Get Mystery Box with random crypto!

በእግዚአብሔር ተስፋ አይቆረጥም! እግዚአብሔር አዲስ ጅማሬንና አዲስ ዕድልን በመስጠት የታወቀ ነው | ናዝራዊ Tube

በእግዚአብሔር ተስፋ አይቆረጥም!

እግዚአብሔር አዲስ ጅማሬንና አዲስ ዕድልን በመስጠት የታወቀ ነው፡፡ እግዚአብሔር የእንደ ገና አምላክ ነው፡፡ የሐዋርያው ጳውሎስን ሕይወት ስናይ፣ ከዚያ ከሞተ ሃይማኖታዊ የጥፋት ወጥመድ (ያለ ኢየሱስ) አውጥቶ፣ ታሪክ እንዲሠራ አድርጐታል፡፡ ሁለት ሦስተኛው የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት በእርሱ የተጻፉ አይደሉምን? ሐዋርያው ጴጥሮስም ከዚያ ውድቀትና መሪር ኀዘን በኋላ፣ በባለ ሃምሳ ቀን አስደናቂ ሰባኪ ሆኖ አልተገለጠምን? ለምን? እግዚአብሔር ለሰዎች እንደ ገና አዲስ ዕድል መስጠት ያውቅበታልና ነው፡፡

የመጽሐፍ ቅዱሷን ሩት ያየን እንደሁ፣ ባሏ የሞተባት፣ መሄጃ የሌላት ሴት ነበረች፡፡ ሕይወቷም ተስፋ የማይጣልበት እጅግ ባዶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከምትገምተውና ከምታስበው በላይ የሆነ አዲስ ሕይወትን አግኝታለች፡፡ ለምን?

አምላካችን እግዚአብሔር "በዚህ ብቻ ነው የሚሠራው" ስለዚህም "አለቀ" ብሎ መደምደም አይቻልም፤ እጅግ ብዙ መንገዶች አሉትና፡፡ በፍጹም ያልጠበቅነውን መስመር ዘርግቶ፣ ሕይወታችንን እንደ ገና ማስዋብ ይችልበታል፡፡

በግሌ ከዚህ በኋላ አበቃልኝ ያልኩባቸው እጅግ በርከት ያሉ ጊዜያት እንደ ነበሩ አልደብቃችሁም፡፡፡ የተዘጉ በሮችን አይቼ “በቃ፣ ከዚህ በኋላ የእኔ ነገር አበቃ” ብዬ አውቃለሁ፡፡ ያኔ በአእምሮዬ እንደ ሰው መውጫ አማራጮችን ፈታትሼ፣ ዝርክርኬ የወጣባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ ነገር ግን ወደ ልቤ ተመልሼ፣ የእኔ መፍትሔ ከላይ ብቻ እንደ ሆነ ገብቶኝ፣ በፊቱ በቂ ጊዜ ወስጄ በማሳለፍ፣ በማልቀስ፣ በመቃተትና በመጮኽ ለረጅም ጊዜ በማሳለፍ የሚደንቁ ትንሣዔዎችን አይቼአለሁ፡፡

ወገኖቼ ሕይወት ባዶ ሆኖባችሁ፣ ልትሄዱባቸው ያሰባችሁባቸው መንገዶች ተዘጋግተውባችሁና ሕይወት አስጠልቷችሁ ካላችሁ፣ የምነግራችሁ አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ምንም ሳታወላውሉ፣ ምንም ሳታመነቱ፣ በመሐሪው አምላክ ፊት ውደቁ፡፡ እናም "የተበጠሱ ጅማቶች እንደ ገና ሙዚቃ የሚያሰማ ድምፅ ይሰጣሉ (Chords that were broken will vibrate once more) !!

መልካም ጊዜ ተባረኩ!
Dr. Bekele brihanu
@nazrawi_tube