Get Mystery Box with random crypto!

➧ *የማስወረድ ፍርድ* አንቺ ሙስሊም እህቴ ሆይ! አሏህ በማህፀንሽ ውስጥ በፈጠረው ፅንስ በሸሪ | Muslim Students

➧ *የማስወረድ ፍርድ*

አንቺ ሙስሊም እህቴ ሆይ! አሏህ በማህፀንሽ ውስጥ በፈጠረው ፅንስ በሸሪዓው እምነት ጥሎብሻል፤ እንዳትደብቂው። አሏህ እንዲህ ይላል፦

﴿ وَلَا يَحِلُّ لَهُنَّ أَن يَكْتُمْنَ مَا خَلَقَ اللَّهُ فِي أَرْحَامِهِنَّ إِن كُنَّ يُؤْمِنَّ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ ۚ ﴾ [ سورة البقرة: 228]

~“በአሏህና በመጨረሻውም ቀን የሚያምኑ ቢኾኑ አላህ በማሕፀኖቻቸው ውስጥ የፈጠረውን ሊደብቁ ለነርሱ አይፈቀድላቸውም።” (አል-በቀራህ፡ 228)

~በየትኛውም መንገድ እሱን ለማውረድ እና ከሱ ለመላቀቅ ዘዴን አትፈልጊ።
ከጎደሎ ሁሉ የጠራው አሏህ እርጉዝ በሆንሽበት ስዓት እንኳን የረመዷን ፆም በአንቺ ወይም በፅንስሽ ላይ ችግር የሚያስከትል ከሆነ ማፍጠርን አግርቶልሻል።

~በዚህ ዘመን ተሰራጭቶ ያለው የውርጃ ስራ ሐራም የሆነ ተግባር ነው። የተረገዘው እሩህ ተነፍቶበት ከሆነ እና የሞተው በውርጃው ምክንያት ከሆነ ይህ ተግባር አሏህ ያለ ሀቅ እንዳትገደል ከጠበቃት ነፍስን እንደማጥፋት ይቆጠራል። እናም በወንጀል መጠየቅን እና እንደየ መጠኑ በዝርዝር ጉማ (የደም ካሳ) ማስከፈልን ያስከትላል።

~በማካካሻም(ከፋራህ) በኩል አንዳንድ ዑለሞች ሙእሚን የሆነችን ባሪያ ነፃ ማውጣት ሲሆን ይህን ካላገኘ ሁለት ወር በተከታታይ መፆም ነው ይላሉ። አንዳንድ ዑለሞች ይህቺን ተግባር ትንሿ ከእነ ህይዎት መቅበር ይሏታል።

~ሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ኢብራሂም መጅሙዑል-ፈታዋ ኪታባቸው 11ኛው ጥራዝ ገፅ 151 ላይ እንዲህ ይላሉ፦

~ “ፅንሱ በማህፀን ውስጥ መሞቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ፅንሱ ለማስወረድ እንቅስቃሴ ማድረግ አይፈቀድም፤ ማህፀን ውስጥ መሞቱ ከተረጋገጠ ማስወረዱ ይፈቀዳል።”
በ1407/6/20 ዓ.ሂ ላይ የታላላቅ ዑለማዎች ኮሚቴ የሚከተለውን የጋራ መግለጫ በ140ኛው ቁጥር ላይ አውጥቷል፦

❶) “በጣም ጠባብ በሆነ ገደብ እና በሸሪዓዊ ምክንያት እንጂ በየትኛውም የእድገት ደረጃ ላይ ያለን ፅንስ ማስወረድ አይቻልም።

❷) ፅንሱ በመጀመሪያው የእድገት ደረጃ ማለትም በመጀመሪያው 40 ቀን ከሆነ እና በማስወረዱ ሸሪዓዊ ጥቅም የሚኖረው ከሆነ ወይም ችግር ለማስወገድ ማስወረዱ ይቻላል። ነገር ግን በዚህ የእድገት ደረጃ ላይ እያለ ማውረድ ያስፈለገው ልጆዎችን ለማሳደግ ችግርን በመፍራት ወይም የኑሮ ወጫቸውን እና ማስተማሪያቸውን በመፍራት ወይም ለወደፊት ህይወታቸው ብሎ ወይም ሁለት ባል እና ሚስት ያላቸው ልጆች በቂ ስለሆኑ እና ልጅ ስለማያስፈልጋቸው ከሆነ ማስወረድ አይቻልም።

❸) ታማኝ የሆኑ የህክምና ኮሚቴዎች ፅንሱ መቀጠሉ በእናትዮዋ ጤንነት ላይ አደጋ ያመጣል ብለው እስካላረጋገጡ ድረስ ፅንሱ የረጋ ደም ወይም የተላመጠ ስጋ እድገት ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ማስወረድ አይፈቀድም። የፅንሱ መቀጠል ለእናትዮዋ መጥፋት ምክንያት ይሆናል ተብሎ ከተፈራ ፅንሱ ማስወረድ ይቻላል፤ ይህም የሚሆነው ሀኪሞቹ ፅንሱን ለማትረፍ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው ሲያቅታቸው ነው።

➍) እርግዝናው አራት ወር ከሞላው እና ከሶስተኛው የእድገት ደረጃ ከደረሰ በኋላ ሁሉም ታማኝ የሆኑ እስፔሻሊስቶች የፅንሱ ከማህፀን ውስጥ መቆየት ለእናቲቱ መሞት ምክንያት ይሆናል ብለው እስካላረጋገጡ ድረስ ፅንስን ማስወረድ አይቻልም። ይህም ማስወረድ የሚከናወነው የፅንሱን ህይወት ለማትረፍ ሁሉንም አማራጮች ከተጠቀሙ በኋላ ነው።

~ከላይ በተጠቀሱት መስፈርቶች መሰረት ማስወረድ የተፈቀደው ከሁለቱ ችግሮች ትልቁን ችግር ለማስወገድ እና ከሁለቱ ጥቅሞች ትልቁን ጥቅም ለማግኘት ሲባል ነው።

~ኮሚቴው ከላይ ያለፈውን መግለጫ ሲሰጥ አሏህን በመፍራት እና ነገሩን በማረጋገጥ ላይ አደራ ይላል። መልካሙን ገጣሚው አሏህ ነው፤ የአሏህ ሶላት እና ሰላም በነብዩና በባልደረቦቻቸው ላይ ይውረድ።” ንግግሩ አበቃ።

~በሸይኽ ሙሐመድ ኢብኑ ሷሊህ አልዑሰይሚን “ሪሳለቱ አዲማኢ አጥጦቢዒያህ ሊንኒሳእ” በተሰኘው ኪታባቸው ላይ ሲናገሩ፦

~“ እርጉዝ ሴቶች በሚያስወርዱበት ሰአት የተፈለገው ፅንሱን ማስወገድ እና “ሩህ” ከተነፋበት በኋላ ከሆነ ይህ ተግባር ያለጥርጥር ክልክል ነው። ምክንያቱም ይህ ያለ ሀቅ ነፍስን ማጥፋት ነው። የተከበረች ነፍስ ያለ አግባብ መግደል ደግሞ በቁርአን፣ በሐዲስ እና በኢጅማዕ ክልክል ነው።” (ከላይ በተጠቀሰው ኪታብ ገፅ 60 ላይ ይመልከቱ)

~ኢማም ኢብኑል ጀውዚ “አሕካሙ አንኒሳእ” በሚባል ኪታባቸው ገፅ108-109 ላይ እንዲህ ይላሉ፦

~ “የኒካህ ዋና አላማው ልጅን ማግኘት ነው፤ ሁሉም ውሃ(የዘር ፍሬ) ልጅ አይሆንም ይህ ከተሳካ በእውነት የተፈለገው ተገኘ፤ ሲታወቀው ለማስወረድ መሞከር የተፈለገበትን አላማ እና ጥበብ የሚፃረር ነው። ይህም በመጀመሪያው የእድገት ደረጃ “ሩህ” ከመነፋቱ በፊት ከሆነ ትልቅ ወንጀል ነው። ምክንያቱም በማደግ እና በመዳበር ላይ ያለ ስለሆነ ነው። ነገር ግን ሩህ ከተነፋበት አንፃር ሲታይ ወንጀሉ ዝቅ ያለ ነው።

~ አንዲት ሴት “ሩህ” በውስጡ ያለውን ፅንስ ለማስወረድ ሲታወቃት ብታደርገው ሙእሚን ሰው እንደመግደል ይቆጠራል። አሏህ እንዲህ ይላል፦

-{ وَإِذَا الْمَوْؤُدَةُ سُئِلَتْ (8) بِأَيِّ ذَنْبٍ قتلت (9) }. [التكوير الآيات 8-9]

“በሕይወቷ የተቀበረችውም ሴት ልጅ በተጠየቀች ጊዜ፤በምን ወንጀል እንደተገደለች።” (አተክዊር 8-9)

➤ሙስሊም እህቴ ሆይ!አሏህን ፍሪ! ይህን አስከፊ ወንጀል ለየትኛውም አላማ ብለሽ አትዳፈሪ። አጥማሚ የሆኑ መካሪዎችንም በመስማት አትሸንገይ።እምነት እና ህሊናን መሰረት ያላደረገች ብልሹ ባህልን አትከተይ።