Get Mystery Box with random crypto!

ተግተው የሚሹኝ ያገኙኛል! ሉተር ለረጅም ጊዜ በፍለጋ ተግቶ ነው ለብዙዎች የመዳን ምክንያት የሆነ | ናዝራዊ Tube

ተግተው የሚሹኝ ያገኙኛል!

ሉተር ለረጅም ጊዜ በፍለጋ ተግቶ ነው ለብዙዎች የመዳን ምክንያት የሆነው ብርሃን ልቡ ላይ የፈነጠቀው፡፡ ጰጳሱ ጆን ፓል 11 (Pope John Paul 11) ሉተርን “a profoundly religious man” ብለውታል፡፡ ይሁን እንጂ በውስጡ ብዙ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ በመሆኑም ሳያሰልስ እውነትን ፍለጋ ላይ ተጠምዶ ነበር፡፡

ሉተር በቀን ለሦስት ሰዓት ያህል የመጸለይ ልማድ የነበረው ሲሆን፣ በየአንድ ሰዓቱ ንስሐ ይገባ ነበር፡፡ አዘውትሮ በመጾሙም ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ውስጡ ምንም ዕረፍት አልነበረውም፡፡ እንዳውም በኃጢአተኝነት ስሜት ይከሰሰስ ስለ ነበር ስቃይ ውስጥ ነበር የቆየው፡፡ በዚያ ከባድ ሁኔታ ውስጥ እያለ፣ “ጻድቅ በእምነት በሕይወት ይኖራል፡፡” (ሮሜ.1፥17) የሚለውን ምንባብ ሲያነብብ በመገረም ልቡ ይሸበር ነበር።

የእግዚአብሔር መንፈስ በዚሁ ቃል ደጋግሞ ተናግሮታል፤ ጥርት ብሎ አልገባውም እንጂ! ከረጅም ጊዜ በኋላ አንድ ልዩ የሆነች ቀን ላይ ግን በሚገርም ሁኔታ የቃሉ ፍቺ ልቡ ላይ ፏ ብሎ በራ፡፡ እናም የወንጌል ዋና መልእክት ወለል ብሎ ገባው፡፡ በዚያም የእግዚአብሔርን ጸጋ በሚገባ ስላስተዋለ፣ ሰው በሥራው ሳይሆን፣ በእምነቱ እንደሚጸድቅ ተረዳ፡፡ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን!

ለመሆኑ ይህ የእርሱ ፍለጋ (search) ምን ያስተምረናል? ጌታ በቅንነትና በትሕትና የሚሹትን እንደማያሳፍር ነዋ! ስለሆነም ነው የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ የሚለን፡-

➢ “እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል።” (ምሳ.8፥17)፤

➢ “አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትሻላችሁ፤ በልብህም ሁሉ በነፍስህም ሁሉ የፈለግኸው እንደ ሆነ ታገኘዋለህ።” (ዘዳ.4፥29)፤

➢ “አንተም፥ ልጄ ሰሎሞን ሆይ፥ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና፥ የአባትህን አምላክ እወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ።” (1ዜና.28፥9)፡፡

መልካም ጊዜ ተባረኩ!
Dr. Beke
@nazrawi_tube