Get Mystery Box with random crypto!

የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች ነን? እንዴት? የእግዚአብሔር ልጆችስ ነን? እንዴት? ክፍል ሦስት ሦ | ናዝራዊ Tube

የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች ነን? እንዴት? የእግዚአብሔር ልጆችስ ነን? እንዴት?

ክፍል ሦስት

ሦስተኛው ልጆች የመሆናችን ገላጭ ቃል ልጆች የመደረጋችን እውነት ነው። ቃሉን ከወደድን ማደጎ እንበለው፤ ከፈለግን ጉዲፈቻ እንበለው፤ ከፈለግን የእንግሊዝኛውን ወስደን adoption እንበለው፤ ቃሉ ቢጥመንም ባይጥመንም አሳቡ ግን ያ ነው። ይህንን ቃል በአዲስ ኪዳን በጳውሎስ ተደጋግሞ ተጽፎ እናገኘዋለን። ይህ የግሪክ ቃል υἱοθεσία ሁዮቴሲያ የተባለው ነው። ትርጉሙ ልጅ መደረግ፥ እንደ ልጅ መደረግ፥ ልጅ ተደርጎ መወሰድ ማለት ነው።

በአዲስ ኪዳን ቃሉ በተጻፈባቸው ቦታዎች ሁሉ በጳውሎስ ነው የተጠቀሰው። ይህ ጳውሎስ ልጆች መሆናችንን አበክሮ የጻፈ ሐዋርያም ነው። እና ልጆች መሆናችንን ሲናገር ይህን ቃል መጠቀሙ በመንፈስ ቅዱስ በመመራት እንጂ ባለማወቅ ወይ በመሰለኝ አይደለም። ልጅ መሆንና ልጅ መደረግ የሚጋጩ ሁለት ነገሮች አይደሉም። ሁለት የልጅነት እርከኖች ወይም ደረጃዎችም አይደሉም። ሁለቱም አንድ ልጅነት ናቸው።

ባለፈው ክፍል መጨረሻ የተመለከትነው ዳግም ልደት የልጅነታችንን ገላጭ የሆነ ሌላ ቃል መሆኑን አይተን ነበር የጨረስነው። ዳግም ልደት በሥጋ ከወላጆቻችን እንደተወለድነው፥ በዮሐ. 3 ጌታ ለኒቆዲሞስ እንዳብራራው፥ በመንፈስ ወይም በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት መንፈሳዊው ማንነታችን የእግዚአብሔር ልጅ ሲሆን ነው። ይህ ማለት ቀድሞ በአካላዊ ሕይወት ኖረንም ልጆች አልነበርንም ማለት ነው። በቲቶ 3፥5 እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ይላል። እዚህ አዲስ ልደት (παλιγγενεσία) እንደገና መወለድ ነው። ቃሉ እዚህና ማቴ 19፥28 ብቻ የሚገኝ አዲስነትን ገላጭ ነው። ዳግም ስንወለድ አንዲስ ፍጥረት ነው የምንሆነው፤ ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። 2ቆሮ. 5፥17። ዳግም ልደት እና ልጅ መደረግ ያው አንዱ ነገር ነው በተለያዩ መግለጫ ቃላት የተገለጠው እንጂ ሁለት እርከኖች ወይም ደረጃዎች አለመሆናቸውን ደግመን እናስብ።

ልጅ መደረግ ለሚለው ቃል ጳውሎስ የጻፋቸው ጥቅሶች እነዚህ ናቸው፤

አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። ሮሜ 8፥15።

እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። ሮሜ. 8፥23።

እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤ ሮሜ. 9፥4።

ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ፥ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ። ገላ. 4፥4-5።

በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። ኤፌ. 1፥5።

እኛ የእግዚአብሔር ልጆች ነን። የሆንነው ደግሞ በመደረግ ነው። ተደርገን ነው። ማለትም፥ እግዚአብሔር ወድዶ ልጆቹ አድርጎን ነው። በፍጥረታችን ወይም በአፈጣጠራችን ልጆች አልነበርንም። እግዚአብሔር ግን ልጆቹ እንድንሆን ወደደና ልጆቹ አደረገን፤ እንደ ልጆቹ አድርጎ ተቀበለን። ልጅነት የተፈጥሮ መብታችን አይደለም። ከተደረግን በኋላ ግን፥ ይህ ልጅነት ከተሰጠን በኋላ ግን፥ ልጅነት መብት ብቻ ሳይሆን ሥልጣንም ሆነ። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሐ. 1፥12። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ስናስብና ስንደሰትበት፥ ልጆች የተደረግን መሆናችንንም አንዘንጋ። ልጆች የተደረግን ልጆች ነን።

በነገረ መለኮት፥ በተለይም በነገረ ክርስቶስ እና በነገረ ሰብዕ፥ የባሕርይ ልጅ እና የጸጋ ልጅ ሲባል ሰምተን እናውቅ ይሆናል። (የባሕርይ ተካፋይ ስለሚለው አሳብ ለብቻ እመለሳለሁ።) የባሕርይ ልጅ ሲባል ከአድራጊው ጋር አንድ መሆንን አመልካች ነው። ይህ ለኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅነት የምንጠቀምበት የስነ መለኮት ቃል ወይም ሐረግ ነው። (እዚህ ላይ፥ የጳውሎስ ፈቃዱን የእግዚአብሔር ልጅ መጽሐፍ በጠቅላላው፥ በተለይ የኛን ልጅነት በተመለከተ ደግሞ በምዕራፍ 8 እና 9ን ተንትኖታልና፥ ይህንን እንድታነብቡ፥ እንድታነብቡ ብቻ ሳይሆን እንድታጠኑ፥ አደራ እላለሁ።) ባሕርይ የሚለውን ቃል ተፈጥሮ እንዳንለው ኢየሱስ ፍጡር አይደለምና የተፈጥሮ ልጅ አይባልም። (ሆኖም፥ አዲስ ኪዳን ይህንን ቃል በአንዳንድ ጥቅሶች ውስጥ ተፈጥሮም ይለዋል።) ሥሪት እንዳይባልም እርሱ ሠሪ እንጂ ተሠሪ አይደለምና ይህም አያስኬድም።

የባሕርይ ልጅ መሰኘቱ ወልድ እና አብ አንድ ባሕርይ ወይም በእንግሊዝኛ essence በግሪክ οὐσία ወይም ούσιος የተባለውን መሆናቸውን ነው። የኒቅያው ጉባኤ አብ እና ወልድ አንድ ባሕርይ ὁμοούσιος ሆሞኡሲዮስ ወይም ὁμοούσιον ሆኖኡሲዮን ያለው ያንን ነው። አብ የሆነውን ሁሉ ወልድም ነው፤ ኹነታችው በሁሉ አንድ ነው። በዚህ ረገድ እግዚአብሔርን የሚመስል እግዚአብሔር ብቻ ነው። አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ በባሕርይ አንድ ናቸው። እግዚአብሔርን በዚህ ማንነቱ ከፍጥረት ወይም ከፍጡር የሚመስለው ምንም፥ ማንም የለም። ሰውን በመልኩና በምሳሌው መፍጠሩም ሰውን የመለኮት ባሕርይ አያላብሰውም ወይም አያቀዳጀውም። ሰው ሲፈጠር ሰው እንጂ፥ የተሰጠው ሥልጣን አለው እንጂ አምላክነት የለውም። መንፈሳዊነት አለው እንጂ መንፈስ አይደለም።

እግዚአብሔር መንፈስ ነውና መልክና አምሳል ሲባል እንደ አካል መልክ አድርገን መውሰድ የለብንም። ይህ መልክና ምሳሌ ምንም አካላዊነት የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን በሰውኛ አኳኋን ቢገልጠውም የሰው ዓይነት አይደለም። ስንዝር፥ ዓይኖች፥ ክንድ፥ ጀርባ፥ መሳቅ፥ መጸጸት፥ ወዘተ፥ በመሰሉ ቃላት ቢገልጠውም፥ ይህ ለሰው መረዳት ቃሉ የተጠቀመበት አገላለጥ ነው፤ anthropomorphism ይባላል፤ ስብዕናን ማላበስ ይባላል። ይህ ለእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ለግዑዛን ነገሮችም ይደረጋል። ወንዞች ሲያጨበጭቡ፥ ተራሮች ሲዘልሉ፥ ፀሐይ እንደ አርበኛ ሲወይም ሮጥ ወዘተ፥ የዚህ ዘር ነው።

እኛ በባሕርይ፥ በፍጥረት፥ ወይም በሥሪት የምንመሳሰለው ከአዳም ጋር ነው፤ በቀጥታ ልጁ የምንሆነውም የአዳምን ነው። ከአዳም ጋር ፍጹም አንድ ነን። በኃጢአት ከመውደቃቸው በፊት ከነበራቸው ንጽሕና በቀር አንድ ነን። አዳም ሲፈጠር ሰው እንጂ አምላክ አልነበረም። ሰው እንጂ መንፈስም አልነበረም። ፍጡር እንጂ ልጅም አልነበረም። እኛም ቀድሞ ልጆች አልነበርንም። በሆነ ጊዜ ግን ሆነን ተገኘን። በራሳችን አልሆንንም፤ ግን ተደረግን። ከላይ እንዳልኩት፥ ቃሉን ማደጎ እንበለው፥ ጉዲፈቻ፤ ወይም የእንግሊዝኛውን adoption እንውሰድ ወይም በሌላ በምናውቃቸው ቋንቋዎች እንጥራው ነጥቡ ልጆች ያልነበርን እኛ ልጆች #መደረጋችን፥ እንደ ልጆች መሆናችን፥ ልጆች መሆናችን ነው።