Get Mystery Box with random crypto!

ውዱ ነፍስ የትኛው ነው? “መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የ | ናዝራዊ Tube

ውዱ ነፍስ የትኛው ነው?

“መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ፥ ዘጠና ዘጠኙን በበረሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ከእናንተ ማን ነው?” ሉቃ 15፡4

“የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶልና።” ሉቃ 19፡10

ሰዉ ሁሉ ንጹሕ ሆኖ እኔ ግን ብቆሽሽ
ምድር ላይ እኔ ብቻ በኃጢአት ብበላሽ
መሞት የሚገባኝ እኔ ብቻ ብሆን
ኢየሱስ ለብቻዬ ይመጣልኝ ነበር፡፡
ዘማሪ በረከት ተስፋዬ

የሰውን ዋጋ ከልቡ ለጠየቀ ልከኛው ምላሽ በክርስቶስ የተከፈለው የደም መስዋእትነት ነው፡፡ የሰው ክቡርነት የሚመነጨውም ከዚሁ ነው፡፡ ሰውን ምን ክቡር ያደርገዋል ከተባለ ምላሹ የተከፈለለት ዋጋ ነዋ የሚል ነው፡፡

በመንፈሳዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን የሰውን ዋጋ የምንተምንበት የተለያየ መስፈሪያ እንዳለን ጥርጥር የለውም፡፡ የነፍስን ሁሉ ዋጋ አስተካክሎ ያለማየት ጉዳይ በቤተክርስቲያንም ሆነ በውጭ በጉልህ ይታያል፡፡ የሰውን ክቡርነት የሚያጎላልን መነጽር ሀብት፣ ዕውቀት፣ ዘር …የመሳሰሉት ይመስላሉ፡፡

በደጅ አካባቢ ለሕመማቸው ከንፈር የማይመጠጥላቸው፤ ለሞታቸው ደረት የማይደቃላቸው፣ መኖራቸው ከመኖር የማይደመርላቸው በርካቶች ናቸው፡፡ በቤተክርስቲያንም ልክ እንዲሁ እጃቸውን አንስተው ጌታን በተቀበሉበት ቅጽበት እልልታ የማይደቅምላቸው፤ መምጣታቸው እንደማይሞላን፣ መቅረታቸውም እንደማያጎድለን የሚታሰብባቸው፤ ሙሉ ፈገግታ የማይቸራቸው፣ መሪዎቻቸው የማያተኩሯቸው፣ የጌታ ቤት የተቀደሰ አሳሳም የሚናፍቃቸው፣ ደጃቸው ለጉብኝት የማይንኳኳባቸው ምእመናን ብዙ ናቸው፡፡

በእግዚአብሔር ቤት VIP እና VVIP ምእመናን የመኖራቸው ጉዳይ በእጅጉ ያስደንቃል፤ ያሳዝናልም፡፡ ያዕቆብ በመልእክቱ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የሰላ ሐሳቡን አስፍሯል፤

“ወንድሞቼ ሆይ፤ ክቡር በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ እንደ መሆናችሁ አድልዎ አታድርጉ። የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤአችሁ ቢመጣ እንዲሁም ያደፈ ልብስ የለበሰ ድኻ ሰው ቢገባ፣ ያማረ ልብስ ለለበሰው የተለየ አክብሮት በማሳየት፣ “ለአንተ የሚሆን መልካም ስፍራ ይኸውልህ” ብትሉትና ድኻውን ሰው ግን፣ “አንተ በዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች በወለሉ ላይ ተቀመጥ” ብትሉት፣ በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? ደግሞስ በክፉ ሐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን? የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወድዱም ተስፋ የተሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን?” አዲሱ መደበኛ ትርጉም ያዕቆብ 2÷1-6

አዎን ጌታ አምላክ የሰዎች ሁሉ ወዳጅ የምስኪኖችም ወዳጅ ነው፡፡ በእርሱ ዘንድ መታወቂያችን አንድ ነው፤ ሁላችን የእርሱ ምሕረት የሚገባን ኃጢአተኞች ነን፡፡ አምነን በዳንበት ቅጽበትም ወደ መንግሥቱ የፈለስን ውድ ልጆቹ፣ በአካሉ ውስጥ ብልቶች እና በእርሱ የቤተሰብ ተቋም ውስጥ የቤተሰቡ አባላት ነን፡፡ በፊቱ ርካሽ እና ቀላል ግምት የሚሰጠው አንዳችም የለም፡፡

በተለይም በቤተክርስቲያን “ቀላል ሰው እንዳይመስላችሁ” እያልን የምናንቆለጳጵሰው፤ አይረቤ እንደሆነ ቆጥረንም የምናዋድቀው ማንም ሊኖር አይገባም፡፡ ድቤ እየደለቅን እንኳን ደኅና መጣህ የምንለውም፤ ጥግህን ያዝ ብለን እንደነገሩ የምናስተናግደውም ሊኖር አይገባም፡፡ እገሌን ማረክን ብለን ግዳይ እንደጣለ አርበኛ የምንፎክርለት፣ እንደዘበት አይተንም የምናልፈው ሊኖር አይገባም፡፡

በመንግሥቱ ውስጥ ለተገኘ ዕድል ፈንታ ለሁሉ እኩል ዋጋ ተከፍሏል፡፡ በአገልግሎት እውነተኛ ተጋድሎ የምንተጋ ወገኖች ክርስቶስ የሞተለትን ሰው ሁሉ በእኩል ዓይን እንይ፣ በእኩል መጠንም እናገልግል፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ በዚህ መልኩ የሚደረግ ነገር ትልቅ ኃጢአት፣ ከእምነት መጉደል እና ሕግ ተላላፊነት እንደሆነ ያዕቆብ በመልእክቱ መስክሯል፡፡ ውዱ ነፍስም ያለ ልዩነት ክርስቶስ የሞተለት ሁሉ ነው፡፡

ጌታ ይርዳን!!
መጋቢ ስንታየሁ በቀለ
@nazrawi_tube