Get Mystery Box with random crypto!

ዴይስቶቹ ዴይዝም (Deism) በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው ግንኙነት 'በመገለጥ' (Reve | ናዝራዊ Tube

ዴይስቶቹ

ዴይዝም (Deism) በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለው ግንኙነት "በመገለጥ" (Revelation) ላይ ሳይሆን "በአመክንዮ" (Reason) ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት ብሎ የሚያምን  በዘመነ "አብርሆት" (enlightenment) የምዕራቡን ዓለም አስተሳሰብ ቅርፅ ያስያዘ "ሃይማኖት ቅብ" ፍልስፍና ነው። የፍልስፍናው ተከታዮችም በስነ መለኮት ምሁራኑ ዘንድ "ዴይስቶች" ተብለው ይጠራሉ።

ታዲያ ዴይስቶቹ ትምህርታቸውን የሚጀምሩት "አፅናፈ ዓለሙን የፈጠረው ፈጣሪ አለ" ብለው ነው። ነገር ግን "ይህ ፈጣሪ መላለሙን ከፈጠረ በኋላ የፈጠረውን ፍጥረት በሙሉ "ለተፈጥሮ ህግጋት" አሳልፎ ሰጥቶታል። ስለዚህ ፈጣሪ በዕለት ተዕለትም ሆነ በአጠቃላዩ የሰው ህይወትና ኑሮ ውስጥ ጣልቃ እየገባ የሰውን ህይወት አይመራም አይቆጣጠርም። ፍጥረተ ዓለም የሚተዳደረው በራሱ "የተፈጥሮ ህግጋት" ነውና ብለው ያስተምራሉ።

ዴይስቶቹ ይህንኑ አቋማቸውንም በምሳሌ ሲያስረዱ፤ "እግዚአብሔርን እንደ ሰዓት ሰሪ ቁጠሩት" ይላሉ። ሰዓት ሰሪ ሰዓቱን ይሰራና ይሸጥልናል እኛም ሰዓቱን ይዘን ወደ ቤታችን እንሄዳለን። ሰዓቱም በራሱ ጊዜ ይዞራል (ይቆጥራል) እንጂ ሰዓት ሰሪው ቤታችን እየተመላለሰ አያዞርልንም። "ፈጣሪም" እንዲሁ ነው፤ ተፈጥሮን ፈጠረና "ለተፈጥሮ ህግጋት" ሰጠው። "የተፈጥሮን ህግጋት አውቀህ መኖር ታዲያ የአንተ ድርሻ ነው። ህይወትህ በእጅህ ናት! ማለታቸው ነው። ዴይስቶቹ።

በነገራችን ላይ ዴይዝም "የቃል እምነት" ወይም "የብልፅግና ወንጌል" ስሁት አስተምህሮ "ቅድመ አያት" ነው። ለዚያ ነው ከቃል እምነት መምህራን መካከል እንደ ማይልስ ሞንሮይ ያሉት "እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚሰራው እኛ ስንፈቅድለት ነው" በማለት እግዚአብሔር በምድር ባለ ጉዳይ "አያገባውም" የሚል ዓይነት የድፍረት ቃል የሚጠቀሙት። እንዲሁም "በአንደበታችን ቃል" (word of faith) "የተፈጥሮ ህግጋቱን" አንቀሳቅሰን የምንፈልገውን ሁሉ ማግኘት እንችላለን የሚሉት ። (ትይይዙን በቀጣይ ልጥፍ   እመለስበታለሁ)

ችግሩ ምንድነው?

ታዋቂው የስነ መለኮት ምሁር ኤን. ቲ. ራይት "ዴይዝም የኤቲዝም (እግዚአብሔር የለሽነት) ምንጭ ነው ብሎ ያምናል። ራይት ሲናገር "ዴይዝም በመጀመሪያ የመፅሐፍ ቅዱሱን እግዚአብሔር እንደ ባላባት (Landlord) እንድትቆጥረው ያደርግሃል። ቀጥሎ ይህ ባላባት (Landlord) የሆነ እግዚአብሔር በሰርክ ኑሮህ ውስጥ የለም ይልሃል። በመጨረሻ እግዚአብሔር ራሱ የለም ይልሃል" ብሏል። እውነቱን ነው። እግዚአብሔር በሰርክ ህይወታችን ላይ መሪ እና ተቆጣጣሪ ካልሆነ በጊዜ ሂደት "እግዚአብሔር የለም!" የማንልበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ስለዚህ አንዱ እና ትልቁ ችግር ዴይዝም "ለእግዚአብሔር የለሽነት" አስተሳሰብ መንገድ ጠራጊ መሆኑ ነው።

ሌላው ችግር፤ ዴይስት (Deist) ስትሆን "ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን" ብለህ መፀለይ አለመቻልህ ነው። "እግዚአብሔር በሰማይና በምድር የወደደውን አደረገ" ብለህም አታመሰግንም። "እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ" እያልህ ለእግዚአብሔር ስልጣን እውቅና አትሰጥም። ዴይስት ስትሆን ተንበርክከህ "ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?" ብለህ እግዚአብሔርን አትለምንም። "እግዚአብሔር እረኛዬ ነው" ብለህም አትዘምርም።

ዴይስት ስትሆን "እግዚአብሔር ምን ይፈልጋል" ሳይሆን "እኔ ምን እፈልጋለሁ" ብለህ ነው ህይወትህን የምትቃኛት። በአይምሮህ ብቻ ነው የምትመራው። ዴይዝም በተፈጥሮ ህግጋት ተጠቅመህ የመረጥኸውን ማምጣት የጠላኸውን ማስወገድ የምትችልበትን ሃይል እንደ ተጎናፀፍህ  እንድታስብ ያደርግሃልና።

በአጭሩ "ዴይዝም" በክርስትናችን ውስጥ መሠረታዊ የሆነውን "እግዚአብሔርን የመታዘዝ" እና "ለእግዚአብሔር ክብር" የመኖር ፍላጎታችንን የሚቀማና "ትዕቢተኛ" የሚያደርግ ክፉ ትምህርት ነው።

ከስር በፎቶው ላይ የምትመለከቷቸው ዳዊትም እና ዳጊ "ዴይስቶች" እንደሆኑ "በአወንታዊ የአስተሳሰብ ሃይል የተፈጥሮ ህግጋትን በመጠቀም ሃብትም ሆነ የምትፈልገውን ነገር ሁሉ" ማግኘት ትችላለህ" በሚለው ዘውትራዊ ትምህርታቸው እና "አነበብናቸው፣ መመሪያዎቻችንም ናቸው" በሚሏቸው መጻሕፍት እንዲሁም "ጀግኖቻችን ናቸው!" እያሉ በሚጠቅሷቸው ሰዎች በቀላሉ መለየት ይቻላል። ዶ/ር ወዳጄነህም በተለያዩ መድረኮች ላይ በሚያቀርባቸው መርኸ አልባ (አይጨበጤ) "አነቃቂ" ንግግሮቹ እንዲሁም ከዳዊትና ከዳጊ ጋር ከፈጠረው ጥምረት ዴይስት እንደሆነ ማወቅ ይቻላል። (ታዲያ ጥንታዊያኑ ዴይስቶች በፎቶው ላይ እንደሚታዩት እና መሰሎቻቸው በገንዘብና በዝና ፍቅር የወደቁ ነበሩ ለማለት አይደለም)

ስለዚህ ሰሞነኛው የሶስቱ ሰዎች ጥምረትና ዘመቻ ምንም እንኳ ዓለማዊ (Secular) ቢመስልም፤ "ሃይማኖት ቅብ" የሆነው፣ "ፈጣሪ" ወይም "አምላክ" የሚሉ ቃላትን ለማታለያነት የሚጠቀመው፣ "ለአዲሱ አስተሳሰብ" (New Tought) እንዲሁም "ለቃል እምነት እንቅስቃሴ" መሠረት የሆነው
"የዴይዝም" (Deism) ፍልስፍና በሀገራችን እየተስፋፋ መምጣቱን አመላካች ስለሆነ ቅዱሳን ወገኖች በተለይ ወጣቶች "ከቃል እምነት" ስሁት ትምህርቶች ብቻ ሳይሆን እንዲህ ካለ ዘመናዊ አስተሳሰብ መስሎ ከሚቀርብና ወደ "ትዕቢት"  ብሎም ወደ "ክህደተ እግዚአብሔር" ከሚመራ "የዴይስቶች" ትምህርት ተጠበቁ ለማለት እወዳለሁ።

ከዴይስቶቹ ተጠበቁ!!

ቴዎድሮስ ተጫን
@nazrawi_tube