Get Mystery Box with random crypto!

#ቅን_ልቦና በሰበር ችሎት ክፍል አንድ ቅን ልቦና ከውክልና እና አላግባብ መበልጸግ ጋር በተያያዘ | ነገረ ፈጅ Negere Fej 📕

#ቅን_ልቦና በሰበር ችሎት ክፍል አንድ
ቅን ልቦና ከውክልና እና አላግባብ መበልጸግ ጋር በተያያዘ በሰበር ችሎት የተሰጡ ትርጉሞች
አብርሃም ዮሐንስ
ውክልና
ሰ_መ_ቁ. 14974 ቅጽ 1

ተወካዩ የራሱን ጥቅም የሚመለከት ጉዳይ ሲያጋጥመው ሁኔታውን ለወካዩ ሳያሳውቅና ወካዩ ሳይስማማ ስራውን እንዳይፈጽም ይከላከላል፡፡ ስለወኪልነት የተደነገጉትን የፍ/ብሔር ድንጋጌዎች ስንመለከትም ተወካዩ ከወካዩ ጋር በሚኖረው ግንኙነት ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና ሊኖረው እንደሚገባ እና የውክልና ስልጣኑን የሚያስቀሩ ምክንያቶች እንዳለበት (የፍ/ብ/ህ/ቁ 2208)፣ ተወካዩ ስራውን የሚፈጽመው በተለይ ለወካዩ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት (ፍ/ብ/ህ/ቁ 2209(1))፣ እንዲሁም ተወካዩ በራሱ ስም ከወካዩ ጋር የሚያደርገው ውል ወካዩ ካላጸደቀው በቀር ሊፈርስ እንደሚችል (የፍ/ህ/ቁ 2188) መደንገጋቸው ተወካዩ ለወካዩ ፍጹም ታማኝ መሆን እንዳለበት እና ለወካዩ ጥቅም ብቻ መስራት እንዳለበት፣ የጥቅም ግጭት ባለበት ጊዜ ሁሉ ሁኔታውን ለወካዩ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡ በመሆኑም Aንድ ተወካይ የጥቅም ግጭት ባለበት ጊዜ ለወካዩ ሳያሳውቅ የሚየከናውነውን ስራ ወካዩ ሊቃወመው የሚችል መሆኑን እና በዚህ ሁኔታ የተከናወነው ስራም ወካዩ ካላፀደቀው በቀር ወካዩ ራሱ እንደፈጸመው ሊቆጠር እንደማይገባ ከውክልና ግንኙነት አጠቃላይ ዓላማ እና ከፍ/ብ/ህጉ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሰ_መ_ቁ. 26399 ቅጽ 5

ሿሚው በግልጽም ይሁን በዝምታ እንደራሴው ሥልጣኑ ቀሪ ከሆነ በኋላ የሠራውን ሥራ ያልተቀበለው መሆኑ ከተረጋገጠ የዚሁ ያለመቀበል ውጤት በቁጥር 2193 ተደንግጓል፡፡ የዚህን ድንጋጌ ይዘት ስንመለከት ሿሚው ይህንኑ የእንደራሴውን ሥራ ካልተቀበለው ምን ጊዜም ይኸው ውል ፈራሽ ነው የሚል አይደለም፡፡
ይልቁንም ከፍ/ብ/ሕ/ቁ. 1808 እስከ 1818 ድረስ የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ተከትሎ የውሉ መፍረስ ወይም መሰረዝ ሊወሰን የሚችል መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም እነዚህኑ አግባብነት ያላቸውን ድንጋጌዎች በመከተል ውሉ ሊፈርስ የማይችልበት አጋጣሚ ያለ መሆኑን የሚያሳይና ነገር ግን ውሉ የሚፈርስ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ውሉ በመፍረሱ ምክንያት በቅን ልቦና ከእንደራሴው ጋር በተዋዋሉት 3ኛ ወገኖች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ካሣ የሚጠየቅበት መንገድ የሚያመቻች ድንጋጌ ነው፡፡

ሰ_መ_ቁ. 77983 ቅጽ 15

ተወካዩ ከወካዩ ጋር የሚያሰተሳስረው ግንኙነት ውስጥ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና ሊኖረው እንደሚገባ በፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 2208(1) ስር ተደንግጓል ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ተወካዩ የተወካይነት ሥራውን የሚፈጽመው በተለይ የወካዩን ጥቅም ሊሰጥ በሚችልበት መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2209 (1) ድንጋጌ ያሳያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተወካዩ በውክልና ሥራው ላይ በሚገኝባቸው ጊዜዎች ሁሉ በውክልና በተሰጠው አደራ አንድ መልካም የቤተሰብ አባት ቤተሰቡን ለመጠበቅ እንደሚያደርገው ሁሉ በትጋትና በጥንቃቄ መጠበቅ ያለበት መሆኑን በፍትሐብሄር ሕግ ቁጥር 2211(1) ስር በግልጽ ተደንግጓል፡፡

አላግባብ መበልጸግ

ሰ_መ_ቁ. 81081 ቅጽ 14

የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2168 ድንጋጌ ይዘት ሲታይም አንድ ሰው ለተወሰነ ጊዜ በእጁ ያቆየውን እቃ እንዲመለስ የተገደደ እንደሆነ ለሕግ ወይም ለውል ተቃራኒ የሚሆን ድንጋጌ ከሌለ በቀር የተባለውን እቃ ከመለዋወጥ የተነሳ ያሉት መብቶችና ግዴታዎች ከድንጋጌው ቀጥለው ባሉት ደንቦች መሰረት የሚወሰን መሆኑን የሚያስገነዝብ ሲሆን በዚሁ ድንጋጌ ስር ከሰፈሩት ደንቦች መካከል አንዱ የሆነው በፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2169 ስር የተቀመጠው ደግሞ የያዘውን እቃ እንዲመልስ የተገደደ ሰው በእቃው ላይ ያደረገው ወጪ ሊመለስለት የሚገባው ወጪው የግድ አስፈላጊ ሁኖ ሲገኝ ስለመሆኑና ወጪው አስፈላጊ ሳይሆን ከቀረ ወይም ወጪው እቃውን እንዲመለስ በተገደደው ሰው ወይም ተገዳጁ ኃላፊ በሚሆንበት ሰው ጥፋት ምክንያት ከሆነ ወጪው ሊመለስ የማይችል መሆኑን ያሳያል፡፡
ሕጉ በአንቀጽ 2171(1) ስርም ለእቃው የተደረገው ወጪ የእቃውን ዋጋ ግምት ከፍ አድርጎት እንደሆነም እቃውን ለመመለስ የተገደደው ሰው ስለዚሁ ጉዳይ ያወጣው ገንዘብ ሊመልስለት እንደሚገባ የደነገገ ሲሆን ይህ ወጪ በክፉ ልቦና ስለመደረጉ የተረጋገጠ ወይም ርትዕም የሚያስገድድ ከሆነ ደግሞ ዳኞች ወጪውን ለመቀነስ ወይም ጭራሹን ለማስቀረት የሚችሉበት አግባብ መኖሩንን የተጠቃሹ ድንጋጌ ቀጣይ የሆነው የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 2172((1) ይዘት ያሳያል፡፡
ይህ ድንጋጌ አንድን ወጪ በክፉ ልቦና የተደረገ ነው ለማለት የሚቻልበት አግባብም ወጪው በተደረገበት ጊዜ ወጪውን የሚጠይቅ ሰው እቃውን ለመመለስ ግዴታ ያለበት መሆኑን ያውቅ እንደነበረ ወይም ማወቅ ይገባው የነበረና ርትዕም ሲያስገድድ መሆኑን በመለኪያነት አስቀምጧል፡፡
ስለሆነም እነዚህ ድንጋጌዎች ሲታዩ አንድ ሰው የሌላ ሰው ንብረት ይዞ ሲጠቀም ከቆየና ንብረቱን በሚጠቀምበት ጊዜ ንብረቱን ከጥፋት ወይም ከብልሽት ለማዳን ሲል ተገቢውን ወጪ ቢያወጣ ይኼው ወጪ በሕጋዊ ባለሃብቱ እንዲተካለት መጠየቅ የሚችልበት አግባብ የሚኖረው ወጪው የግድ አስፈላጊ ከሆነና በቅን ልቦና የተደረገ መሆኑ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡ ሲሆን በክፉ ልቦና የተደረገ ስለመሆኑ የተረጋገጠውን ወጪ ግን እቃውን እንዲመለስ የተደረገ ሰው ሊቀነስበት ወይም ጭራሹንም ዳኞች ሊያስቀሩት የሚችሉ ስለመሆኑ ሕግ ስልጣን የሰጣቸው መሆኑን ድንጋጌዎች ያስረዳሉ፡፡