Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል ሁለት፤ በክፍል አንድ ያልሆንነውን ተመልክተናል። ቀጥሎ የሆንነውን እንመልከት። . . . | ናዝራዊ Tube

ክፍል ሁለት፤

በክፍል አንድ ያልሆንነውን ተመልክተናል። ቀጥሎ የሆንነውን እንመልከት። . . .

1ኛ፥ ልጆች ነን። ልጅ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፊ ትርጉም ያለው ቃል ነው። የሥጋ ልጅ ልጅ ነው፤ ልጅ ናት። በቀጥታ ከወላጅ የተወለደም፥ በቀጥታ ሳይሆን የልጅ ልጅ የሆነም፥ ዘር የሆነም ልጅ እየተባለ ተጠርቶአል። ሁለቱ የዮሴፍ ልጆች፥ ለምሳሌ፥ የያዕቆብ ልጆች ተብለው ከ12ቱ ነገድ ጋርም ተቆጥረዋል። በሥጋ ያልተወለዱም ልጆች ተብለዋል፤ ያም ባሕርይን ገላጭ አሳብ ነው፤ የሚያስተራርቁ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለዋል፤ የእፉኝት ልጆች፥ የቁጣ ልጆች፥ የዲያብሎስ ልጆች ሲል በሥጋ መወለድን መናገሩ አይደለም። ምስስልን መናገሩ ነው። ምሳሌያዊና ባሕርያዊ ልጅነቶችም አሉ፤ ለምሳሌ፥ የነጎድጓድ ልጆች፥ እና የመሰሉትን አላወሳሁም።

ልጅነት የግንኙነት ገላጭ ነው። በቀጥታ ብንወለድም ግንኙነት አለ፤ ልደቱ ወይም ልጅነቱ አካላዊ ባይሆንም ወይም ካልሆነም ግንኙነቱ ግን አለ። እስራኤል የእግዚአብሔር ልጅ ወይም በኵር ልጅ ሲባሉ የግንኙነት ጉዳይ የተሰመረበት ነው። ከአብርሃም ጋር የተገባ ኪዳንና ግንኙነት አለና፥ በጠቅላላው እንደ ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት ማዕከላዊው ቦታ ላይ የሚገኝ ነው።

እኛ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆናችን እውነት በግልጽ የተጻፈ ቃል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እኛ በጌታ የሆንን ቅዱሳን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ምንም ሳይንተባተብ ይነግረናል። የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ይህን ግልጽ ነው። ልጆች ነን።

ግን እንዴት ልጆች ሆንን? ይህ ትልቅ ጥያቄ ነው። የልጅነታችን ሂደትስ እንዴት ነው የተከናወነው? ልጆች የሆንንበት መንገድ ደግሞ አለ፤ ልጆች የሆንንበትን መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ በገላጭ ቃላት ይገልጠዋል።

ሀ፥ ስጦታ፤ ልጅነት ስጦታ ነው። ልጅነት ስጦታችን ነው። ስጦታ ይለዋል። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ ዮሐ. 1፥12። ክርስቶስን ስንቀበለው የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን። ሰጣቸው ሲል የተሰጠ ሥልጣን መሆኑ ይታያል። የተሰጠን፥ የተቀበልነው ሥልጣን ነው። ቀድሞ እኛ ልጆች አልነበርንም፤ ሥልጣኑም አልነበረንም። ኋላ ግን ተሰጠንና ኖረን፤ እኛም ልጆች ሆንን።

ይህ ስጦታ የተሰጠን በእምነት በኩል፥ ክርስቶስን በመቀበል ነው፤ በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ገላ. 3፥26። ስጦታ ከሆነ የተሰጠን ነን ማለት ነው። የተቀበልን ከሆንን የሰጠን አለ ማለት ነው። የተሰጠን ሆነን እንዳልተሰጠንና እንደተቀዳጀነው ሆነን የምንኮፈስበት ምንም ምክንያት ሊኖረን አንችልምም፥ የተገባም አይደለም። አስቀድመን የእግዚአብሔር ልጆች ያልነበርን የቁጣ ልጆች ነበርን፤ በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ኤፌ. 2፥3።

ልጅነት እውነት ነው፤ ልጅነታችን እርግጥ ነው። እርሱም በፍቅር የተሰጠንና በትሕትና የተቀበልነው ስጦታ ነው። የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ፥ እንዲሁም ነን። ስለዚህ ምክንያት ዓለም እርሱን ስላላወቀው እኛን አያውቀንም። ወዳጆች ሆይ፥ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፥ ምንም እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ቢገለጥ እርሱ እንዳለ እናየዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን። 1ዮሐ. 3፥1-2። ልጅነታችን በፍቅር የተሰጠንና የተቀበልነው ስጦታ ነው። ስጦታ ሽልማት አይደለም። ሽልማት በሆነ ነገር በልጠን፥ ልቀን የምናገኘው የኛ ሥራ ያለበት የሌሎችን አድናቆት የምናገኝበት የሥራ ፍሬ ነው። ይህ የኛ ልጅነት ድንቅና ግሩምም ነው። ግንኙነት ነው፤ ሥልጣን አለበት፤ ወራሽነትም ነው። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ስጦታና ስጦታ ብቻ ነው። ስጦታ ከሆነ ሰጪ አለ፤ ተቀባይ አለ። እኛ ተቀባዮች ብቻ ነን።

ሁለተኛ፥ ዳግም ልደት፤ ልጅነታችንን ገላጭ የሆነው ሌላ ቃል ዳግም ልደት ወይም መንፈሳዊ ልደት ነው። ይህ ማለት መንፈሳችን ለብቻው ዳግም ተወልዶ ነፍሳችንና ሥጋችን ደግሞ በዝግመትና በትንሣኤ ዳግም ይወለዳሉ ማለት አይደለም። እኛ ኋላ የምንገጣጠም ቁርጥራጮች አይደለንም። መጽሐፍ ቅዱስ ሁለንተናችንን ሰው ብሎ ይጠራዋል። ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። . . . ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። ዮሐ. 3፥3 እና 7። ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር ነው ያለው። ዳግም መወለድን ከመንፈስ መወለድም ይለዋል፤ ቁጥር 5።

ዳግመኛ መወለድን ከማይጠፋ ዘር በእግዚአብሔር ቃል መሆኑንም ይነግረናል፤ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ። 1ጴጥ. 1፥23። እዚህ ዘር የተባለው ቃሉ ራሱ ነው። ይህ ዘር ቃሉ መሆኑን የምናገኘው ከቀጣዮቹ ሁለት ጥቅሶች (ከቁ. 24-25) ነው። ይህ ዳግመኛ መወለድ እንደገና መወለድ ነው። እዚሁ 1ጴጥ. 1፥3-4 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይላል። በሥጋ ስንወለድ የወላጆቻችን ልጆች እንደምንሆን እንደገና ወይም ዳግመኛ ስንወለድ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን።

ይህ ልደት የመንፈስ ልደት ወይም መንፈሳዊ ልጅነት ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን መንፈስ መሆን አይደለም። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት መወለድና የእግዚአብሔር ልጆች መሆን ነው። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። ሮሜ. 8፥15። እዚህ ጥቅስ ውስጥም፥ ልጅነትን ወይም የልጅነት መንፈስን መቀበላችንን ይነግረናል። መቀበል ከኖረ ሰጪ አለ። መቀበል ከኖረ፥ ከመቀበል በፊት ያ ነገር በእኛ ዘንድ ያልነበረ ነገርና ኋላ የኖረ ነገር ነው።

ሦስተኛው ልጆች መደረጋችን ነው።

ይቀጥላል።

ዘላለም መንግሥቱ
@nazrawi_tube