Get Mystery Box with random crypto!

ዕለተ ዓርብ - ስቅለት፤ ሞት፤ ጨለማ፤ ስርየት ጌታ፣ 'ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእ | ናዝራዊ Tube

ዕለተ ዓርብ - ስቅለት፤ ሞት፤ ጨለማ፤ ስርየት

ጌታ፣ "ይህን ጽዋ ከእኔ አርቀው፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን” አለ። ተከዳ፤ ተሸጠ፤ ተተወ፤ በአንድ ወቅት ይከተለው የነበረውና “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤” “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤” “ሆሣዕና በአርያም!” እያለ ያከበረው ሕዝብ “ይሰቀል!” በማለት አሳልፎ ሰጠው፤ ልብሱን ተገፈፈ፤ የእሾኽ አክሊል ተደፋበት፤ በወንበዴዎች መካከል ተሰቀለ፤ ተሰደበ፤ ተሾፈበት፤ ተጨነቀ፤ ተሠቃየ፤ እንደ ጠቦትም ለዕርድ ተነዳ፤ በሸላቾች ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ አፉን አልከፈተም፤ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” እያለ ጮኸ፤ ጨለማ ወረሰው!

መድቀቁና መሠቃየቱ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር። የመስዋዕቱም በግ፣ ካህንም ሆነና ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ ጫነው። ደዌያችንን ወሰደ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ ተሠቃየም፤ ስለ መተላለፋችን ተወጋ፤ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የብዙዎችን ኀጢአት ተሸከመ፤ ስለ ዐመፀኞችም ማለደ። ለአሰቃዮቹ ሁሉ፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት ጣር ውስጥ ማለደ። የፍጥረት ፈጣሪ፣ ተጠማ፤ በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ፤ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ፤ ድነት ኾነ! በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።

ዕለተ ቅዳሜ - መቃብር፤ ታላቅ ዝምታ

አምላክ ወደ መቃብር ወረደ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አይችልም!” ተባለ። "የታመነበት እግዚአብሔር ትቶታል" ተባለ፤ ስለራሱ የተናገረው ሐስት፣ የሰጠውም ተስፋ መና ነበር ተባለ። በልመና በድኑ ተቀበረ! በትልቅ ድንጋይ የመቃብሩ በር ተዘጋ፤ መቃብሩን በማኅተም አሽገው ጠባቂ አቆሙበት፤ ታሪኩ ተዘጋ፤ ፍርሃት ወደቀ፤ ላመኑበትና ለተከተሉት ጨለማ ኾነ፤ እግዚአብሔር ዝም ያለ፣ ሞትም ለዘላለም የነገሠ መሰለ፤ ተስፋ ሁሉ ተሟጠጠ። ታላቅ ዝምታ ኾነ!

ዕለተ እሁድ - ትንሣኤና ሕያው ተስፋ

እንደ ተናገረው ተነሣ፤ ድንጋዩ ተንከባለለ፤ መቃብሩ ባዶ ኾነ፤ በፈቃዱ ነፍሱን ሰጠ፤ እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አስወግዶ አስነሣው፤ ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለምና! ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ደመሰሰ፤ ጨለማው ነጋ! ልቅሶ በደስታ ተለወጠ፤ ፍቅር አሸነፈ፤ ወዳጆቹን ፍለጋ ሄደ። በፍርሃት በተዘጋ ደጅ የለበሩት “ሰላም ለእናንተ ይሁን አለ!” ስብራታቸው ጠግኖ፣ ተስፋቸውንም አድሶ ወደ ዓለም ሁሉ ላካቸው። ከአምላክ ጋር ዕርቅ ሆነ፤ ድነታችን ሙሉ ኾነ፤ ተስፋችንም ዘላለማዊና ሕያው! ያለ ትንሣኤው፣ ክርስቶስ ሰማዕት፣ መልክታችንም ታሪክ ብቻ ነበር የሚሆነው! ሞት በድል ተዋጠ፤ የሞት መንደፊያ ኀጢአት ተወገደ፤ ሰይጣን ተረታ። እንደ ተናገርው ሞተ፤ እንደ ተናገረው ተነሣ፤ እንደ ተናገረው ወደ ሰማይ ዐረገ፤ እንደ ተናገረው መንፈስ ቅዱስን ላከ፤ እንደ ተናገረው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእኛ ጋር አለ፤ እንደ ተናገረው በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ፣ በክብር ይመለሳል!

እንደ ግል አማኝ፣ እንደ ቤተ ሰብ፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን፣ እንደ አገር የምናልፍባቸው ብዙ የፈተና ወቅቶች አሉ። በእግዚአብሔር የተተውን፣ እርሱም የማያየን፣ ዝም ያለን፣ እንዲሁም ይህቺ ምድር ለክፉዎች ዐልፋ የተሰጠች እስኪመስል ድረስ የፍትሕ ጨኸት የማይሰማበት፣ ክፋት ያሸነፈና ሰይጣን ለዘላለም የነገሠ የሚመስልባቸው የተስፋ መቁረጥ፣ የዝምታና የጨለማ "ዓርቦችና ቅዳሜዎች" አሉ።

ሆኖም፣ "ዓርብና ቅዳሜ" የመጨረሻ ቃሉች አይደሉም! የእኛም ኾነ የመላ ዓለሙ ታሪክ በእነዚህ ሁለት ቀናት በሆኑ ኹነቶች አልተቋጨም። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተነሥቶአል! ስለዚህ ይቅር መባላችን፣ የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን፣ የትንሣኤ ተስፋችን፣ ከአቤል ጀምሮ እስከ አሁን እየፈሰሰ ያለው የንጹሓን ደም ጩኸት ምላሽ ማግኘቱ፤ መከራ መወገዱ፤ እንባ መታበሱ፣ ኀጢአት፣ ሞትና ሰይጣን ለዘላለም መወገዳቸው፣ በመጨረሻም አዲስ ሰማይን አዲስ ምድር የማየታችን ተስፋዎች እውነት ናቸው። እንደ ተናገረው ይመለሳል!

“እነዚህን ነገሮች የሚመሰክረው፣ “አዎ፣ ቶሎ እመጣለሁ” ይላል። አሜን፤ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ና። የጌታ የኢየሱስ ጸጋ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ይሁን፤ አሜን።” (ራእይ 22:20-21)

መልካም የትንሣኤ በዓል!
Dr. Girma bekele
@nazrawi_tube