Get Mystery Box with random crypto!

እንደምን አደርን። እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ከአንዳንድ ጉድ ውስጥ ቶሎ መንጥቆ ያወጣናል፡ አንዳ | ናዝራዊ Tube

እንደምን አደርን።

እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ከአንዳንድ ጉድ ውስጥ ቶሎ መንጥቆ ያወጣናል፡ አንዳንዴ ግን ብዙ ስንፍጨረጨርና ስንጨነቅ እያየ ዝም ይልና በራሱ ጊዜ ያወጣናል፡ ሌላ ጊዜ ጭራሹኑ ላያወጣን ሁሉ ይችላል፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁና መጽሃፍ ቅዱሳዊው ምክንያት የሚመስለኝ እግዚአብሔር የገባንበትን ጭንቅ ወይም መከራ ወይም "የተወላገደ" የሕይወት መንገድ ክብደት እያየ ሳይሆን የሚሰራው የገባንበት ነገር እርሱ የሚፈልገውን ነገር በሕይወታችን ሰርቶአል ወይ በሚለው መስፈርት መሆኑ ነው፡ መፈተናችንን ወይም መጨነቃችንን አይወድም ነገር ግን እጅግ ለተሻለው ጉዳይ በእኛ ሕይወት ዝም ይላል።

የዕብራውያን ጸሃፊ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፦

"እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው"

ኢየሱስ በስጋው ወራት በብዙ ጣርና እንባ ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ቃተተ፡ ነፍሴ እስከሞት ድረስ ተጨነቀች አለ፡ ጸለየ፡ ይህች ጽዋ ብትወድ ከእኔ ትለፍ ብሎ ለመነ፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሞትን አልወሰደለትም ወይም ሐሳቡን አልቀየረም፡ ነገር ግን የዕብራውያን ጸሃፊ "እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት" ይለናል፡ እግዚአብሔር የኢየሱስን ልመና የሰማው በሞት ውስጥ አሳልፎ ከሞት በማስነሳት ነው እንጂ ሞትን በማስወገድ ወይም ጽዋውን በማንሳት አልነበረም፡ ኢየሱስን ሰምቶታል ግን እኛ በምንጠብቀውና በምንፈልገው መልኩ አይደለም የሰማው፡ በጭንቅ ውስጥ እያሳለፈ ነበር የሰማው፡ እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት አስነሳው ደግሞም በዛ ሞት ሊሰራ የሚፈልገውን ስራ ሰራ፡፡

ኢየሱስ "አምላኬ አምላኬ ስለ ምን ተውኸኝ" ብሎ ሲቃትት እግዚአብሔር "ዝም" ያለው ወይም ጣልቃ ያልገባው በዛ መንገድ የሚሰራው ስራ ስለነበረው ነው፡ ልጁን ረስቶት ወይም ጠልቶት ሳይሆን በዛ ህመም ውስጥ የብዙዎችን ፈውስ ስላየ ነው፡ ስለ ልጁማ ምን ጥርጣሬ አለ "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ እርሱ ነው" ብሎ መስክሮለታል፡ ታዲያ መስቀል ላይ ጠልቶት ነው? ፈጽሞ!

የተበላሸ ወይም የተጣመመ በሚመስለው መንገድ እግዚአብሔር ጣልቃ አልገባም ማለት ረስቶናል ማለት አይደለም፡ ለእኛ ባይመስለንም እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከመጋረጃው በስተጀርባ ስራውን ይሰራል፡፡

የቲአትር ቤቱ መብራት ሲደበዝዝ ተመልካቹን ጨለማ እንዲውጠው ተፈልጎ ሳይሆን የመድረኩ ተውኔት በደንብ ተግ ብሎ እንዲታይ ስለሚፈለግ ነው።

እግዚአብሔር በህይወትህ ጣልቃ አልገባም ማለት ረስቶሃል ማለት ሳይሆን መስራት የሚፈልገውን አልጨረሰም ማለት ነው፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ የሚኖረን ብቸኛ አማራጭ በእርሱ ላይ መታመን ብቻ ነው፡ ልክ ኢየሱስ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ እንዳለ እንዲሁ እኛም በምናልፍበት የህይወት መንገድ ያለን ወሳኝ ምርጫ በስተመጨረሻ ታማኝነቱን ለሚያረጋግጠው እግዚአብሔር ነፍሳችንን አደራ አሳልፎ መስጠት ነው።

እግዚአብሔር ከአንድ መከራ መንጭቆ ከሚያወጣን ይልቅ መከራው በእኛ ህይወት ለሚሰራውና ለምንማረው እውነት ቅድሚያ ይሰጣል።

ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ።

በምናልፍበት መንገድ እግዚአብሔርን እያሰብን መጽናት ይሁንልን።

ሰላምና ጸጋ ለሁሉም።

ይልቃል ዳንኤል
@nazrawi_tube