃብት፣ የተወለድክበት ቦታ ልዩነት አይፈጥርም። ዋናው ራስህን የምታስቀምጥበት ቦታ፣ ራስህን የምታገኝበት የሰዎች ስብስብ ነው። ልዩነቱ ያለው ራስህን ለመሸከም በምትመርጥበት መንገድ ነው። ሕይወትህን ሙሉ የሁለት ብር ድንጋይ ዋጋ ስትሰጠው ኖረህ ይሆናል።
ሕይወትህን ሙሉ የኖርከው ዋጋህ ሁለት ብር ብቻ እንደሆነ በሚያስቡ ሰዎች ተከበህ ይሆናል። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ውድ የሆነ የከበረ ድንጋይ በውስጡ ይዟል። ልዩነቱም ያለው ውስጣችን ያለውን የከበረ ድንጋይ አይተው ዋጋ በሚሰጡን ሰዎች መሃል መገኘትን ስንመርጥ ነው።
ራሳችንን በገበያ ወይም በከበሩ ማዕድናት ሱቅ የማስቀመጥ ምርጫው አለን። በሌሎች ሰዎች ውስጥ ያለውንም ውድ ዋጋ ለማየት ምርጫው የኛው ነው። ሌሎች ሰዎችም የከበረ ዋጋቸውን እንዲረዱ ማድረግ እንችላለን። አብረህ የምትውላቸውን ሰዎች በጥንቃቄ ምረጥ። ይህ በሕይወትህ ልዩነትን ይፈጥራልና!
(ሻውን ቡንደናሂራን ከተረከው፣ የተተረጎመ)
Hiju@...
85 viewsTIGSTU AMBAW, 04:58