Get Mystery Box with random crypto!

#የእኔነት አባዜ፣ የግለኝነት ስካር! የዚህ ዘመን የቤተክርስቲያን አንዱ ምናልባትም ዋነኛው ተግዳ | ናዝራዊ Tube

#የእኔነት አባዜ፣ የግለኝነት ስካር!

የዚህ ዘመን የቤተክርስቲያን አንዱ ምናልባትም ዋነኛው ተግዳሮት እኔነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዞ ማገልገል፣ ተከባብሮ መንግሥቱን ማስፋት፣ አንተ ትብስ የሚል መንፈስ ጨርሶ እየጠፋ ይመስላል፡፡ ባመዛኙ በቤተክረስቲያን መካከል ያለ ክፍፍልም ምንጩ ይኸው ነው፡፡ እኔነት አዙሪቱ ከባድ ነው፡፡ እኔነት ራስን የማንገሥ ሩጫ ነው፡፡ እኔነት ዙሩ ሲከርር “ከእኔ በቀር!” ያሰኛል፤ ይህ ደግሞ አንጋጦ ከመትፋት አይተናነስም፡፡ “ከእኔ በቀር” ሊል የተገባው አንዱ አንድዬ ብቻ ነውና፡፡

ለእኛ “እኔነት” ከፍጥረታችንም ጋር እንኳ አይገጥምም፡፡ ስሪታችን በእኔነት ክንፍ ለብቻ ለመክነፍ የሚያበቃ አይደለም፡፡ አንዳችን ያለሌላችን ምንም ነን፡፡ የቤተክርስቲያን ክብር ደግሞ በአብሮነት ውስጥ የሚገለጥ ልምላሜ ነው፡፡ ማንም ብንሆን ለብቻችን ምንም ነን፡፡ ለዚህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ምንነታችንን በአካል መስሎ የሚያስተምረን፡፡ ከአካል ክፍሎች አንዱ የጎደለ እንደሁ፣ በሙሉነት መድመቅ አይቻልም፡፡ ያው “ጎዶሎ” የሚል ተቀጥላ ያስከትላል፡፡

ብቻ የመድመቅ አባዜ የሉሲፈር መንገድ ነው፡፡ የገነነ እኔነት ውስጥ ትእቢት አሸምቆ አለ፡፡ ዶ/ር ኃይሉ ቸርነት በአንድ ወቅት “ትእቢት በእኔነት ጢም ብሎ መሞላት ነው” ሲል ሰምቼዋለሁ፡፡ እውነት ነው፤ የገነነ እኔነት መጨረሻን ያከፋል፡፡ አብሮት በሚያገለግለው ወንድም ምክንያት በቂ ከበሬታ ያጣ የመሰለው ወንድም፣ “ሁለት ፀሐይ በአንድ ሰማይ ላይ አይደምቅም” በሚል አመክንዮ ከወንድሙ ተለይቶ ብቻውን የሚደምቅበትን የገዛ ቸርቹን ከፍቷል፡፡ (በነገራችን ላይ የአገልግሎት ጥሪ ግብ ራስን ማድመቅ ሳይሆን፣ ራስን መደበቅ ነው፡፡) እዩኝ እዩኝ ማለት የልከኛ መንፈሳዊነት መገለጫ አይደለም፡፡ የአገልግሎቱ እና የጸጋው አሠራር ግብ እርሱን እዩልኝ የማለት ነው፡፡

የዚህ ዘመን የአገልግሎት ዝንባሌ ግን ባመዛኙ ሐዲዱን የሳተ ይመስላል፡፡ የአዲስ ኪዳን ጸሐፍት አብሮነትን በእጅጉ ያበረታታሉ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በአብዛኞቹ መልእክቶቹ ውስጥ እኔ በማለት ፈንታ “እኔና…” ሲል እናነባለን፡፡ ሰላምታ እንኳ ሲያቀርብ “እኔና አብረውኝ…” ይላል፤ ምን ጸጋ የበዛለት ቢሆን፣ ብቻውን እንዳልቆመ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡

አሁን የእኔነት አባዜ በእጅጉ ገንኖ ይታያል፡፡ እኔነት በአልባሌ ጭብጨባ ይፋፋል፤ ያልተካደ እኔነት የመስቀሉ ጠላት አድርጎ ያቆማል፡፡ የደረስንበት ጥግ እኔነትን የሁሉ መፍትሔ እና መላ አድርጎ እስከማቅረብ የተለጠጠ ነው፡፡ “እኔ እንደሌላው አይነት አይደለሁም” እስከማለት ደፍረናል፡፡

በየግል ቤተክርስቲያኖቻችን እንደነገሥን ለማሳየት በየደጆቻችንን ደማቅ ፎቶዎቻችንን በየአቅጣጫው ሰቅለናል፡፡ በየመርሐግብሮቻችን “ዋነኛው እኔ ነኝ!” ለማለት፣ ከጋበዝናቸው ሰዎች አናት ላይ ደማቅ ፎቶዎቻችንን እናኖራለን፡፡ በአዳራሹ መካከል የተለየ የከበሬታ ወንበር አሰናድተን በእርሱ ላይ እንሰየማለን፤ በሌለን ጊዜ እንኳ ሌላ አይቀመጥበትም፡፡ ክርስቶስ ራስ በሆነለት አካል ውስጥ፣ ከአካሉ ብልቶች መካከል እንደ አንዱ በመሆን ፈንታ፣ ከ“ራሱ” በላይ ጠቃሚ መሆናችንን ለፍፈን በሕዝቡ ላይ ሰልጠነናል፡፡ የመለኮት ሙላት ሁሉ ተጠቅልሎ እጃችን እንደገባ አምነን በእኔነታችን ሰክረናል፡፡ ክርስቶስ በእኛነታችን እንዳይገለጥ እኔነት ትልቁ መጋራጃ ነው፤ ቢያምም የእኔነትን መጋረጃ ገፍፎ መጣል የተገባ ነገር ነው፡፡

ይኸው ሩጫችን ደግሞ መጨረሻ ያለው አይመስልም፡ በየዕለቱም በእኔነት የፋፉ ሰዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው፡፡ በዘመን እላቂ እንደመኖራችን ብዙ ተስፋ ማድረግ ላይኖርብን ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ልኩ ይኸው መስሏቸው በቅንነት እና ባለማወቅ በዚህ መንገድ የተጠመዱትን ማዳን ይቻል እንደሆን እውነትን እንናገራለን፡፡ ከገነነ እኔነት መዳን ከብዙ ነገር መዳን ነው፡፡ የእኔነት ስካር ወስዶ ወስዶ የት እንደሚደፋ አይታወቅም፡፡ ከእኔነት መዳን ሌለውን በልኩ ለማየት እና ንጉሡን በእውነት ለማላቅ ዕድል ይሰጣል፡፡

ሕዝብ ሁሉ ግርርርር ብሎ ይከተለው የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ በጮክታ “እኔ አይደለሁም!” ብሎ ወደ መሲሁ እጁን ጠቁሟል፡፡ ይህ አይነተኛው ማምለጫ ነው፡፡

“እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል።” ዮሐ 3፡30

መጋቢ ስንታየሁ በቀለ
@nazrawi_tube