Get Mystery Box with random crypto!

ጋብቻ መኖሩ ስለሚረጋገጥበት መንገድ ሰ/መ/ቁ 206403 ጋብቻ የሚፈጸመው በሦስት መንገድ ማለት | ነገረ ፈጅ Negere Fej 📕

ጋብቻ መኖሩ ስለሚረጋገጥበት መንገድ ሰ/መ/ቁ 206403

ጋብቻ የሚፈጸመው በሦስት መንገድ ማለት በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣ በሃይማኖት ሥርዓት ወይም በባህሌ ሥርዓት ሲሆን ከእነዚህ ከሦስቱ በአንዱ መንገድ መፈጸሙን በማስረጃ በማስረዳት የጋብቻ መኖርን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ እነዚህ ጋብቻ የሚፈፀምባቸው መንገዶች የራሳቸው አፈፃፀም ሥርዓት ያላቸው በመሆኑ ከተጋቢ ጥንዶች ውጭ ሥርዓቱን በማስፈፀም፣ በምስክርነት፣ በታዳሚነት ወዘተ ደረጃዎች ሰዎች የሚሳተፉበት ነው፡፡ በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 94 መሰረት ጋብቻ መኖሩን ለማስረዳት የሚቀርበው ቀዳሚ ማስረጃ የጋብቻ የምስክር ወረቀት ነው፡፡
ጋብቻቸውን አስመዝግበው የምስክር ወረቀት ያልያዙ ተጋቢዎች ወይም መዝገቡ በመጥፋቱ ምክንያት የጋብቻ ምስክር ወረቀት ማቅረብ ያልቻሉ ተጋቢዎች ጋብቻ መፈፀሙን በትዳር ሁኔታ መኖር ማስረዳት እንደሚችሉ በአዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 95 ተመልክቷል፡፡ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት የትዳር ሁኔታ አላቸው ለማለት እራሳቸውን እንደባልና ሚስት የሚቆጥሩና የሚኖሩ ከመሆናቸው በላይ ቤተሰቦቻቸውና ማህብረሰቡ በባልና ሚስትነት የሚቀበሏቸው ሆነው ሲገኙ መሆኑን አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 96 ያስረዳል፡፡
የትዳር ሁኔታ መኖር ሌላ አራተኛ ጋብቻ የሚፈፀምበት ሥርዓት ሳይሆን ከሦስቱ የጋብቻ አፈፃፀም መንገዶች በአንዱ ጋብቻ መፈፀሙን የሚያስረዳ ማስረጃ ነው፡፡ የትዳር ሁኔታ መኖሩን ለማስረዳት የሰው ምስክር፣ የሰነድ ማስረጃን እና ሌላ ማስረጃ ማቅረብ የሚቻል ሲሆን፣ ማስረጃውን የማቅረቡ ዓላማ ጋብቻ መኖሩን ለማስረዳት በመሆኑ፤ ማስረጃው ማስረዳት ያለበት ጭብጥ ጋብቻ መፈፀሙን ማወቅን የሚያመለክት እንጂ በባልና ሚስትነት መኖራቸው ላይ ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ ምስክርነቱ እራሳቸውን እንደ ባልና ሚስት መቁጠር ወይንም እንደ ባልና ሚስት ማወቅ ላይ ብቻ የሚንጠለጠል ከሆነ የጋብቻ መኖርን በትዳር ሁኔታ ለማስረዳት በሚል ምክንያት ጋብቻንና ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት መኖር መካከል ልዩነት የሌለ ያስመስላል፡፡
ጋብቻ ተፈጽሟል ሊባል የሚችለው ጋብቻ ከሚፈጸምባቸው ሶስቱ መንገዶች በአንዱ መንገድ ተፈጽሞ ሲገኝ በመሆኑ ጋብቻን በትዳር ሁኔታ ለማስረዳት የሚቀርብ ማስረጃ ጋብቻው መኖሩን እንዲሁም የተፈፀመበት ሥርዓት (types of celebration) ማስረዳት ይጠበቅበታል (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ቁ 213/1992 አንቀጽ 95) ይመልከቱ።