Get Mystery Box with random crypto!

በፈረንጆች አቆጣጠር በግምት 2008 ዓ.ም በአራት ኪሎ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት | ናዝራዊ Tube

በፈረንጆች አቆጣጠር በግምት 2008 ዓ.ም በአራት ኪሎ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አዳራሽ ሁለት ሺህ ለሚሆኑ የኮሌጅ/ ሃይስኩል (?) ክርስቲያን ተማሪዎች ኢቫሱ ባቀረበልን ጥያቄ መሰረት እኔ ሰሎሞን ጥላሁን፣ ወንድም ምኒልክ አስፋውና ወንድም ተስፋዬ ሮበሌ ስለ Secret / "ሚስጥሩ" ትምህርት እንድናቀርብ ተጠይቀን አቅርበን ነበር፡፡

አሁን በዚህ ሰሞን ወንድም ጌታነህ ሔራሞ ያቀረበውንም ሙግት ተመለከትኩና ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ የሁላችንም ዘመን ጩኸት አንድ ኣይነት መሆኑ አስደነቀኝ

አሁን ሚስጥሩ ግልጥ ሆኖ አገር እያተራመሰ ስናይ "ይህ ህዝብ..." በሚል ስሜት ተይዘናል፡፡ ያን ጊዜ እኔ ያቀረብኩትን ወረቀት ከድሮው ፎንት እንደምንም ለመቀየር ሞክሬ የሚከተለውን መክፈቻ ንግግር አገኘሁና አንድ ገጽ ለምትታገሱ አንባብያንና ምናልባት ከሁለት ሽሆቹ ጥቂቶች ካላችሁ ለማስታወስ እነሆ ልበለችሁ... የዛሬ 15 ኣመት ከተናገርኩት ላይ አንዲት ፊደል እንኳ አልጨመርኩበትም!

[በመጻሕፍት ገበያ እሽቅድድም በድንገት ፈትልኮ የወጣ፣ ቀድመውት ከወጡ አቻዎቹም ከእነ ዳቬንቺ ኮድና ሃሪ ፖተር ይልቅ በድንገት የገበያውን ማእበል ያግለበለበ መጽሐፍ ነው። ርእሱ መልስ ፈላጊ ለሆነው የሰው ልጅ አእምሮ ማራኪ ነው ቀለሙና የሽፋኑ ገጽታ በዘይት ያማረ ጥርብ ጣውላ ይመስላል፣ ደምቆ ዓይን አይወጋም፣ ፈዞም አይሰወርም።

በመጽሐፉ ውስጥ የተነሱ ርእሰ ጉዳዮች አይመለከተኝም የሚል ከቶውንም ቢሆን አይኖርም። የጥረትና የግረት ምክንያቶች በመሪ ርእሰ ጉዳይነት ከነፈጣን መፍትሔአቸው ተዘርዝረዋል። እሺ ባይ ሁሉ ተጠቃሚ እንደሆነ ሙሉ ተስፋ ይሰጣል። ደሃን እንደሚያበለጽግ፣ ባለጠጋን እንደሚያናጥጥ፣ በሽተኛን እንደሚፈውስ፣ ጤነኛን እንዳይታመም እንደሚያደርግ የጠበቀና የማያወላዳ ተስፋ ይሰጣል።

በትዳር በሥራ በሕይወትህ ወይ ደግሞ ገንዘብ በማጣት አዝነሃል? አዕምሮህን ተጠቀም የተሻለውን ማንነትህን አስብ ፕዘቲቭ አስተሳሰቦች ይለውጡሃል የምታውቃቸውን ማንኛውንም ዓይነት መልካም ነገሮች ሁሉ ይስቡልሃል ይህ የማይታመን ይመስልህ ይሆናል ግዴለም ደግመህ አስብ በሳይንስም የተደገፈ ነውና
ታዋቂው የሲ ኤን ኤን ቶክ ሾው አቅራቢ

ታዲያ እርሱ እንዲህ ያስተዋወቀውን መጽሐፍ ማን በቀላሉ ያየዋል!

በእንግድነት በሔድኩበት በአንድ ቤ ት ውስጥ ከአልጋው ፊት ለፊት በቁም ሳጥኑ ከፍ ባለ የመዝጊያ ጠርዝ የተለጠፉ ሁለት ብሮች አየሁ የመለጠፋቸው ምክንያት የገባኝ ከጥቂት የቆይታ ቀናት በኃላ ነው በዚያ ቤት ውስጥ ነዋሪ የሆነ ወጣት ካነበበው አንድ መጽሐፍ የተነሣ የብር ሐሳብ ብርን ይስባል ለዚህም ብርን ግድግዳ ላይ ለጥፎ ማፍጠጥ ወይም ስለ ብሩ ማሰላሰል የብር ሐሳብን ወደ ብር ይለውጣል

በውጪ አገር የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ የኮሌጅ ተማሪ ቡና እየጠጣን ስለ ትምህርት ቤት ጉዳይ ስናወራ የአንድ ትምህርት ፕሮፌሰር ቫይብ /ቫይብሬሽን/ ወይም ከውስጡ የሚወጣው ነዛሪ ኤሌክትሪክ ሲያስቸግረው እንደ ከረመ አጫወተኝ ምንድን ነው ይሄ ቫይብ ብዬ ብጠይቀው የሰውየው ኔጋቲቭ የኤሌክትሪክ ንዝረት ከእኔ ከሚወጣው ጋር በመጋጨት ተጽእኔ ያሳድርብኛል በኃላ ሁኔታውን ሳጣራ የሚከተለው አንድ ህቡዕ /ስውር/ እምነት ያለው ሰው እንደሆነ አወቅሁ

«ሚስጥሩ´ ሚስጥሩ አንድ ነው እርሱ ሃይማኖታዊ መልእክት ነው መልእክቱም ሰው አምላክ ነው የሚለው ነው ለዚህ ነው ኢ አማኒያኑ /ኢቲስቶች/ የዚህ መጽሐፍ መልእክት ከሌሎች ሃይማኖች ይልቅ ያሳሰባቸው ምክንያቱም አሁን በሚስጥሩ የተነሳ ነባሩ አምላክ አለወይም የለም የሚለው ክርክር ሰው አምላከ ነው ወይስ አይደለም ወደሚለው ዞሯልና ነው

ዘ ሴክሬት የተባለው መጽሐፍ በቁሳዊው ዓለም ስላሉ ልዩ ልዩ ስኬቶችና የማግኛ ቀመራቸው /ፎርሙላ/ አኮብኩቦ ተሳፋሪውን ከያለበት ስፍራ ስበትን አስለቅቆ ሲያንሳፍፍ ከዋለ በኃላ ወደ ማክተሚያው ሲደርስ አንተ አንቺ አምላክ ነህ ከዚህ በኃላ በራስህ መንገድ ማረፍ ትችላለህ በማለት በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ተሳፋሪዎቹን አየር ላይ ጥሎአቸው የሚሔድ በራሪ ቅዥት ነው:: ይሁን እንጂ በርካታ ክርስቲያናዊ ቃላትን በመውሰዱ አስተሳሰቡ በሙሉም ሆነ በከፊል ያመነው ማሕበረሰብ ውስጥ ለመግባት ያመቸዋል በተለይም የእምነትን ትምህርት በተለጠጠ መልኩ በሚያስተምሩት ቤተ ክርስቲያኖች አካባቢ ከምስባኩ /ከመድረኩ/ የተለመዱ ቃላትን ስለሚጠቀም እነዚህ ቤተ ክርስቲያኖች ትምህርቶቻቸውንና የሚጠቀሙባቸውን ቃላት ሊመረምሩ ይገባል ...]

መጋቢ ሰለሞን ጥላሁን
@nazrawi_tube