Get Mystery Box with random crypto!

② ምክሮች ለ② ሰዎች ================== ①) በቢዝነስ ጉዳይ፦ አንተ ማሻ አላህ ጎበዝ | Murad Tadesse (Official Channel)☪️🇪🇹

② ምክሮች ለ② ሰዎች
==================
①) በቢዝነስ ጉዳይ፦
አንተ ማሻ አላህ ጎበዝ ተማሪ ነገር ነህ፣ ጥሩ ትሠራለህ። ዩኒቨርስቲ ገብረህ ድግሪህን ጨርሰሃል፣ ከዚያም ማስተርስና ፒኤችዲ እያልክ ሂደሃል፣ ወይም ስፔሻላይዝ ካደረግክ በኋላ ሰብ ስፔሻሊስት ሆነሃል። ግን ይህን ሁሉ አድርገህ ስትመለስ የምትቀጠረው ያኔ 10ኛ ክፍል ላይ ማትሪክ ወድቆ ውጤት ሳይመጣለት ሲቀር ሙያና ቴክኒክ ገብቶ ተምሮ ከተመረቀ በኋላ ባቋቋመው ተቋም ውስጥ ነው። ሰብ ስፔሻሊስት ሆነህ ወጥተህ ተቀጥረህ የምትሠራው ጭራሽ ሜዲስን እንኳ ሳይገባ ገና ከድፕሎማ ጀምሮ ተምሮ ራሱን አስተዳድጎ በከፈተው የGP ክሊኒክ ውስጥ ነው። ዕውቀትህ ከርሱ በላይ፤ ግን ገቢህ ከርሱ በታች! የግሌ ልክፈት ብትል እንኳ ሁሉም ቦታ ቦታውን ስለተያዘ መግቢያ ቀዳዳ የለም፤ በዛ ላይ ያለው የዋጋ ንረት በቀላሉ አስፈላጊውን ነገር አሟልቶ መጀመር አያስችልም። ያኔ ከመቀጠር ውጭ አማራጭ የለህም፤ በተለይ ደመወዟ አሪፍ ከሆነች ስለምታዘናጋህ በቅጥርህ ትሞታለህ። የተማርከው አካዳሚ ለአኺራህ ጥያቄ መልስ የሚሆን ሸሪዓዊ ነገር ሳይሆን ዱንያህን በአግባቡ ልትጠቀምበትና በርሱም አኺራህን ልትሻበት ነው። ስለዚህ የልፋትህን ማግኘት አለብህ።

መፍትሄ፦ ቢያንስ ድግሪህን እንደያዝክ በፊልድህ የሚሄድ ቢዝነስ ጀምር። የተወሰኑ አመታት እርሱን ቢዝነስ አጠናክረኸው በሁለት እግሩ ሲቆምና ከአንተ ትከሻ ሲወርድ ሌላ ባለሙያ ቀጥረህ አንተ ትምህርትህን ቀጥል፤ በጎድንም በፓርት ታይም ሥራ። ያኔ እየተማርከው ያለው ዕውቀት ተቋምህንም ያጠናክረዋል፤ ትምህርቱም ቢዝበሱም አልቀረም። ተመርቀህ ጸጉርህን መልጠህ ስትመጣ መግቢያ አታጣም፤ ቀድመህ የሰራኸው ቤት ስላለ። አንዳንዱ ሰው ከመማር ውጭ አዕምሮ ለቢዝነስ ክፍት አይደለም፤ ሪስክ ይፈራል፣ እና ይሄን መሰናክል ማሳለፍ ካላስቻለህ መማርህ ምኑጋ ነው? ለዱንያ የሚሆን እንጂ ለአኺራ የሚሆን ሒፍዝ የገባህ መሰለህ እንደ¿

*
②) በትዳር ጉዳይ፦
ገና ሃይስኩልና ካምፓስ ተማሪ እያለሽ የትዳር ጥያቄ ሲቀርብልሽ «ቆይ ትምህርቴን ልጨርስ!» እያልሽ ስትመልሺ ነበር። ወላጆችም ልጃችሁን ስትጠየቁ «ገንዘብ (ቤትና መኪና) የሌለው መናጢ ድሃ ነው!» ከሚለው ባሻገር እነዚህን ያሟላ ቢመጣ እንኳ «ቆይ! ተምራ ትጨርስ!» እያላችሁ ስንትና ስንት ሰዎችን ስትመልሱ ነበር።

ድግሪዋን ስትጨርስ 23ና 24 አመት አካባቢ ይሆናታል። ሥራ ፍለጋ ይባልና በትንሹ አንድ አመት ጫማዋ እስኪገረጣ ልትሯሯጥ ትችላለች። ሥራው ከተገኘ በኋላ አንድ ሦስት አመታት ያልፋል። እነዚያ ለትዳር የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር ባልተጠበቀ ሁኔታ እየቀነሱ ይመጣሉ። እንዲህ እንዲህ ይልና 30ዎቹ መግባት ይጀምራሉ። ያኔ ጭራሽ ጠያቂም ይጠፋል። ከማንም በላይ መከረኛዋ እናት በሯን ዘግታ ማልቀስ ትጀምራለች። ልጅም ወላጅም ያኔ ከእንቅልፋቸው መንቃት ይጀምራሉ፤ ግን ምን ዋጋ አለው! ብዙውን ነገር አሳልፈውታል። ያኔ ለሁለተኛም ሆነ ለሦስተኛ ብቻ በተገኘ ወደሚል ስሜት ይመጣል። አለፍ ሲልም የማይመጥን ወንድም ቢሆን ችግር የለም ወደሚል ተናዙል ይወረዳል። እነዚያ ከአንድ ገፅ በላይ የሚሆኑ የሚደረደሩ መስፈርቶች ወደ አንድ ሃረግ ይወርዳሉ። 40 ሲገባ አንድ ቃል ብቻ መሆናቸው አልቀረም።

ምን የመሰለ መልክና ቁንጅና፣ ምን የመሰለ ዲንና ጥንካሬ፣ ምን የመሰለ ውብ ቤተሰብና ዘር እያለ፤ ምን የመሰለችዋን ልጅ ጊዜዋን አሳለፉባት። አይበለውና ተስፋ መቁረጥ ከተደረሰ ወደ በቀላሉ ወደ ሐራም ግንኙነቶች፣ አላህ ይጠብቀንና ከካ'ፊ'ርም ጋር ቢሆን መጃጃል ይመጣል።

መፍትሄ፥ ገና ሃይስኩል እያለሽም ይሁን ግቢ ላይ እያለሽ ሸሪዓው ባዘዘው መልኩ የሚሆንሽ የትዳር አጋር ከተገኘ በጊዜ ተሰተሪ። በዚህ ወቅት አማርጠሽ የማግባት ሰፊ እድል አለሽ። ማግባት ትምህርትን አያስቋርጥም። ካገባሽ በኋላ ያስተምርሽ። ካላስተማረሽ ንገሪኝ! ወላጆችም ኋላ ከመጨነቅ በዚህ ወቅት ብዙም ሳታካብዱ በሐላሉ ሰትሯቸው። ኋላ ለናንተም ስቃይና ጭንቀት ነው።

በመጨረሻም፦ ምንም ይሁን ምን፤ ያለነው በጠፊዋ ዓለም በዱንያ ላይ ነውና ለሁሉም ነገር በሐላሉ ሰበብ ማድረስ፣ አላህን መፍራትና እርሱን መለመን፣ ጉዳይን ወደርሱ ማስጠጋትና በርን ዘግቶ ከርሱ ጋር ማንሾካሾክ መረሳት የለበትም። ያኔ አይሆንም ብለን ያሰብነውን ሁሉ አድርጎት እናገኘዋለን። ሆኖም ግን መዳረሻችን አኺራህ ነውና ለሁሉም ነገር ሶብር ማድረግ፣ ለሙእሚን ከዱንያ ይልቅ አኺራህ የተሻለ መኖሪያው መሆኑን ማሰብ፣ ዱንያ ሁሉ ነገሯ ፈተና የሆነች መሆኗን ማወቅ ያስፈልጋል።

አላህ በሪዝቁም ይሁን በትዳር በኩል መልካሙን ይወፍቃችሁ።



ወንድማችሁ፦ ሙራድ ታደሰ
=========
ሸዋል 13, 1445 H.C.
ሚያዚያ 14, 2016 E.C
አፕሪል 22, 2024 G.C.

||
t.me/MuradTadesse