Get Mystery Box with random crypto!

ፍየል የሚመራቸው በጎች አንዳንዶቻችሁ ምናልባት እንደምታውቁት ተወልጄ ያደግኩበት አካባቢ (ወላይታ | ናዝራዊ Tube

ፍየል የሚመራቸው በጎች

አንዳንዶቻችሁ ምናልባት እንደምታውቁት ተወልጄ ያደግኩበት አካባቢ (ወላይታ) በSIM ሚስዮናዊያን አማካይነት ወንጌል በቀዳሚነት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው። አስታውሳለሁ ልጅ እያለሁ አማኞች በእኛ አካባቢ ውሻና ፍየል አያረቡም ነበር። ውሻ በሐሰተኛ መምህራን የተመሰለው ችግር ቢኖርበት አይደል? ብለው ነው። (ከውሾች ተጠበቁ ይላል) "እርኩስ ነው" ተብሎ ይታመናል። ፍየል የማያረቡበት ምክንያት ደግሞ በስተመጨረሻ በግራ በኩል ይሆናሉ የሚለውን አንብበው ነው። ከዚያም ባሻገር ፍየል በባሕርዩ ቀበጥ፣ ስግብግብ፣ ሴሰኛ፣ ነገር ነው ተብሎ አይወደድም።

በግ እንደሚታወቀው የዋህ፣ በእረኛው የሚታመን፣ የእረኛውን ድምጽ የሚሰማ፣ የሚከተል፣ የተረጋጋ ፍጥረት ነው። መዝ 23 የእረኛውን መግቦት ብቻ ሳይሆን የበጎቹንም እርጋታ (መርካት መቻል) የምናይበት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። ክርስቲያኖች በበጎች ተመስለዋል ክርስቶስ የበጎች እረኛ መሆኑን ተናግሮአል። በግ በፍጥረቱም ገመናውን ሸፍኖ እርቃኑን ሳይገላልጥ የሚኖር ቡሩክ እንስሳ ነው።

ስለ ፍየል በደንብ አላጠናሁም ግን በጎችን መምራት የሚያስችል የሞራል ብቃት የለውም። አስተውላችሁ ከሆነ ፍየል "እረኛዬ ነው" ብሎ የራሱን ባለቤት በእርጋታ አይከተልም። ይልቅስ ቅጠል ወዳገኘበት በጥሶ ሊጎርስ ሯጭ ነው። ለሆድ አዳሪ ነው። የፍየል እረኛ መሆን አድካሚ ይመስለኛል። ፍየል ባለበት ሠላም ጸጥታና መረጋጋት አታገኙም። ፍየል ከስግብግብነቱ ከቀበጥነቱና ከሰሰኝነቱ አንጻር በጎችን የመምራት ዕድል ሊያገኝ አይገባውም። በተቀላጠፈ ነው እንዴ?

ለምንድ ነው ይህን ምሳሌ ያነሳሁት?? የሐስት መምህራን ስግብግብና ነገሮችን ከራሳቸው ግል ጥቅም አኳያ ብቻ የሚያዩ ከመሆናቸው አንጻር የበጎች መሪ መሆን የለባቸውም ብዬ ነው። በምንም መስፈርት ፍየል በግን መምራት አይኖርበትም። ሊመሩ የሚችሉት ወዴት እንደሆነ ስለሚታወቅ። እነዚህ ሐሰተኞች ሐዋሪያትና ተንባዮች የሚታይባቸውን ሌሎች ባሕርያት ሁሉ ትተን ስግብግብ ሆዳምነታቸውን ከተመለከትን በትክክል የፍየል ባሕርይ እንጂ በግነት ሲያልፍም አልነካካቸውም ማለት ትችላላችሁ። ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ከብልይና ከሐዲስ እንድታጠኑ ሰጥቻችሁ ልሰናበታችሁ።

1. "ካሕናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፣ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያሟርታሉ፤ ከዚህም ጋር እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን? ክፉ ነገር ምንም አይመጣብንም እያሉ በእግዚአብሔር ይታመናሉ።" (ሚክ. 3:11) ይላል። ገንዘብ መገኘቱን ብቻ እንጂ ስለሚናገሩት መልዕክት እውነተኝነት ግዴላቸውም ፍየሎቹ እረኞች። "ሠላም ነው"፣ "ድግስ ነው"፣ "ቁርጥ ነው"። ይላሉ የሚሆነው ግን ተቃራኒው ነው። ፍየሎቹ እረኞች "ደቡብ በእናንተ ምክንያት ሰላም ነች" በተባለ ማግስት ምን እንደተከሰተ ታስታውሳላችሁ። የሐሰተኞች ሠራተኞች ስግብግብነትና ሆዳምነት ከየትም የሚያመጡት ሳይሆን ከባሕርያቸው ያፈለቁት ካላመነ ልባቸው የሚያመነጩት ነው።

2. "የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።" (2ቆሮ. 2:17) ሐዋሪያው ጳውሎስ እነዚያ ስግብግቦቹ ሌላው ቀርቶ ቃሉንም ቀላቅለው ይሸቃቅጣሉ።ይላል። ቅንነት የሌለባቸው ለሆድ አዳሪዎች መሆናቸውን ጠቁሞአል። እርሱ ግን እንደ መልዕክተኛ በቅንነት በክርስቶስ ሆኖ የሚናገር መሆኑን በንጽጽር ተናግሮአል። ልዩነቱ ጉልህ ነው። ሐሰተኞች አለመርካት፣ ጥቅመኝነት መለያቸው ነው። ተልዕኳቸው ራስ ተኮር ነው። ዓላማቸው ራስ ተኮር ነው። ግባቸው ራስ ተኮር ነው። መነሻቸውም መድረሻቸውም ራስ ተኮር ነው። የዛሬው መልዕክቴ በጎች ሆይ ምንም የዋህ ብት ሆኑ በፍየል አትመሩ!!መልካም ቀን!! ቻው።

ወርቅነህ ኮይራ
@nazrawi_tube