Get Mystery Box with random crypto!

የመውጫ ፈተና/Exit Exam መንግስት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጠን | ትምህርት ሚኒስተር

የመውጫ ፈተና/Exit Exam

መንግስት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጠንካራ ትግበራ እና ርምጃዎችን ለመውሰድ ከያዛቸው የሪፎርም አጀንዳዎች መካከል የመውጫ ፈተና (Exit Exam) ዋነኛው ነው።

በህግ እና በህክምና ሙያ የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና እና የብቃት ማረጋገጫ ፍተሻ እንደ ልምድ በመውሰድ መንግስት በሌሎች የትምህርት መስኮችም የመውጫ ፈተና እንዲሰጥ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ትምህርት ሚኒስቴር የመንግስትን አቅጣጫ በመከተል በ2015 ዓ.ም በመንግስት እና በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በየሙያውና ትምህርት ዘርፍ ተዘጋጅቶ ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና ትግበራ ፖሊሲ እና ዝርዝር ማስፈፀሚያ መመሪያ በማዘጋጀት ወደ ሥራም ገብቷል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለመውጫ ፈተና ትግበራ የተዘጋጀውን የአፈፃፀም መመሪያ በማጸደቅም ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሰራጭቷል።

ለመሆኑ መመሪያው ምን ይላል?

➤ የመውጫ ፈተናው የመጀመሪያ ዲግሪ የመንግስት እና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ይመለከታል።

➤ መመሪያው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ እና ሀገሪቱ የምትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከሚከወኑ የማስፈፀሚያ ስልቶች አንዱ ነው።

➤ የመውጫ ፈተናውን ወስዶ 50 በመቶ ውጤት ማምጣት ያልቻለ ተማሪ መመረቅም ሆነ ከተማረበት ዩኒቨርሲቲ የዲግሪ ሰርተፊኬት ማግኘት አይችልም።

➤ በመውጫ ፈተና 50 በመቶ ማምጣት ያልቻለ ተጨማሪ ጊዜ ወስዶ በአግባቡ አጥንቶ ፈተናውን 50 በመቶ እና ከዛ በላይ አምጥቶ ማለፍ እንዲችል ለሁለት ተጨማሪ ጊዜ የመፈተን እድል ይሰጠዋል። ተፈታኙ እድሉን መጠቀም ያለበት የመጀመሪያውን ፈተና ከወሰደ በሦሥት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው።

➤ አንድ ተማሪ ለምርቃት ብቁ የሚሆነው የመውጫ ፈተናውን ካለፈ ብቻ ሲሆን ሦሥት ጊዜ ተፈትኖ የማለፊያ ነጥብ ያላገኘ ተፈታኝ ከብሔራዊ የብቃት ማዕቀፍ ተገቢው ማስረጃ ይሰጠዋል።

➤ የቅድመ ምረቃ የመውጫ ፈተና እንደየትምህርት ፕሮግራሙ ባህሪ በዓመት ሁለቴ እና ከዛም በላይ ሊሰጥ ይችላል።

➤ የመውጫ ፈተና የሙያ ማህበራት ተጠናክረው የሙያ ፍቃድ ፈተና መስጠት እስከሚጀምሩ በትምህርት ሚኒስቴር ወይም ውክልና በሚሰጠው ተቋም ይዘጋጃል።

➤ መውጫ ፈተና ላይ የሚካተቱ ኮርሶችን በተመለከተ በየትምህርት መስኩ በሚዘጋጁ የማስፈፀሚያ ዝርዝር መመሪያዎች ይለያል።

➭ የመውጫ ምዘና ጠቀሜታዎች፦

➤ ተመራቂ ተማሪ በቂ ዝግጅት እንዲያደርግና በራሱ እንዲተማመን ያስችላል።

➤ ተማሪ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ጠንክሮ እንዲሰራ፤ ብቁ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲወጣ ያስችላል።

➤ ተቋማት ተማሪዎቻቸውን በጥሩ ውጤት ለማለፍና ያላቸውን ተፈላጊነት ለማስፋት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲሰሩ ያደርጋል።

➤ መምህራን ተማሪዎቻቸውን ብቃት ተላብሰው እንዲመረቁ ለማስቻል በኃላፊነት ተከታታይ ምዘና በማካሄድ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ክፍተቶች እንዲሞሉ ያደርጋል።

➤ ቀጣሪ ድርጅቶች/ኢንዱስትሪው በተማሪው ብቃት ላይ አመኔታ እንዲኖረው ያደርጋል።

➤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፥ የምሩቃንን ክህሎትና እውቀት ለመፈተሽ እና የሥራ ገበያንም ለማሳደግ ያግዛል።

➤  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አቅምና ጥራትን ለማሻሻል ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

➤ ተማሪዎች በሰለጠኑባቸውና በተማሩባቸው ሙያዎች ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ያስችላል።


@NEAEA_nea