Get Mystery Box with random crypto!

ኢየሱስ በየትኛው ቀን ነው የተሰቀለው? . . . ከሞተ በኋላስ የት ነበር? (ኢ. ማ.) ይህ አ | ናዝራዊ Tube

ኢየሱስ በየትኛው ቀን ነው የተሰቀለው? . . . ከሞተ በኋላስ የት ነበር? (ኢ. ማ.)

ይህ አሳብ አምና በጥቂቱ፥ ዘንድሮ በመጠነኛ ስፋት የተወሳ አሳብ ነው። አምና ከተንሸራሸሩት አሳቦች ሌላው፥ 'ኢየሱስ ከሞተ በኋላ እስከ ትንሣኤው የት ነበር?' የሚለው ነው።

‘በየትኛው ቀን ተሰቀለ?’ ለሚለው፥ ነጥቡ ኢየሱስ ዐርብ ተሰቅሎ እሁድ ማለዳ ከተነሣ እንዴት ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይሆናል? የሚል ነው። አንዳንድ ሙስሊሞችም ይህንን የሰማይ ስባሪ እመሬት ላይ እንደወደቀ አድርገው ያዳንቁታል። ከሙስሊሞች ጋር ስለዚህ ጉዳይ ስነጋገር፥ ‘ሲጀመር በትንሣኤው ታምናላችሁ ወይ?’ ብዬ እጠይቃቸዋለሁ። እንደማያምኑ የታወቀ ነው። እንደማያምኑ ከተናገሩ፥ ‘ስለ ቀኑ ሳይሆን ስለ ትንሣኤው እንነጋገር፤ ስለ ትንሣኤው ካላመናችሁ ስለምን ስለ ቀኑ እንከራከራለን?’ በማለት ወደ ዋናው ጉዳይ እሄዳለሁ። ለነገሩ የቁርኣኑ ዒሳ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ አይደለም። ሆኖም አያውቅም። ስለዚህ ጉዳይ ያዘጋጀሁት መጽሐፍ እዚህ ይገኛል፤ https://t.me/zelalemmengistu/462

ወደ ቀኑ ስንመጣ፥ በወንጌላት ውስጥ ቀኑ የትኛው መሆኑ አልተጻፈም። ጥያቄውን ከሁለት አንጻር መመልከት እንችላለን።

1. በአይሁድ አንድ ሙሉ ቀንም የቀን ሽራፊም እንደ ቀን ነው የሚቆጠረው። ዐርብ፥ ቅዳሜ፥ እሑድ ሙሉም ጎዶሎም ሆነውም እንደ ሦስት ቀን ይቆጠራሉ። ዕድሜያችንን ስንቆጥር ወር አንቆጥርም። ዓመቱ ሊያልቅ አንድ ወር ወይም አንድ ቀንም ቢቀረው ቀጣዩን ዕድሜ አንቆጥርም። ከዓመቱ አንድ ወር ወይም አንድ ቀን ብቻ ቢያልፍም ለአሮጌው ይቀርባል ብለን በአሮጌው አንቆጥርም። ይህም ልክ እንደዚያ ነው። ይህ አንደኛው አሳብ ነው።

2. ሁለተኛው፥ በወንጌላት ውስጥ ቀኑ የትኛው መሆኑ አልተጻፈም ብያለሁ። ጸሎተ ኀሙስ፥ ስቅለተ ዕርብ የምንለው ከትውፊት እንጂ ቀኑ ይህ ነው ተብሎ አልተጻፈልንም። የመዘጋጀት ቀን መሆኑ፥ ሉቃ. 23፥54፤ የሰንበት ዋዜማ መሆኑ፥ ማር. 15፥42 በዮሐ. 19፥31 የማዘጋጀት ቀን መሆኑ ተጽፎልናል። ዮሐንስ ስለዚያ ቀን ሲናገር ከዚያም የበለጠ ብሎአል፤ አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ሆነ ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት። ብሎአል። ἦν γὰρ μεγάλη ἡ ἡμέρα ἐκείνη τοῦ σαββάτου• ነበረና ትልቅ ቀን ያ ሰንበት።

የአይሁድ ፋሲካ በአዲሱ ዓመታቸው የመጀመሪያ ወር 14ኛ ቀን ነው የሚከበረው፤ ዘሌ. 23፥5፤ ዕዝ. 6፥19፤ ሕዝ. 45፥21።በተለያዩ ምክንያቶች በቀኑ ማክበር ያልቻለ እንዲያውም በሁለተኛ ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ያከብረዋል፤ ዘኁ. 9፥1-14፤ 2ዜና 30፥1-18። የአይሁድ ወር ጨረቃዊ ወር ነውና ይህ ቀን ሁሌም በአንድ ቀን ላይ አያርፍም። ፀሐያዊ ወርም እንኳ ቢሆን በአንድ ቀን አያርፍም። ስለዚህ የአይሁድ ፋሲካ የግድ በአንድ ቀን እንደሚያርፍ አድርገን መጠበቅ የለብንም። ፋሲካ የበዓል ቀን እንጂ የሰንበት ቀን አይደለም።

ሌላው፥ ትልቅ ሰንበት ወይም ታላቅ ሰንበት የተባለ ሰንበት በብሉይ ኪዳን አንድ ብቻ ሆኖ ተጠቅሶአል። የተለመደው የአይሁድ ሰንበት ቅዳሜ ስለሆነና ቀናቸው የሚጀምረው ከምሽት ጀምሮ ስለሆነ፥ ስቅለት ዐርብ እንደሆነ መውሰዱ አግባብ ነው። ሰንበት ማለት ትርጉሙ ማረፍ ነው። ሰባተኛው ቀን ስለሆነም ሰባት ማለትም ነው። ከሰባት ይልቅ ግን ትርጉሙ ማረፍ ወይም ከሥራ መታገድ ነው። አይሁድ ከሰባት ቀናት በአንዱ ማረፍን ያርፋሉ። በአይሁድ ከሰባቱ ቀናት ሌላ ሰንበት የተባለ ቀንም አለ። በሰባት ዓመት የሚከበር የዓመት ሰንበትም አለ። በዚህኛው ሰው ብቻ ሳይሆን ምድሪቱም ሰንበት አድርጋ ታርፋለች አትታረስም። በ50ኛው ዓመት የሚከበር የኢዮቤልዩ ዓመትም አለ። ስለ ተለየ የሰንበት ቀን በዘሌ. 16 እናገኛለን። ይህ ሰንበት የስርየት ቀን የተባለው ቀን ነው። ቀኑ በሰንበት (ወይም ሰባተኛ) ቀን ዐረፈም አላረፈም ሰንበት ይባላል። ከሳምንቱ በየትኛውም ቀን ቢያርፍ ሰንበት ይባላል። ይህኛው ቀን የሚውለው ሰባተኛው ወር እና አሥረኛው ቀን ነው፤ ዘሌ. 16፥29-31። ይህ ቀን በዓመት አንዴ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚገባበት ቀን ነው። ያ ቀን የተለየ ሕዝባዊ ወይም ብሔራዊ የስርየት ቀን ነው።

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ያ የስቅለት ዕለት ከዚያ ቀን ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ያስባሉ። ቀኑ שַׁבָּתוֹן שַׁבָּת ሻባት ሻባቶውን ተብሎአል፤ ሰንበተ ሰንበት ማለት ነው። በዘሌ. 16፥31 ታላቅ ሰንበት ይሆንላችኋል፥ ራሳችሁንም ታዋርዳላችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው። የተባለው ቀን ነው። ይህ ቀን ሁሌም ሰባተኛ ወር አሥረኛ ቀን ስለሆነ ሰኞ ወይም ረቡዕ፥ ወይም ቅዳሜም ሊውል ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ትልቅ ሰንበት የፋሲካ ሰንበት ሊሆን አይችልም። ፋሲካ በሰባተኛው ሳይሆን በአንደኛው ወር ነው የሚከበረውና።

እንግዲህ ኢየሱስ የተሰቀለው የፋሲካ ቀን፥ ልብ እንበል ፋሲካ የምንለው በጉ የሚታረድበት ቀን ነው፤ በተለምዶ ስቅለተ ዐርብ እንበል እንጂ ፋሲካ ዐርብ ነው መባል የነበረበት። ይህ ቀን ታዲያ የግድ ዐርብ ነው ማለት አይደለም። ረቡዕ ወይም ኀሙስም ሊሆን ይችላል። ከሆነ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ከዚህ አንጻርም ሲታይ ስሌቱ ትክክል ሊመጣ ይችላል።

. . . . .

ኢየሱስ ከሞተ በኋላ የት ነበር የቆየው?

ኢየሱስ ወደ ሲዖል ወረደ፤ በዚያም ተሰቃየ፤ አጋንንት ሲሳለቁበት፥ ሲጫወቱበት ቆይተው በዚያ ዳግም ተወልዶ በሦስተኛው ቀን ተነሣ ብለው ኑፋቄ የሚያስተምሩ አሉ። በአጋንንት መሰቃየቱና ዳግም መወለዱን እንተወው፤ የራሳቸው እኩይ ፈጠራ ስለሆነ። ወደ ሲዖል መውረዱን ከወዴት አገኛችሁት ብለን እንጠይቅና ከዚያ ለመልሳቸው ምላሽ መስጠት ይቻላል። በብሉይ ኪዳን ቋንቋ ሲዖል (שְׁאוֹל ሽዖውል) የኃጢአተኞች የስቃይ ፍጻሜ ስፍራ ከመሆን ጋር፥ መቃብር ከማለት ጋርም አንድ ነው። ለምሳሌ፥ ያዕቆብ፥ ሽምግልናዬን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ። ሲል (ዘፍ. 42፥38) ወደ ሲዖል ወረደ ማለት አይደለም፤ ሞቶ ተቀበረ እንጂ። ኢየሱስም ሞቶ ተቀበረ እንጂ ወደ ሲዖል ወረደ ተብሎ አልተጻፈም።

ይህንን ጥያቄ በሉቃ. 23፥43 ከተጻፈው መመለስ ይቻላል። ኢየሱስ አብረውት ተሰቅለው ከነበሩት አንዱ ለተናገረው ሲመልስ፥ ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው። ተብሎ ተጽፎአል። ኢየሱስ በገነት እንደሚሆን ከተናገረና እነዚህ በሲዖል ሦስት ቀን ቆየ ካሉ ማንን እንስማ? አሳቾቹን ከሰማን ሲዖል ማለት እና ገነት ማለት አንድ ናቸው ማለት ነው።

ዘላለም መንግስቱ
@nazrawi_tube