Get Mystery Box with random crypto!

እግዚአብሔር ያስታውሳል! በዘገየ የጸሎት መልስና በእግዚአብሔር ዝምታ አንዳንድ ጊዜ ልባችን በተስ | ናዝራዊ Tube

እግዚአብሔር ያስታውሳል!

በዘገየ የጸሎት መልስና በእግዚአብሔር ዝምታ አንዳንድ ጊዜ ልባችን በተስፋ መቈረጥ ይሞላል። በሕይወታችን “ዝምታዎችም” መካከል እግዚአብሔር በሉዓላዊነቱ በሥራ ላይ ነው። ልጅን ያለመወለድ ከርግማን፣ ከኀጢአት ወይም የእግዚአብሔር ሞግስ ከማጣት ጋር በሚያቆራኝ ማኅበረ ሰብ ውስጥ፣ ዘካርያስና ባለቤቱ ኤልሳቤጥ በታማኝነት ያገለግሉ ነበር። ይህ በነበሩበት ማኅበረ ሰብ ትውፊትና መንፈሳዊ ዐውድ ከባድ “መሰቀል ነበር”። “ለምን እግዚአብሔር ዝም አለ?”፣ እፍረታችንንስ ለምን “አይመለከትም?” የሚሉት ጥያቄዎች ዘወትር በነዝናዥነት ይከተሏቸው ነበር። አስነካሽ፣ ቀና የማያሰኙና ልብ አዛይ መልስ የሌላቸው ጥያቄዎች ነበሩ።

ኾኖም፣ እየታገሉም በመሰጠት ጌታን ያገለግሉ ነበር። በኋላ እንደምናስተውለው ያገለግሉ የነበረበት ቤተ መቀደስና መሪዎቹ በብዙ መፈሳዊ ቀውስ ውስጥ ነበሩ። ለማገልገል ቀርቶ ለማምለክም ዐቅም የሚያሳጣ መንፈሳዊ ብሉሽነት እንደ ነበረ ጌታ ቤተ መቀዱስን ሲያጸዳ ከተናገረው መገመት ይቻላል፦

“ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ ሻጮችን ከዚያ አስወጣ፤ ደግሞም “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት።” (ሉቃስ 19፥45᎓6)።

ይሁን እንጂ በዚህም ልብን በሚጥል ሁኔታ ውስጥም ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ስሜታቸውን በመከተል ሳይሆን፣ እግዚብሔርን ተመልካች በማደረግና ልባቸውንም በእርሱ ሉዓላዊነት ላይ በማሳረፍ እያመለኩ ያገለግሉ ነበር። ዋጋቸው እርሱ ብቻ እንደሆነ ተገንዝበዋልና! እንደሚመስለኝ በዚህ ወቅት ስለ ልጅ መጸለይ አቁመዋል። የሚመለስ አይመስልም ነበርና። ስለዚህ ጸሎታቸው በመሲሑ መምጣት ስለሚሆነው የእግዚብሔርን ጕብኝት ይመስለኛል። በአጭሩ “መንግሥትህ ትምጣ” ሳይሆን አይቀርም። ከስምዖን ጸሎት እንደምንረዳው ይህ የትሩፋኑ ሕዝብ የመለኮታዊ ጕበኝት ናፍቆትና ጕጕት ነበር።

“በዚያን ጊዜ ጻድቅና ትጉህ የሆነ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው በኢየሩሳሌም ይኖር ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን መጽናናት የሚጠባበቅና መንፈስ ቅዱስ በላዩ ያደረ ሰው ነበር።” (ሉቃስ 2፥25)

እኛ በምንፈለገው መንገድ ወይም ጊዜ ባልተመለሰ ጸሎትና የሕይወት እንቆቅልሽ ውስጥ እግዚአብሔር ተመልካችና አድማጭ በማድረግ እንድናመልከና እንደናገለግል የሚያስችል የጌታ ጸጋ አለ። ለዘካርያስና ለኤልሳቤጥ ዘመን መጣ - የእግዚአብሔር ጊዜ። ራሱ በወደደው ጊዜ በድነት ታሪክ ውስጥ በሕይወታቸው ውስጥ የነበረው ዝምታ ተሰበረ። በእግዚአብሔር የድነት ዓላማ ውስጥ ዮሐንስ መምጣት ነበረበት። ይህ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ካሰቡት፣ ከጠበቁትና ከተመኙት በላይ ትልቅ ዕቅድ ነበር። የእግዚአብሔር መግሥት በደጅ ነበር!

“የጌታም መልአክ ከዕጣን መሠዊያው በስተ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፤ በፍርሀትም ተዋጠ። መልአኩ ግን እንዲህ አለው፤ “ዘካርያስ ሆይ፤ አትፍራ፤ ጸሎትህ ተሰምቶአል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። በእርሱ ተድላና ደስታ ታገኛለህ፤ ብዙዎችም እርሱ በመወለዱ ደስ ይላቸዋል፤ በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና። ከእስራኤልም ሰዎች ብዙዎቹን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳቸዋል፤ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆቻቸው፣ የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ፣ ለጌታ የተገባ ሕዝብ ለማዘጋጀት በኤልያስ መንፈስና ኀይል በጌታ ፊት ይሄዳል።” (ሉቃስ 1፥11-16)

ሳይመለስ በዘገየ ጸሎት ልባችሁ የዛለና ለጊዜው መልስ ከሌለው ውስብስብ ችግር ጋር የምታገለግሉ ትኖሩ ይሆን? ያልታየን ስንመስል፣ በርግጥ እርሱ ያየናል! ያልተሰማስን ሲመስለን በርግጥ እርሱ አስቀድሞ ሰምቷናል። ሕይወት በዝምታና በጸጥታ ስትዋጥና የእግዚአብሔር አብሮነት ሳይሰማንም ሲቀር እግዚአብሔር በአጠገባችን አለ። በቅንነትና በታማኘት እናምልከው፤ እናገልግለውም! እንደ ስሙ፣ ዘካሪያስ - እግዚአብሔር ያስባል፤ እግዚአብሔር ያስታውሳል፤ እግዚአብሔር ይመለከታል።

አሜን!
Dr. Girma Bekele
@nazrawi_tube